ጋዜጠኞች ሲታሰሩና ሲደበደቡ የሚከራከርላቸው ባለመኖሩ የሚዲያ ስራ አደጋ ውስጥ ነው ተባለ

0
536

መረጃ ሲጠየቁ መስጠት የማይፈልጉ፣ ስልካቸውን እና ቢሯቸው ለተራው ዜጋ ብቻ ሳይሆን ለጋዜጠኞች ዝግ ያደረጉ፤ ሲፈልጉ ብቻ የሚናገሩ እንጂ ሲጠየቁ የማይመልሱ የመንግስት ተቋማት እና ኃላፊዎች በርካታ መሆናቸውን ያነጋገርናቸው ጋዜጠኞች ገልጸዋል።

“አብዛኛዎቹ” የመንግስት ተቋማት መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸውና በተለይም ለግል የሚዲያ አውታሮች ከተቋማቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች እና አመራሮች ምላሽና መረጃ ማግኘት ቀላል አለመሆኑን አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን የሚሰሩ ጋዜጠኞች ያማርራሉ።

አዲስ ማለዳ ይኼንኑ የመረጃ ማግኘት ተግዳሮትን በተመለከተ በቀጥታ የሚመለከታቸውን የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም እንዲሁም የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኀን ማኅበርን ለምን እና መፍትሔውስ ስትል ጠይቃለች።

ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታውን ያደረገ ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ ጋዜጠኛ “በመደበኛ እንዲሁም ጠንካራ ወይንም ፖለቲካዊ ይዘት ባለው ጉዳይ መረጃ ለማግኘት ከመንግስት ተቋማት እንዲሁም ከፌደራል እና ከክልል አመራሮች ስልክ ካለማንሳት ጀምሮ ምላሽ ላለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆን፣ የመፍራትና ወደ ሌላ አካል የመምራት ነገር በስፋት ይስተዋላል” ይላል።

አንዳንዴ ስራው የሚፈልገውን ፍጥነት ካለመረዳትም ይሁን ወይም በሌላ ምክንያት ለአስር ደቂቃ ቃለ መጠይቅ ከጠዋት ሶስት ሰዓት ለአስር ሰዓት ይቀጥራሉ በማለትም ያማርራል።

የሕዝብ ግንኙነቶች በጉዳዩ ላይ ያላቸው የመረጃ ውስንነት ፈተና ከመሆኑ ባሻገር “የማን አለብኝት ስሜት አይነት ነገር ይስተዋልባቸዋል። መረጃ መስጠት ግዴታቸው መሆኑን ፈጽሞ ይዘነጋሉ። የሕዝብ ግንኙነት ክፍል የተቋቋመበት ዋናው አላማም ሕዝቡ የሚፈልገውን መረጃ መስጠት ነበር” ሲል ጋዜጠኛው ገልጿል።

በኢትዮጵያ መረጃን የማግኘት መብት አሁን በሥራ ላይ ባለው የመረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 ክፍል ሦስት ላይ፣ ዜጎች መረጃ የማግኘት ሕገ መንግሥታዊ መብት እንዳላቸውና የመረጃ ባለቤቶች ስለመሆናቸው ይደነግጋል። መረጃን የማግኘት መብት ሲባል ከማንኛውም መንግሥታዊ አካል ዜጎች መረጃን ለመጠየቅ፣ ለማግኘትና ለማስተላለፍ ያላቸውን መብት እንዲረጋገጥ፣ መረጃ ፈላጊዎች በተቻለ መጠን በፍጥነትና በዝቅተኛ ወጪ ሳይደክሙ የሚያገኙበት አሠራርና ሥነ ሥርዓት በመመሥረት፣ መብቱ ተፈጻሚ እንዲሆን የሚፈቅድና የሕዝብ ተሳትፎና የሥልጣን ባለቤትነትን የማረጋገጥና የአሠራር ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና ውጤታማነት የሰፈነበት የመንግሥት አሠራርና መልካም አስተዳደር የማጠናከርን ዓላማ የያዘ መሆኑ በአዋጁ ተብራርቷል።

በዚሁ አዋጅ ላይ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊነቶች በዝርዝር የተቀመጠ ሲሆን፤ መረጃ መከልከል የሚችሉባቸው የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች ወይንም የፋይናንስ ደህንነት ጉዳት ላይ ሊጥል የሚችል፣ የአገርን ጸጥታና ደህንነት ሊጎዳ የሚችል፣ የግለሰብን ህይወት ለአደጋ የሚያጋልጥ ከሆነ እንዲሁም በአዋጁ ከተጠቀሱ ዝርዝር እና ግልጽ ምክንያቶች በስተቀር የሕዝብ ግንኙነቶች ኃላፊነቶች በግልጽ ሰፍሮ ይገኛል።

