ተለዋዋጭ የምንዛሬ ስርዓቱ ጉዳት እሴቶቻችን ድረስ የሚዘልቅ ነው

0
539

ታህሳስ 1 ቀን ላይ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይኤምኤፍ በድረ-ገፁ እንዳስነበበው የዓመቱን የአንቀጽ አራት ውይይት ለማድረግ የድርጅቱ ሰዎች ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር በተገናኙበት ጊዜ ባለሥልጣናቱ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ለማስፈፀም የሚሆን 2.9 ቢሊዮን ዶላር በሦስት ዓመት እንዲለቀቅላቸው ጠይቀው ነበር።ይህንን ተከትሎ በተደረገው ድርድር ሁለቱ ወገኖች በገንዘብ ተቋሙ የሥራ አስፈፃሚ ቦርድ መጽደቅ የሚቀረው የቅድሚያ ስምምነት እንዳደረጉ ይታወቃል።በዚህ ስምምነት መሰረት ኢትዮጵያ ገንዘቡን ለማግኘት ስትል የተቀበለቻቸው ተቋሙ እንዲተገበሩ የሚፈልጋቸው ፖሊሲዎች አሉ።ይህ የፖሊሲ ማዕቀፍ አምስት ዋና ዋና ምሰሶዎች አሉት።
ከእነዚህ ምሰሶዎች መካከል በመጀመሪያ ደረጃ የተጠቀሰው የውጭ ምንዛሬ እጥረቱን በዘላቂነት መፍታት እና ወደ የበለጠ ተለዋዋጭ የሆነ የምንዛሬ ስርዓት መሻገር የሚለው ነው።ተለዋዋጭ ምንዛሬ የሚባለው በፍላጎት እና አቅርቦት ላይ ተመርኩዞ የምንዛሬ መጠኑ የሚወሰንበት የገንዘብ ስርዓት ነው።ይህም እስከ አሁን ኢትዮጵያ ስትከተል ከነበረው በብሔራዊ ባንክ ውሳኔ ከሚወጣው የምንዛሬ ተመን በተቃራኒ የቆመ ነው።
ምንዛሬውን ገበያው ይምራው ከተባለ በጥቁር ገበያ ላይ ያለው ዋጋ ሕጋዊ ይሁንና ብሔራዊ ባንክ የምንዛሬ መጠን ማውጣቱን ያቁም ማለት ነው።ይህ ማለት ደግሞ በአሁኑ ጊዜ በባንኮች ያለው ከ32 ብር ለአንድ ዶላር የምንዛሬ መጠን ወደ 40 ወይም ከዚያ በላይ ከፍ ይበል ማለት ነው።በመሆኑም ተለዋዋጭ የገንዘብ ስርዓት መከተል ማለት ባለው የኢትዮጵያ ሁኔታ የብርን አቅም ከተለያዩ ዓለም አቀፍ መገበበያያዎች አንፃር መቀነስ ማለት ነው።ይህ ደግሞ የዛሬ ሁለት ዓመት እንዲሁ የአይኤምኤፍን የአንቀጽ አራት ውይይት ተከትሎ በብሔራዊ ባንክ በ15 በመቶ እንዲቀንስ የተደረገውን እርምጃ አጠናክሮ የሚያስቀጥል ነው።
የዛሬ ሁለት ዓመት አንድ ዶላር 22 ብር ይመነዘር የነበረ ሲሆን ይህ ስምምነት ምንዛሬውን ወደ 43 ብር ከፍ አድርጎ የብርን የመግዛት አቅም በግማሽ እንደሚቀንሰው ይጠበቃል።ባለፉት ሁለት ዓመታት ያየነው የዋጋ ግሽበት በመጪው ጊዜ የሚቀንስ እንዳልሆነም የሚጠቁም ነው።የኑሮ ውድነት እያንገላታን ከሆነ የሚመጣው ጊዜ የሚቀብረን ይሆናል።የዋጋ ግሽበት ደግሞ የቁሳቁሶችን ዋጋ ከማናር ባለፈ የግለሰቦችንም ሆነ የማህበረሰብን ባህሪና ትውፊት የሚነካ ችግር ነው።