መንግስት ውስን የሆነውን የሀገር ሀብት እያባከነ ነው- ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ

0
816

ማክሰኞ ግንቦት 13 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በጦርነት፣ በተሳሳተ የመንግስት የልማት ፍልስፍና እና ፕሮግራሞች ምክንያት የአገሪቷ ኢኮኖሚ “በጠና ታሟል” ያለው ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ)፤ ከፍተኛ የዋጋ ንረት፣ የምርት እና ምርታማነት መቀነስ፣ ስራ አጥነት፣ የውጭ ምንዛሬ መመናመን የአገሪቱ ኢኮኖሚ መገለጫዎች ሆነዋል አለ።

ፓርቲው የምስረታውን አምስተኛ ዓመት ክብረ በዓል መጠናቀቅ አስመልክቶ ለአዲስ ማለዳ በላከላት መግለጫ፤ “አገሪቷ ካለችበት ውስብስብ የምጣኔ ሀብት ቀውስ ትላቀቅ ዘንድ፣ መንግስት ጥልቅ የማክሮ ኢኮኖሚ እና የፊስካል ፖሊሲ ክለሳ እንዲያካሂድ፣ ውስን የሆነውን የአገር ሀብት ለአብዛኛው ሕዝብ አንገብጋቢ ባልሆኑ ፕሮጀክቶች ላይ ከማባከን ይልቅ የዜጎችን መሰረታዊ እና አጣዳፊ ችግሮች ለመፍታት እንዲያውል” ሲል አሳስቧል።

እንዲሁም መንግስት ከገባበት የማክሮ ኢኮኖሚ ቀውስ ለመውጣት፣ የችግሩን ስረ መሰረት ለመፍታት ጥረት ከማድረግ ይልቅ፣ ጊዜያዊ መፍትሄ ለማበጀት የሚንቀሳቀስ ነው ማለቱን አዲስ ማለዳ ፓርቲው ከላከላት መግለጫ ተመልክታለች።

ሆኖም ግን የአገሪቷ የኢኮኖሚ ቀውስ መሰረታዊ ችግር “የአገሪቷን ተጨባጭ ሁኔታ ታሳቢ ያላደረገው ስሁት የኢኮኖሚ ፖሊሲ እና በስርአት ያልተመራው የኢኮኖሚ አስተዳደር ነው” ያለው ነእፓ፤ ዘላቂ መፍትሄውም የውጭ ብድር ሳይሆን በጠንካራ ዲሲፕሊን የሚመራ የመንግስት የምጣኔ ሀብት አስተዳደር መሆኑን ጠቁሟል።

በመሆኑም መንግስት ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ብድር ለማግኘት የሚያደርገው ጥረት “የአገሪቷን የረዥም ጊዜ ምጣኔ ሀብታዊ እድገት የሚያቀጭጭ እና አገርን ለከፋ የውጭ እዳ ጫና” የሚዳርግ እንዳይሆን ተገቢው ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ ገልጿል።

ነእፓ በመግለጫው የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግስታት በልማት ስም የሚያካሂዷቸው ፕሮጀክቶች የዜጎችን ህይወት እና ደህንነት ታሳቢ ያደረጉ፣ በቂ ጥናት የተደረገባቸው እና መግባባት ላይ የተደረሰባቸው ሊሆኑ ሲገባ ባለፉት ዓመታት መንግስት በልማት ስም የሚያካሂዳቸው ፕሮጀክቶች ዜጎችን ለከፍተኛ እንግልት እና ስቃይ የዳረጉ መሆናቸውን አመላክቷል።

በመሆኑም መንግስት የሚፈጽማቸውን ፕሮጀክቶች በግልጽነት እና በኃላፊነት ስሜት እንዲያካሂድ፣ በዜጎች ላይ ሊደርስ የሚችልን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ታሳቢ ያደረገ እንዲሆን ፓርቲው አሳስቧል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here