ባለፈው ዓመት ትርፋቸው ቢሊዮን ብር ከተሻገረ ሦስት የግል ባንኮች አንዱ ነበር
ወጋገን ባንክ አክሲዮን ማኅበር በ2011 የበጀት ዓመት ያስመዘገበው ያልተጣራ ትርፍ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ315 ሚሊዮን ብር ቅናሽ ማስመዝገቡን ባንኩ አስታወቀ። በተለይም ባለፈው በጀት ዓመት ሁሉም በኢትዮጵያ የሚገኙ የንግድ ባንኮች የትርፍ እድገት ባሳዩበት ዓመት፣ ወጋገን ይህ ዓይነት ውጤት ማስመዝገቡ ያልተጠበቀ ሆኗል።
ወጋገን ባንክ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ማትረፍ ከቻሉ ባንኮች መካከል ተቀላቅሎ የነበረ ሲሆን፣ በተያዘው ዓመት ግን የትርፍ ቅናሽ አሳይቷል። ባንኩ ያስመዘገበው ትርፍ ከቅርብ ተፎካካሪው አቢሲኒያ ባንክ ጋር ሲነጻጸር፣ በ300 ሚሊዮን ያነሰ ሲሆን፣ በሌሎች ዘርፎች ውጤቱ ያነሰ ሆኗል።
በ2010 የበጀት ዓመት ከግብር በፊት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ አስመዝግቦ የነበረው ባንኩ፣ በ2011 የበጀት ዓመት ግን ወደ 735 ሚሊዮን ብር ገደማ ዝቅ ብሏል። ባንኩ ከግብር በኋላ 620 ሚሊዮን ብር ትርፍ ያገኘ ሲሆን፣ ከአንድ ዓመት በፊት ያጣራው ትርፍ ግን 793.5 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ነበር።
ባንኩ ይፋ ያደረገው ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ ከኦፕሬሽን የሚገኘው ገቢ ከ 2 ነጥብ 24 ቢሊዮን ብር ወደ 2 ቢሊዮን ብር ዝቅ ብሏል። በተመሳሳይም የባለ አክሲዮኖች የትርፍ ክፍፍል ድርሻ ከ 36 ነጥብ 5 በመቶ ወደ 25 ነጥብ 6 በመቶ ወርዷል።
የተሰበሰበ የሃብት መጠን በ2009 እና 2010 በአምስት መቶ ሚሊዮን ብር ሲያድግ፣ ከነበረው መጠን በመውረድ በሦስት መቶ የሃምሳ ሚሊዮን ብር ብቻ እድገት አስመዝግቧል። የተሰጠ የብድር መጠን እድገትም ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር ቅናሽ በማሳየት በ 150 ሚሊዮን ብር ብቻ ጭማሪ አሳይቷል።
በበጀት ዓመቱ ከተከፈቱ የ‹ሌተር ኦፍ ክሬዲት› ክፍያዎች እና ኮሚሽን ያገኘው ገቢም በ 324 ሚሊዮን ብር ቅናሽ ያሳየ ሲሆን፣ ባንኩ ከዚህ ቀደም ሃብቱን ካፈሰሰባቸው ኢንቨስትመንቶች ሽያጭ ያገኘው ገቢም ከ 107 ሚሊዮን ብር ወደ 1.3 ሚሊዮን ብር ወርዷል።
ወጋገን ባንክ በቅርብ ሲፎካከራቸው የነበሩት አዋሽ፣ ዳሽን፣ አቢሲኒያ እና ኦሮሚያ ባንክ በተያዘው በ2012 ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ አጠቃላይ ትርፍ አስመዝግበዋል።
አዋሽ ባንክ በተገባደደው በጀት ዓመት ያስመዘገበው ያልተጣራ ትርፍ 3.3 ቢሊዮን ብር፣ ካለፈው ዓመት አንጻር የ70 በመቶ ብልጫ ይዟል። ከተመሠረተ 24 ዓመታትን ያስቆጠረውና የመጀመሪያዎቹን 21 ዓመታት ከግል ባንኮች ከፍተኛውን ትርፍ በማስመዝገብ መሪ የነበረው ዳሽን፣ 1.3 ቢሊዮን ብር ትርፍ አስመዝግቧል። በተመሳሳይ የአቢሲኒያ ባንክ ትርፍ ከአምናው የ766 ሚሊዮን ብር አንጻር የ57 በመቶ ብልጫ አሳይቷል።
በሌላ በኩል የተመሠረተበትን ዐሥረኛ ዓመት በማክበር ላይ የሚገኘው ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ 1.2 ቢሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታውቋል።
