ጣና በለስ ስኳር ልማት ፕሮጀክት ለሀብት ብክነትና ለዜጎች የኑሮ መጎሳቆል መንስኤ ነው ተባለ

0
549

ጣና በለስ ስኳር ልማት ፕሮጀክት ለሀብት ብክነትና ለዜጎች የኑሮ መጎሳቆል መንስኤ ሆኖ መገኘቱን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታወቀ።

ፕሮጀክቱ ከበለስ ወንዝ የመስኖ ውሃ መጥለፍ፤ በ75 ሺሕ ሄክታር መሬት ላይ ሸንኮራ አገዳ ማልማት፤ አርሶ አደሮችን ከመሬታቸው ላይ በማንሳት አርሶ አደሮች በሰፈራ ማዕከላት ማስፈር፤ መሰረተ ልማት ማሟላት እና ሦስት የስኳር ፋብሪካዎችን መገንባት እንደሚያጠቃልል ተገልጾ የነበረ ሲሆን፣ ሥራዎቹ በ2003 ተጀምረው በአራት ዓመታት ውስጥ እንደሚጠናቀቁ ተገልጾ ነበር።

ፕሮጀክቱ ሦስት ክፍሎች ሲኖሩት ሦስቱም ግንባታቸው ተቋርጦ እና ለግንባታ ግብአት በቦታው የሚገኙ እቃዎች ያለመጠለያ ዝናብ እና ፀሐይ እየተፈራረቀባቸው እንደሚገኝ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢዎች፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በቦታው ላይ በመገኘት ባደረገው ምልከታ ማረጋጋጡን አስታውቋል።

የበለስ ቁጥር 2 ግንባታ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን 25 በመቶ አከናውኖ ለስኳር ኮርፖሬሽን አስረክቦ የወጣ ሲሆን፣ የበለስ ቁጥር – 3 ግንባታ 18 ሚሊዮን ብር ፈጅቶ የቆመ እና የፋብሪካውም ዕቃዎች ለብልሽት እየተዳረጉ መሆናቸውን ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል። ለዘጠኝ ዓመታት በሸንኮራ አገዳ የለማው መሬት 13 ሺሕ 147 ሄክታር እና የተፈጠረው የሥራ ዕድልም በአሁኑ ሰዓት 3 ሺሕ 525 ብቻ ነው ተብሏል።

የጃዊ ወረዳና የአዊ ዞን የመሬት ባለቤት እና አምራች የነበሩ 4 ሺሕ 310 አባወራና እማወራ በሕዝብ ብዛት 19 ሺሕ 310 ሰው ለእንስሳትም ሆነ ለእርሻ የማይመችና በቂ ያልሆነ መሬት ላይ ሰፍሮ ተመፅዋች ሆኖ ከግለሰቦችና ከመንግሥት ዕርዳታ እየተሰፈረለት እንደሆነ ነው የተገለጸው። ቋሚ ኮሚቴው ከመንግሥት እና ከተራድኦ ድርጅቶች በሚገኝ ድጋፍ ሕይወታቸውን ለመምራት መገደዳቸውን አስታቋል።

እነዚህ ሥራዎች ለ69 ሺሕ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩ እና በዓመት 7,620,000 ኩንታል ስኳር፣ 62 ሺሕ 481 ሜ.ኩብ ኢታኖል እና 135 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ኃይል ማምረት እንደሚያስችሉ በግንባታው መጀመሪያ ላይ ሲጠቀስ ቆይቷል።

ቅጽ 2 ቁጥር 60 ታኅሣሥ 18 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here