ሰዎች ኑሮ በከበዳቸው ጊዜ ቀደም ብለው የሥነምግባር ጥሰት የሚመስሏቸውንም ነገሮች ለማድረግ ይገደዳሉ።እስከአሁን የመጣንበትን መንገድ እንኳን መለስ ብለን ብንቃኝ በአገርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሰማው የሥነ ምግባር መሸርሸር፣ የማህበራዊ እሴቶች መናድ እና ቀውስ ከገንዘብ የመግዛት ኃይል ማሽቆልቆል ጋር ቀጥተኛ ተዛማጅነት አላቸው።በመሆኑም የኑሮ ውድነት ማህበረሰብ የነበሩት እሴቶች እንዲጠፉና ቻርልስ ዳርዊን ያለውን ዓይነት ጠንካሮች ብቻ የሚኖሩባትን ዓለም የሚፈጥር ከባድ ችግር ነው።በዚህ ተፈጥሯዊ ምርጫ ውስጥ ለመካተት ደግሞ ሰዎች ቀድሞ የማይቀበሏቸውን አዳዲስ አስተሳሰቦች ይቀበላሉ።የማህበራዊ ደህንነትም ከዚሁ ጋር ተያይዞ ይቀንሳል።በመሆኑም ይህን ዓይነቱን የከፋ ማህበራዊ ችግር የሚጋብዘውን ርምጃ አዲስ ማለዳ ትቃወመዋለች።
በተጨማሪም የምንዛሬ መጠኑን ገበያው የሚቆጣጠረው ከሆነ የውጭ ኃይሎች በእኛ ገበያ ላይ የሚገኘውን የዶላር መጠን ከፍ እና ዝቅ በማድረግ ምንዛሬውን የሚቆጣጠሩበት እድል ይፈጠራል።በመሆኑም ስምምነቱ ተለዋዋጭ የምንዛሬ ስርዓት እንዲፈጠር ብቻ ሳይሆን የሚያደርገው የምንዛሬ ተመኑን ቁጥጥር ከኢትዮጵያ መንግሥት ወደ ውጭ ኃይሎች አሳልፎ የሚሰጥ ነው ማለት ይቻላል።
ይህንን ተደራራቢ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች የሚያስከትል ርምጃ ማደባበስ ወይም መካድ ችግሮቹን የሚያስቀር አይደለም።መንግሥት ይህንን ተለዋዋጭ የምንዛሬ ፖሊሲ ለመተግበር መዘጋጀቱን ተከትሎ ባለፈው አንድ ወር ብቻ በብር ላይ ስድስት በመቶ ገበያን መሰረት ያደረገ ቅናሽ (depreciation) ታይቷል።መንግሥት የምንዛሬ ማሻሻያ ካደረገበት ጊዜ ውጭ ባለፈው አምስት ዓመታት ገበያን መሰረት ያደረገው የምንዛሬ ቅናሽ በዓመት ከሁለት እስከ አምስት በመቶ ሆኖ ቆይቷል።ባለፈው አንድ ወር የታየው ይህ ያልተለመደ ትልቅ ቅናሽ ፖሊሲው እየተተገበረ መሆኑን የሚያሳይ ነው።
መቼም መተግበር ላይ ከደረሰ ይህ ርምጃ የሚያመጣውን ጥቅም መንግሥት አምኖበታል ማለት ነውና ጥቅሙን ለመዳሰስ ያናገርናቸው ባለሙያዎች የብር አቅም መዳከም በዓለም አቀፍ ገበያ የውጭ ገበያ ምርቶቻችን ሳቢ እንዲሆኑ ያደርጋል ይህም ኢንቬስተሮች ኢትዮጵያ ውስጥ መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ ይጋብዛል የሚል ነው።ይህም ለኢኮኖሚ ዕድገት ጉልህ እስተዋጽኦ የሚያደርግ መሆኑ ታምኖበታል።
ነገር ግን ወደ ውጭ ከምንልከው ጋር በማይመጣጠን መንገድ ወደ አገር ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ ቁሳቁሶችን የምናስገባ አገር በመሆናችን በምንዛሬው የብር ዋጋ መቀነስ የእኛን ምርቶች ዋጋ አርክሶ ከውጭ የሚመጡትን የሚያስወድድ ነው።የዚህም ውጤት በገቢና ወጪ ንግድ ላይ ያለውን ያለመመጣጠን የሚያሰፋና ለበለጠ ችግር የሚዳርገን ነው፡፡