የወጋገን ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ መንግሥተአብ ገበረኪዳን፣ በቻይና እና በአሜሪካ መካከል የተፈጠው የንግድ ጦርነት በዓለማቀፉ ኢኮኖሚ ላይ ያመጣው ጫና የዓለማቀፉ ኢኮኖሚ የሚያድግበትን ፍጥነት ቀንሶታል ብለዋል። በዓመታዊ ትርፍ መግለጫ ላይ ባስተላለፉት መልእክት፣ ዓመቱ በኢትዮጵያም ቢሆን የፖለቲካ ቀውስ፣ የውጪ ምንዛሬ እጥረት፣ ባለ ኹለት አሃዝ የዋጋ ንረት እና የብድር ጫና መብዛት የፈተነው ነው ብለዋል።
አጠቃላይ የደንበኞቹ ቁጥር 1.3 ሚሊዮን የደረሰው ባንኩ፣ በ2011 የበጀት ዓመትም 341 ሺሕ አዳዲስ ደንበኞችን ማፍራቱንም ገልጿል። በበጀት ዓመቱ 62 አዳዳስ ቅርንጫፎች የተከፈቱ ሲሆን፣ ይህም አጠቃላይ የቅርንጫፍ ቁጥሩን 339 አድርሶታል።
ምርቶች ላይ ናሙና ተወስዶ የጥራት ፍተሻ እንደሚደረግበት ተናግረዋል።
ሜጀር ጄነራል መሐመድ ጨምረው፣ ኤታማጆር ሹሙ እና ምክትል ኤታማጆር ሹሙ በተደጋጋሚ ለብሰውት የሚታዩት የውጊያ ልብስ አዲሱ ዲዛይን መሆኑን አረጋግጠዋል። እንደ ኀላፊው ገለጻም ልብሱ በተደጋጋሚ ተለብሶ እና ተሞክሮ ጥራቱ ሊረጋገጥ ችሏል።
በምርት ሒደት ከኹለት ጊዜ በላይ ባለሞያዎች እየተላኩ ናሙና በመውሰድ እና በዓለማቀፍ ላቦራቶሪ በማስገምገም ጥራቱን መከታተላቸውንም አዲስ ማለዳ ከምንጮቿ ሰምታለች። የአንድ የደንብ ልብስ ዋጋ ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ ባይቻልም፣ አሁን የሚገባው የደንብ ልብስ ከቀደመው የ 20 በመቶ ጭማሪ እንዳለው አዲስ ማለዳ አረጋግጣለች።
በተመሳሳይም ከዚህ ቀደም ሠራዊቱ የደንብ ልብሱን ገዝቶ የሚጠቀም የነበረ ሲሆን፣ ይህንን የደንብ ልብስ ግን መንግሥት ሙሉ ወጪውን በመሸፈን በዓመት ከአንድ ቅያሪ ጋር እንደሚሰጥ አዲስ ማለዳ ከታማኝ ምንጮቿ ተረድታለች።
ከአየር ጸባይ እና ከመልክአ ምድራዊ አቀማመጥ ጥናት እንዲሁም የመስክ ሙከራ የተደረገበት ይህ ልብስ፣ የዲዛይን ፓተርኑ እስከዛሬ ከነበረው ዘመኑ ወዳፈራው ተለውጧል።
ሜጀር ጄነራል መሐመድ እንዳሉት፣ የሠራዊቱ የደንብ ልብስ ከሚቀየርባቸው ምክንያቶች መካከል ልብሱ ለሕገወጥ ተግባር ሲባል በተለያዩ ሰዎች እጅ በመግባቱ ነው። አክለውም የደንብ ልብሱ የሚቀየርበት መመሪያ የሚዘጋጅ ሲሆን፣ አወጋገዱ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ እንደሚሆንም ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም የመከላከያ ሠራዊት የደንብ ልብስ አገር ውስጥ ይመረት የነበረ ሲሆን፣ ከአንድ ዓመት በፊት በውጪ ተዘጋጅቶ መጥቷል። በዓመት ከሚሰጠው ኹለት የደንብ ልብስም አንዱን አባላቱ እንዲገዙ የሚደረግ ሲሆን፣ ጡረታ በሚወጡ ጊዜም በገንዘባቸው የሚገዙትን ልብስ ለማስመለስ አስቸጋሪ እንደነበርም ሜጀር ጄነራል መሐመድ ተናግረዋል።
አዲስ ማለዳ ባደረገችው ማጣራትም በትግራይ መልሶ ማቋቋም ድርጅት (ኤፈርት) ባለቤትነት የሚተዳደረው እና ከአድዋ ከተማ ሰባት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው አልመዳ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ የሰራዊቱን የደንብ ልብስ ያቀርብ ነበር። ፋብሪካው በድረ ገጹ ላይ የወታደር ልብሶችን እንዲያመርትም ይገልፃል።
ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ሒደት የኢትዮጵያም ሆነ የዓለማቀፍ የጉምሩክ ሥነ ስርአቶች እንዲሁም የመርከብ ጭነት ሒደቶች ካላዘገዩት፣ በተባለው ጊዜ ቅያሬው እንደሚገባደድ ኀላፊው ተናግረዋል።
ከደንብ ልብስ ባሻገርም የሠራዊቱን የጥቅማ ጥቅም ጥያቄዎች ለማሻሻል የሕግ ሥራዎች ተጠናቀዋል ሲሉ ሜጀር ጄነራል መሐመድ ተናግረዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 59 ታኅሣሥ 11 2012



