“ሰዎች ከኦርቶዶክሳዊ ቀኖና እና ሥርዓት ባፈነገጠ መልኩ ራስን በራስ የመሾም አባዜ እየተለማመዱ ነው”- ቅዱስ ፓትሪያርክ 

0
163

ረቡዕ ግንቦት 21 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የኢቱዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ዓመታዊ የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በዛሬው ዕለት ሲጀመር ቅዱስ ፓትሪያርኩ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት አባ ማትያስ እንደገለጹት ