መንግስት በኪነ ጥበብ ስራዎችና ባለሞያዎች ላይ የሚያደርሰውን ጫና እንዲያቆም ተጠየቀ

0
294

👉🏿 ተዋናይ አማኑኤል ሀብታሙ እና አዘጋጅ ዳግማዊ አመለወር ታስረዋል 

ቅዳሜ ግንቦት 17 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ኪነ ጥበብን ማፈን የሃሳብ ነጻነትን መጋፋት ስለሆነ ተገቢ ጥበቃ እንዲደረግለት አሳሰበ።

አዲስ ማለዳ ማዕከሉ ዓርብ ግንቦት 16 ቀን 2016 ካወጣው መግለጫ እንደተመለከተችው ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን የሚዳስሱት “ቧለቲካ” እና “እብደት በሕብረት” የተሰኙ መድረኮች በጥር ወር እና ሚያዝያ ወር በተከታታይ የታገዱ ሲሆን የእብደት በሕብረት ተዋናይ አማኑኤል ሀብታሙ እና አዘጋጁ ዳግማዊ አመለወርቅ መታሰራቸውን አረጋግጧል። በርካታ የጥበብ መድረኮችም የስብሰባ ፈቃድ ያስፈልጋችኋል በሚል መስተጓጎላቸው ተገልጿል።

የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ለመንግስት ጥሪ ባቀረቡበት መግለጫ ኪነ ጥበብ ማህበረሰባዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንዲኖረው ነጻነት እና የህግ ከለላ የሚያስፈልገው በመሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ እና በኢትዮጵያ ሕገ መንግስት አንቀጽ 29 ጥበብ እንደ አንድ የሃሳብ መግለጫ መንገድ እውቅና ያለውና ከለላ የሚደረግለት መሆኑን አጽንዖት ሰጥቷል።

ይህ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲ በኪነ ጥበብ ባለሞያዎች እና ስራዎች ላይ እየደረሱ ያሉ ወከባዎች፣ ክልከላዎች፣ እስሮችና ጫናዎች ከዕለት ዕለት እየጨመሩ መሆናቸው አሳሳቢ እንደሆነ አዲስ ማለዳ ከመግለጫው ተረድታለች።

በጥበብ ላይ የሚደረጉ ጫናዎች ማህበረሰቡ ሀሳቡን በነጻነት እንዳይገልጽ የሚያደርጉ ሕገ መንግስታዊ መብትና ነጻነትን የሚጋፉ እንደሆኑ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ገልጿል። “አንዳንድ አገላለጾች የሰላ ትችት ቢሆኑም እንኳን” ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት መሆናቸው መታወቅ አለበት ተብሏል።

ማዕከሉ የኢትዮጵያ መንግስት ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን እንዲያከብር እና እንዲያስከብ፤ በስራቸው ምክንያት የታሰሩ ባለሞያዎችን እንዲፈታ አልያም የተፋጠነ ፍትህ እንዲያገኙ እና የተከለከሉ መድረኮችን በነጻነት እንዲሰሩ መፍቀድ አለበት ብሏል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here