በተቋማት በኩል ለመረጃ ክፍት የሆኑ ሁኔታዎች አለመመቻቸት ለበርካታ የሚዲያ ባለሞያዎች ፈተና መሆኑን እንረዳለን ሲሉ በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ስራ አስፈጻሚ አብዱ አሊ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ሆኖም ግን “የሙያ ስነ ምግባሩን የተከተለ የጋዜጠኝነትን መርህ አክብሮ የሚንቀሳቀስ ሙያተኛ ትክክክለኛ፣ ሚዛናዊ እና ወቅታዊ መረጃ ባደረሱ ቁጥር የመረጃ አቅርቦቶም በዛው ልክ ክፍት ይሆናል፤ በአንጻሩ ተዓማኒ መረጃ የማያቀርቡ ከመርህ ያፈነገጡ ጋዜጠኞች በተበራከቱ ቁጥር ተቋማት መረጃ ከመስጠት እንዲታቀቡ ያድረጋቸዋል” ብለዋል።

የትምህርት ሚኒስቴር፣ የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ትራንስፖርትና ሎጅስቲክ ሚኒስቴር፣ የማዕድን ሚኒስቴር፣ የኢንዱስትሪ ግብዓት አቅራቢ ድርጅት፣ የስኳር ኮርፖሬሽን፣ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን እና የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን መስሪያ ቤቶች መረጃና ምላሽ ለማግኘት አዳጋች መሆናቸውን ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉ ጋዜጠኞች በተደጋጋሚ ጠቅሰዋቸዋል።

ከትምህርት ሚኒስቴር መረጃ ማግኘት የማይቻል መሆኑን በርካታ ጋዜጠኞች የሚስማሙበት ሲሆን፤ ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደርገ አንድ ጋዜጠኛ ከትምህርት ሚኒስቴር በአንድ ወቅት መረጃ በስልክ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ ባለመሳካቱ ወደ ተቋሙ ቢሄድም የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዋ ምላሽ ልትሰጠው ፈቃደኛ ባለመሆኗ ግጭት ውስጥ መግባቱን አስታውሷል። በሌላ ጊዜ የትምህርት ሚኒስትሩን ብርሃኑ ነጋ ከሚመሩት ተቋም መረጃ ማግኘት እንዳልተቻለ አግኝቶ በነገራቸው ወቅት “በቃ መረጃ ስትፈልግ እኔ ጋር ደውልልኝ” የሚል ምላሽ ሰጥተውኛል ብሏል።

በተመሳሳይም ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረገች ጋዜጠኛ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ያለው አሰራር ምንም ግልጽ ያልሆነ ለመረጃ ፈጽሞ ክፍት ያልሆነ ተቋም መሆኑን በማንሳት፤ የጤና ሚኒስቴር ከዚህ ቀደም ከነበረው ጥሩ የመረጃ አሰጣጥ ሂደት በቅርቡ በተቋሙ የተደረገውን አዲስ መዋቅር ተከትሎ መረጃ ለማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን ታዝቤያለሁ ስትል ተናግራለች።

መረጃ ላለመስጠት የተቋሙን ስልክ እያወቁ አለማንሳት፣ መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ነኝ ብለው ቀጠሮ አስይዘው ሐሳብ የመቀየር እንዲሁም በጉዳዩ ላይ ለጊዜው መረጃ አንሰጥም ብለው ምላሽ መስጠት ተደጋጋሚ መሆኑን ጋዜጠኞቹ ጠቁመዋል።

ተጠሪነቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሆነው የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን፤ መረጃ ለመስጠት ቅድመ ሁኔታዎች እንዳሉ የሚገልጹት ጋዜጠኞቹ ለባለስልጣኑ ደብዳቤ ከተላከ በኋላ፤ ምላሽ ማግኘት የሚቻለው ከ15 ቀናት በኋላ ወደ ሚመለከተው ክፍል ይመራ በሚል ተጨማሪ ቀናቶችን የሚወስድ መሆኑን አመላክተዋል።

