ከታህሳስ ዐስር በፊት የወላይታ የክልልነት ጥያቄ ለምርጫ ቦርድ እንዲመራ ጥያቄ ቀረበ

0
759

‹‹ክልሉ በኮማንድ ፖስት ስር የሚገኝ በመሆኑ እንደዚህ አይነት ማስፈራሪያዎችን የሚቀበልበት አቋም የለውም›› የደቡብ ክልል

ከአንድ ዓመት በፊት ለደቡብ ክልል ከወላይታ ዞን ለቀረበው የክልልነት ጥያቄ እስከ ታኅሳስ አስር ለምርጫ ቦርድ እንደመራ እና የክልልነት ጥያቄው በሕግ አግባብ ብቻ እንዲደረግ የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ (ወብን) ጥሪ አቀረበ።

በቅርቡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ሌሎች ከፍተኛ ባላሥልጣና ጋር ውይይት ያካሔዱት የወብን ተወካዮች ‹‹ጠቅላይ ሚኒስተሩ ወላይታ የክልልነት ጥያቄ ካነሱ ሌሎች ዞኖች ጋር በጋራ አንድ ክልል ሆኖ እንዲቆይ እና ዋና ከተማ እንዲሆን ያቀረቡት አስተያየት አግባብ አይደለም፣ የወላይታ ሕዝብ ጥያቄ የክልልነት እንጂ የዋና ከተማነት አይደለም›› በማለት ተቃውሞውን ገልጸዋል።

የወብን የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ተከተል ላቤና እንዳሉት፣ ዞኑ እስከ አሁን ተገቢውን ምላሽ ማግኘት ያልቻለ ሲሆን ኅዳር 21/2012 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ርስቱ ይርዳው፣ የደኢሕዴን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሙፈሪያት ካሚል በተገኙበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምርጫ ቦርድ ‹‹አቋማችሁ ይህ ከሆነ ግን ለምርጫ ቦርድ እና ለደቡብ ክልል ምክር ቤት ሪፈረንደሙን እንዲያካሒዱ እነግራቸዋለሁ›› ብለዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ በኩል ‹‹የወላይታ ዞን አቃፊ ዞን ነው፤ በክልል መደራጀቱ የወላይታ ሕዝብን አይጠቅምም። በመሆኑም ከሌሎች ተመሳሳይ ጥያቄ ካላቸው ዞኖችን በማቀፍ ሶዶ ከተማን መሰረት ባደረገ መልኩ አብራችሁ ብትቀጥሉ›› የሚሉ ሐሳቦች ተነስተው ነበር ያሉ ሲሆን፣ ውይይቱ ዞኑ የክልልነት ጥያቄውን ወደ ጎን እንዲተው የሚወተውት ነበር ብለዋል።

የዞኑ ተወካዮችም ‹‹የሌሎች ሕዝቦች ጥያቄዎች ለራሳቸው ለሕዝቦቹ ሊመለስላቸው ይገባል። የወላይታ ዞን ጥያቄ ለራሱ ሕዝብ ነው እንጂ ለሌሎች ሕዝቦች ሊሆን አይችልም።›› የሚሉ ምላሾችን መስጠታቸውን ገልጸው፤ የክልልነት ጥያቄው ምላሽ እንዲያገኝ እና ሕዝባዊ አመፅ እና ውድመት እንዳይደረስ አሳስበናል ብለዋል።
የወጣት አደረጃጀቶች ታኅሳስ ዐስር የወላይታ ክልልን ለማወጅ በተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያ ቅስቀሳ እየተደረገ መሆኑን ያነሱት የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊው ተከተል፣ ፓርቲአቸው ለመንግሥት የተወሰነ ጊዜ በመስጠት ጥያቄው እንዲፈታ መሞከር የተሻለ አማራጭ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

‹‹መንግሥት ሕገ መንግሥታዊ መብታችንን እንዲያከብር ግፊት እናደርጋለን፣ ነገር ግን በዚህ ምክንያት ያልተፈለጉ ቀውሶች መከሰት የለባቸውም›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የወላይታ ዞን ለደቡብ ክልል ምክር ቤት በክልል የመደራጀት ጥያቄን በ2011 ታኅሳስ ወር ያቀረበ ሲሆን፣ ጥያቄው ከቀረበ አንድ ዓመት ሊሞላው ከአስራ አምሰት ቀናት ያነሰ ጊዜ ይቀረዋል።

የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ (ወብን) በጉዳዩ ላይ ለአዲስ ማለዳ በሰጠው ማብራሪያ፣ እስከ አሁን በተለያዩ አደረጃጀቶች አማካኝነት ጥያቄው ሰላማዊ ሰልፎችን በማከናወን ቢቀርብም አፋጣን ምላሽ ሊሰጠው እንዳልቻለ ገልጿል።

ይህንንም ተከትሎ ሕዝቡ በከፍተኛ ቁጣ ውስጥ ይገኛል የተባለ ሲሆን፣ የዞኑ ምክር ቤት ጥያቄውን ለክልሉ ምክር ቤት ካቀረበ አንድ ዓመት ሊሞላው ደኢሕዴን እና የክልሉ ምክር ቤት ጥያቄውን ለማፈን ጥረት እያደረጉ በመሆኑ በቀሩት ቀናት አስቸኳይ ጉባኤ ተጠርቶ ጥያቄው ለምርጫ ቦርድ እንዲቀርብ ወብን አሳስቧል።
በደቡብ ክልል በሚነሱት የክልልነት ጥያቄዎች ላይ በደኢሕህዴን በተደረገው ጥናት ላይ በተለያዩ ከተሞች ውይይት ሲደረግ ከወላይታ ሕዝብ ጋር ውይይት አልተደረገም የሚሉት ተከተል፣ ታኅሳስ 10 በወላይታ ሶዶ ከተማ ትልቅ ክስተት ይኖራል ብለዋል።