ለዓመታት አይኤምኤፍ ሲወተውትና የኢትዮጵያ መንግሥት ሲያደርግ እንደኖረው የዶላርና የብር ንፅፅር የዛሬ 30 ዓመት በፊት ከነበረው የአንድ ዶላር በሁለት ብር ምንዛሬ በአሁኑ ጊዜ ወደ አንድ ዶላር በ32 ብር ምንዛሬ ዝቅ ብሏል።ባለፉት ዐስር ዓመታትም ብናይ የንፅፅር ቅናሹ ቀጥሎ የቆየ ቢሆንም የውጭ ንግዳችን ግን አይኤምኤም እንዳለው ጨምሮ ሳይሆን ቀንሶ ነው የተገኘው።በመሆኑም የውጭ ንግዱ ችግር የብር ጠንካራነት እንዳልሆነ የሚጠቁሙ ምልክቶች አሉ።ለውጭ ንግድ የሚሆኑ ምርቶች በበቂ ሁኔታ ያለመመረት ለምሳሌ አንዱ ጠንካራ ምክንያት ነው።የግብርና ምርታማነት የሚያሳድጉ ግብዓቶችን (ማሽኖች እና ሌሎችም ግብዓቶች) ለማስገባት ያለው ከፍተኛ ችግርና ከፍተኛ ግብር ሌላው ምክንያት ነው።በመሆኑም ለዓመታት ሊጨበጥ ላልተቻለው የብርን ተነፃፃሪ ዋጋ የመቀነስ ጥቅም ብሎ እስካሁን የተዘረዘሩትን ችግሮች ማባባስ ትክክለኛው መንገድ እንዳልሆነ አዲስ ማለዳ ታምናለች።
ለውጭ ገበያው መስፋት እና የበለጠ ኢንቬስትመንት ለመሳብ ደንቃራ ሆነዋል ተብለው ከሚጠቀሱ ምክንያቶች አንዱ የቢሮክራሲው ረጅም እና ውስብስብ መሆን ነው።ይህ ችግር ከሌሎች አገሮች ጋር ሲነፃፀር ጠንካር ያለ ሆኖ ከተገኘ ኢንቬስተሮች ቀለል ያለበትን አገር ይመርጣሉ።ይህንን ለማሻሻል የሕዝብ አገልጋዮችን ብቃት ማሳደግ አስፈላጊ ነው።ከዚያ አንጻር ተመጣጣኝ የገቢ ጭማሪ በሌለበት የሚኖር የኑሮ ውድነት ይህን ኃይል ለሙስና እና አጠቃላይ የሞራል ልሽቀት የሚገፋ እና ያለውንም ችግር የሚያባብስ ነው።ባለው ሁኔታ እንኳን እየናረ የመጣውን የቤት ኪራይ፣ የትራንስፖርት፣ የምግብ፣ የልጆች ትምህርት፣ የልብስ እና ሌሎችም ወጪዎችን መቋቋም የከበደው የሕዝብ አገልጋይ ከዚህ ውሳኔ በኋላ ጎዳና እንዳይወጣ ያሰጋል።
እንዲህ ዓይነቱ ማህበራዊ ችግር ሲደራረብ ደግሞ መንግሥት ላይም ስጋት ሊያመጣ የሚችል የፖለቲካ እና የደህንነት ችግር መሆኑ የማይቀር ነው።በሥራ አጥነት፣ የፖለቲካ ጽንፈኝነት፣ የክልልና ማዕከል ፖለቲካ፣ የተለያዩ መሰረተ ልማቶች ያለመሟላት እንዲሁም ሌሎች ቁጥር ስፍር የሌላቸው ትልቅም ሆኑ ትንሽ ችግሮች የተወጠረው የአብይ አሕመድ (ዶ/ር) መንግሥት ያሉበትን ችግሮች የሚያባብስ ሌላ ውሳኔ አያስፈልገውም።በመሆኑም ይህ አደጋው የበዛ የአይኤምኤፍ የፖሊሲ ምክረ ሀሳብ እንዳይተገበር አዲስ ማለዳ ትጠይቃለች።

ቅጽ 2 ቁጥር 59 ታኅሣሥ 11 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here