ባለስልጣኑ በመገናኛ ብዙሃን በተደነገገው አዋጅ ከዓላማዎቹ በግንባር ቀደምነት የተጠቀሰው ሃሳብን በነጻነት የመግለጽና የመገናኛ ብዙሃን ነጻነትን በተሟላ መልኩ እንዲረጋገጥ ምቹ ሁኔታቸው መፍጠር ቢሆንም፤ ነጻ እንዲሁም ገለልተኛ መሆን ሳይችል መቅረቱን ያነሳሉ። አዋጁ ግን “ባለስልጣኑ ከመንግሥት፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሚቆጣጠረው የመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ፣ ከሃይማኖት ተቋማት፣ ከንግድና ከሌሎችም ማኅበረሰባዊ ቡድኖችና ተቋማት ገለልተኛና ነፃ መሆን ይኖርበታል” ሲል ይደነግጋል።

በደብዳቤ ጠይቁ የሚሉ የመንግስት ተቋማት መደበኛውን አሰራር ለመከተል ከመሻታቸው ባሻገር መረጃ ያለመስጠት ፍላጎታቸው ማሳያ ነው ሲሉ ጋዜጠኞች ይተቻሉ። በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ላይ በቀረበው ቅሬታ የማይስማሙት የባለስልጣኑ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ስራ አስፈጻሚ አብዱ አሊ “አንዳንዴ ለመወንጀል የሚመስል ነገር ይስተዋላል” በማለት ጋዜጠኞች ሰፊ ትንታኔ ሲፈልጉ በቀጥታ ከባለሙያው ጋር እንዲገናኙ ለማድረግ ሲባል ደብዳቤ እንዲያስገቡ የሚጠየቁበት አሰራር መኖሩን ገልጸዋል። ነገር ግን “መረጃ ፈላጊ ጋዜጠኞች ደብዳቤውን አስገብተናል ብለው ደብዳቤው ግን ሲፈለግ አይገኝም። በዚህም ምክንያት ድጋሜ እንዲያስገቡ ይጠየቃሉ” ብለዋል።

አክለውም ሰፊ የሆነ ትንታኔ የሚፈልጉ በሚሆንበት ጊዜ በጉዳዩ ላይ የሕዝብ ግንኙነት መረጃ ከሚሰጥ በጉዳዩ ላይ ባለሞያ ቢሰጥ የተሻለ ይሆናል በሚል መሆኑን በማንሳት፤ “ይኼ ደግሞ ትክክለኛውን መረጃ እንዲያገኙ ከማድረግ አንጻር እንጂ መረጃ ለመከልከል አይደለም” ሲሉ የጋዜጠኞችን ወቀሳ አስተባብለዋል።

በዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ባለሞያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ “መረጃ የማግኘት ችግር በአገራችን ከረጅም ጊዜ ጀምሮ የነበረ ችግር ነው” ይላሉ። በአዋጁ በግልጽ መረጃ ስለማግኘት መብት የተደነገገ ቢሆንም አንድ ተቋም አሊያም አመራር መረጃ በመከልከሉ ተጠያቂ የሚሆንበት ሕግ ባለመኖሩ “የግል ሆነ የመንግስት የሚዲያ ተቋማት መረጃ ለማግኘት እንደሚቸገሩ” የማህበሩ ፕሬዝዳንት ገልጸዋል።

በየዘመኑ ወደ ሥልጣን የሚመጡ መንግሥታት ሥልጣን በተረከቡ ማግሥት ፈጥነው ለውጥ ከሚያደርጉባቸው መስኮች መካከል የሐሳብና የአመለካከት ነፃነት፣ የመገናኛ ብዙኃንና የፕሬስ ውጤቶችን ያለገደብ ተግባራዊ ማድረግና የመሳሰሉ ቢሆኑም፤ ዘላቂነታቸውን ግን ማረጋገጥ እንዳልተቻለ ፕሬዝዳንቱ ይገልጻሉ።

ለአብነትም የደርግ እና የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ታሪኮችን የጠቀሱት ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ አሁን ወደ ስልጣን የመጣው የብልጽግና መንግስት “ጅማሮው እጅግ ጥሩ ነበር። ሕጎችና ደንቦች የተሻሻሉበት ነበር” ብለው “ወዲያው ደግሞ ጋዜጠኞች ሲታሰሩና ሲደበደቡ መመልከት ችለናል። ለእነርሱም ጠበቃ ሊሆንላቸው ሊከራከርላቸው የቻለ ባለመኖሩ የፕሬስ እንቅስቅሴ ላይ ጥላውን አጥልቷል” ብለዋል።