ደኢሕዴን አስጠናሁት ባለው ጥናት መሰረት የክልልነት ጥያቄው የሕዝቡ ጥያቄ ስለመሆኑ ጥርጣሬ አለው የሚሉት ስማቸው እንዳይገለፅ የፈለጉ በደቡብ ክልል የሚገኙ የአዲስ ማለዳ ምንጮች፣ በክልሉ በኩል ጥያቄው ከሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄ ተከትሎ የመጣ ነው። ስለዚህ ሕዝቡን በድጋሚ የማወያየት አቋም እየተንፀባረቀ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

አክለውም በክልሉ ተመሳሳይ ጥያቄ ያላቸውን ዞኖች በአንድ ላይ በማድረግ ለመስቀጠል ታስቧል ያሉ ሲሆን፣ ክልሉ በኮማንድ ፖስት ስር የሚገኝ በመሆኑ እንደዚህ አይነት ማስፈራሪያዎችን የሚቀበልበት አቋም የለውም ብለዋል።

የደቡብ ክልል መንግሥት የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ኀላፊ ሠናይት ሰሎሞን በበኩላቸው፣ ጥያቄው ታኅሳስ 10/2011 ለክልሉ ምክር ቤት መቅረቡን የገለፁ ሲሆን፣ ጥያቄው ሕገ መንግሥታዊ መሰረት ያለው ነው ብለዋል። አክለውም ጥያቄው በበርካታ ዞኖች በተመሳሳይ ወቅት ላይ የቀረበ መሆኑን ተናግረዋል።

የክልሉ መንግሥት የወላይታን ጥያቄ መልሶ የሌሎች ዞኖችን ጥያቄ ወደ ጎን የሚተውበት ምክንያት የለምም ብለዋል። የደቡብ ክልል ከምክር ቤቱ እና ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ጥያቄዎቹ በሚመለሱበት መንገድ ዙሪያ ውይይት እያደረገ ይገኛል ያሉ ሲሆን፣ የክልሉ መንግሥት ተመሳሳይ ጥያቄ ካላቸው ሕዝቦች ጋር እስከታች በመውረድ ውይይት ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆኑን ገልፀዋል።

የክልልነት ጥያቄው የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄ በተስተናገደበት ሰላማዊ መንገድ ይፈታል ተብሎ ይጠበቃል ያሉ ሲሆን፣ ከታኅሳስ ዐስር በኋላ የሚኖሩት ጉዳዮች ጊዜው ሲደርስ የሚታወቁ ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ሲዳማ፣ ወላይታ፣ ጉራጌ፣ ከምባታ እና ሐዲያን ጨምሮ በርከት ያሉ ዞኖች የየራሳቸው ክልላዊ መንግሥት ለማዋቀር ጥያቄ ማቅረባቸው ይታወሳል።

የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 47 ንዑስ አንቀጽ ኹለትና ሦስት ለብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ስለመመሥረት መብት የሚደነግጉ ሲሆን፣ በንዑስ አንቀጽ ኹለት የተዘረዘሩት ‹‹በዘጠኝ ክልሎች ውስጥ የተካተቱት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች በማንኛውም ጊዜ የየራሳቸውን ክልል የማቋቋም መብት አላቸው›› ሲል ንዑስ አንቀጽ ሦስት ደግሞ ይህ መብት ሥራ ላይ የሚውልባቸውን ሒደቶች ያትታል።

ማንኛውም ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ የራሱን ክልል የመመሥረት መብት ሥራ ላይ የሚውለው የክልል መመሥረት ጥያቄው በብሔሩ፣ በብሔረሰቡ ወይም በሕዝቡ ምክር ቤት በኹለት ሦስተኛ ድምፅ ተቀባይነት ማግኘቱ ሲረጋገጥና ጥያቄው በጽሑፍ ለክልሉ ምክር ቤት ሲቀርብ፣ ጥያቄው የቀረበለት የክልል ምክር ቤት ጥያቄው በደረሰው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለጠየቀው ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ወይም ሕዝብ ሕዝበ ውሳኔ ሲያደራጅ፣ ክልል የመመሥረት ጥያቄው በብሔሩ፣ በብሔረሰቡ፣ ወይም ሕዝቡ ሕዝበ ውሳኔ በአብላጫ ድምፅ ሲደገፍ፣ የክልሉ ምክር ቤት ሥልጣኑን ለጠየቀው ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ሲያስረክብና በሕዝበ ውሳኔ የሚፈጠረው አዲስ ክልል ጥያቄ ማቅረብ ሳያስፈልገው በቀጥታ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አባል ሲሆን ነው ይላል።
የወላይታ ዞን የክልልነት ጥያቄ ለክልሉ ምክር ቤት በ 2011 ታኅሳስ 10 የቀረበ ሲሆን፣ አንድ ዓመት ሊሞላው ከ 15 ቀናት ያነሰ ጊዜ ቀርቶታል።

ቅጽ 2 ቁጥር 57 ኅዳር 27 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here