ድንበር የለሽ ጋዜጠኞች (reporters without borders) ዓለም አቀፍ ተቋም ባወጣው የ2024 የፕሬስ ነጻነት ሪፖርት ባለፈው ዓመት 130ኛ ደረጃ ላይ የነበረችው ኢትዮጵያ፤ በዚህ ዓመት 141ኛ ደረጃን ከ180 አገራት ይዛ መገኘቷን ገልጿል።

ከስድስት ዓመታት በፊት የታየው የሚዲያ ነጻነት አውድ የማንነት ግጭቶች እና የእርስ በእርስ ግጭቶች ሳቢያ ተቀልብሶ አሳሳቢ ሁኔታ መፈጠሩን ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች ተቋም ያስታወቀ ሲሆን በወቅታዊነት ደግሞ በአማራ ክልል የቀጠለው በትጥቅ የታገዘ ግጭት የጋዜጠኞችን ስራ ጫና ውስጥ እያስገባ እንደሆነ አዲስ ማለዳ ከሪፖርቱ ተገንዝባለች። ባለፉት አምስት ወራት ብቻ 15 ጋዜጠኞች እስካሁን መታሰራቸውንም ተቋሙ ገልጿል።

የመረጃ ነፃነት አዋጁ በግልጽ እንዳስቀመጠው አስፈጻሚ አካላት ከሕዝብ በሚሰበሰብ ግብር የሚተዳደሩ ቢሆኑም፣ ለሕዝቡ የሚጠበቅባቸውን መረጃ እያደረሱ አለመሆናቸውን በተለያየ ጊዜ ሃሳባቸው የሚያነሱ ሰዎች የሚያንጸባርቁት ነው።

የመንግሥት ተቋማት ከሕዝብ በሚሰበሰብ ሀብት የሚተዳደሩ ከሆነ ስለሚሰጡት አገልግሎት ለህብረተሰቡ በየወቅቱ መረጃ ይፋ ማድረግ ቢኖርባቸውም፣ የአስፈጻሚ አካላቱ የመረጃ አሰጣጥ ግን የተቋማቸውን ገጽታ ይጠብቁልኛል የሚሏቸውን መረጃዎች እየመረጡ መስጠት ላይ ብቻ እንደሚያተኩሩ ይጠቀሳል። ይህ ሁሉ መረጃ በመስጠት ሊመሰገኑ የሚገቡ ተቋማት እና የመንግስት አመራሮች እንደተጠበቁ ነው።

ጋዜጠኞቹ ካነሷቸው ተቋማት መካከልም የአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ የትራፊክ ማኔጅመንት፣ የአዲስ አበባ ብሔራዊ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የደንብ ማስከበር ባለስልጣን፣ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት እንዲሁም ንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ለመረጃ ክፍት እንደሆኑ የሚጠቀሱ ናቸው።

በአማራ ክልል በመንግስትና በክልሉ የሚገኙ ታጣቂ ሃይሎች ጋር በተቀሰቀሰው ግጭት “እንኳንም ዘንቦብሽ የነበረው” የመረጃ ማግኘት ችግር አድማሱን ማስፋቱን ጋዜጠኞቹ የሚስማሙበት ሲሆን፤ ከግጭቱ ወዲህ ክልሉ በራሱ እና በክልሉ ሚዲያ በኩል ከሚያወጣቸው ጉዳዮች በተጨማሪ መረጃ ጠይቆ ማግኘት የሚታሰብ አለመሆኑ ገልጸዋል።

በክልሉ ስላለው ግጭት እና ስለደረሰው ጉዳት መጠየቅ “ጉንጭ ማልፋት ነው” የምትለው አንድ ጋዜጠኛ በሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ጭምር መረጃ ለማግኘት አለመቻሉ፤ የሰላም እጦት በአገሪቷ ቀድሞ የነበሩ ችግሮችን ይበልጥ የሚያሰፋ መሆኑ ማሳያ ነው ትላለች።

በዚሁ በጋዜጠኛዋ ሃሳብ የሚስማሙት የባለሞያዎች ማህበሩ ፕሬዝዳንት ጥበቡ በለጠ አሁን በአገሪቷ ባለው የሰላም እጦት ምክንያት “መረጃ ማግኘት ቅንጦት ሆኗል” ያሉ ሲሆን፤ ጋዜጠኞች በተለያዩ ቦታዎች ተዘዋውረው የሚዘግቡበት አስቻይ ሁኔታዎች አለመኖራቸውን ጠቁመዋል። አሁን ላይ የጋዜጠኛ መታወቂያ ይዞ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ እንደ ቀድሞው የይለፍ መታወቂያ መሆኑ ቀርቶ “ለአደጋ የሚያጋልጥ” ሆኗል ይላሉ። መፍትሄው በቅድሚያ ቆም ብለን የአገር ሰላም፣ አንድነት እና መረዳዳትን መሻት ነው ብለዋል።

ከግል ሚዲያ እና በመንግስት ሚዲያ መካከል መረጃ ለማግኘት ያለው ሂደት ፈጽሞ የተለያየ መሆኑን የሚያነሱት ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉ ጋዜጠኞች፤ የመንግስት ሚዲያዎች መረጃዎች ቀድመው እንደሚደርሷቸው በተለያዩ የመግለጫ አሰጣጥ ሂደቶች ላይ ቅድሚያ የሚያገኙበት ሁኔታ መኖሩን ያነሳሉ።

በተለይም በአገሪቷ የሚገኙ አገር አቀፍ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተቁማት እንደ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ካሉ ተቋማት መረጃ በስፋት ሲያገኙ የሚስተዋሉት እነዚሁ “የመንግስት የሚዲያ ተቋማት” በሚል የተለዩት ናቸው ይላሉ። በተመሳሳይም ከገዢው ፓርቲ እነዚሁ የመንግስት ሚዲያዎች ያለምንም ገደብ መረጃ ሲያገኙ በአንጻሩ በግሉ ዘርፍ የተሰማሩ የሚዲያ ባለሙያዎች ቁንጽል መረጃዎችን ብቻ እንደሚያገኙ ጋዜጠኞች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በዚህም ከገዢው ፓርቲው ይልቅ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች መረጃና ምላሽ ለማግኘት የሚቻልበት ሁኔታ የተሻለ መሆኑን በመጠቆም ‘የግል ሚዲያና የመንግስት ሚዲያ’ የሚለው መከፋፈል ተገቢ ካለመሆኑ ባሻገር ሁለቱም ለሕዝቡ ሁሉን አቀፍ መረጃ መስጠት እንዳይችሉ ያደርጋል ይላሉ።

የመንግስት ሚዲያዎች ይበልጥ መረጃዎችን ያገኛሉ በሚለው እንደማይስማሙ የሚገልጹት ጥብቡ በለጠ በመንግስት ሚዲያ ላይ የሚቀርቡ የተቋማት አመራሮች ሆኑ የሕዝብ ግንኙነቶች የተቋማቸውን ገጽታ ለመገንባትና ከፍ ለማድረግ፣ ስራቸውን ለማስተዋወቅ እንጂ የሕዝብን ጥያቄ ለመመለስ፣ ሙግትና ጥያቄ ለመቀበል እና መረጃ ለመስጠት ባለመሆናቸው መረጃ ያገኛሉ ማለት አይቻም ሲሉ ይገልጻሉ።

በአንጻሩ ጋዜጠኞቹ ባለፈው 37ኛው የአፍሪካ ሕብረት ጉባኤን ለመታደም አንድም የመንግስት ሚዲያ እንዳይሳተፍ ባልተደረገበት ሁኔታ በስፍራው የተገኙት ሃገሬ፣ አሻም፣ ባላገሩ እና አሃዱ ቲቪና ሬድዮ መግባት መከልከላቸው የመንግስትና የግል ሚዲያ በሚል ያለውን አድልዖ ማሳያ መሆኑን ያነሳሉ።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ሃሳባቸውን የሰጡት የባለስልጣኑ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ስራ አስፈጻሚው “በወቅቱ በተፈጠረው ችግር በአጠቅላይ ዱላው ያረፈው እኛ ጋር ነው። እውነታው ግን እሱ አይደለም” በማለት የአፍሪካ ሕብረት የኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ከሌሎች የአፍሪካ አገራት የተገኙ ሚዲያዎችንም የከለከለበት ሁኔታ እንደነበር አስታውሰዋል። “የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ምንም ጣልቃ አይገባም። የአፍሪካ ሕብረት ልክ እንደሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት የራሱ አሰራር ነው። የራሱ ቴክኒካል ጉዳይ ነው ተስተካክሎ ምናልባት ሰዓቱ ስላለፈ ነው እንጂ ጉዳዩን አስተካክሎ የሰበሰበውን መታወቂያ መልሷል” ብለዋል።

ቢሆንም “እነዚህ ነገሮች ሲፈጠሩ አይ አድልዖ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ተደርሶ ነበር፤ እንደተቋም ሁሉንም ሚዲያዎች እኩል በመመልከት ነው አገልግሎት የምንሰጠው” ሲሉ ገልጸዋል።

አክለውም “ለመንግስት የመገናኛ ብዙሃን ተለይቶ መረጃ መረጃ የሚሰጥበት ሂደት መኖሩን አላውቅም” የሚሉት አብዱ አሊ፤ “ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ለሚዲያዎች ፈቃድ ሲሰጥ ዋና አላማው በመረጃ የበለጸገ ማህበረሰብ መፍጠር ነው። የመንግስት ሚዲያዎችን ላይ ብቻ ትኩረት ማድረግ እንደማያዋጣ እናውቃለን” ይላሉ።

“ከዚህ ቀደም በነበረኝ የስራ ተሞክሮ መረጃዎችን ለማግኘት እና ለህዝቡ ለማድረስ የምሄድበት እርቀት እንግልት የበዛበት አልነበረም” የሚለው ሌላው ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታውን ያደረገው ጋዜጠኛ “አሁን ግን አንድን መረጃ ለማግኘት በጣም አስቸጋሪ እና ፈታኝ ጊዜን አሳልፋለሁ” ይላል፡፡

ተቋማት እና ግለሰቦች መረጃ ለመስጠት እንደሚፈሩ የገለጸ ሲሆን፤ የመንግስት ተቋማት የገጽታ ግንባታቸው የሚበላሽባቸው መስሎ ስለሚሰማቸው እና በሚሰሩት ስራ ተጠያቂነት እንዳይመጣባቸው በመስጋት መረጃዎችን የመሸሸግ ነገር በስፋት የሚስተዋል እንደሆነ ጠቁሟል።

ህብረትሰቡ ደግሞ “አንድም በሰጠው መረጃ ብዙ እንግልቶች እንዳይደርሱበት እና ለቤተሰቡም ስለሚፈራ መረጃ ይሸሽጋል” ብሏል። በተመሳሳይም ህብረተሰቡ ለሚዲያ መረጃ መስጠት ምንም መፍትሄ እንደማያመጣ በማሰብም መረጃ ለመስጠት እንደሚያመነታ የጠቆመው ጋዜጠኛው፤ በተደጋጋሚ በመብራት፣ በውሃ፣ በኑሮ ውድነት የሚያነሳው ሃሳብ እና የሚሰጠው አስተያየት በቂ የሆነ ትኩረት አግኝቶ ለውጥ አለመምጣቱ ሃሳቡ ከማጋራትና መረጃ ከመስጠት እንዲቆጠብ አድርጎታል ይላል።

የመረጃ ነጻነት ከሦስቱ አንዱ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ የሰብኣዊ መብት አካል ነው። የቀሩት፤ ሐሳብን ያለማንም ጣልቃ ገብነት የመግለጽ እና አመለካከት የመያዝ መብቶች ናቸው። ይህ የሰብዓዊ መብት ኢትዮጵያ አባል በሆነችባቸው የዓለም አቀፍ ስምምነቶች እና በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ተደንግጎ ይገኛል።

የዜጎች ከመንግሥታዊ ተቋማት መረጃ የማግኘት መብት የሕግ ፍልስፍናዊ መሠረቱን የሚያገኘው ተቋማቱ ካላቸው ሕዝባዊ ባህሪ እና የመረጃው ባለቤት አንጻር ነው። ይህም ማለት ተቋማቱ የሚኖሯቸው መረጃዎች የራሳቸው ሳይሆኑ፣ ዜጎችን በመወከል የያዟቸው ናቸው። ስለዚህ ዜጎች የሚጠይቁት የራሳቸውን መረጃ በመሆኑ ተቋማቱ በማንኛውም ጊዜ የማቅረብ ኃላፊነት ይኖርባቸዋል።

አዲስ ማለዳ ከሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የመረጃ ነጻነት ዳይሬክተር ማናዬ ዓለሙ በጉዳዩ ላይ ተቋማቸው ምን እየሰራ እንደሆነ ለመጠየቅ በስልካቸው የደወለች ሲሆን፤ የጽሁፍ መልዕክት ላኩልኝ በማለታቸው ያንን ብታደርግም ምላሻቸውን ማግኝት ሳትችል ቀርታለች።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here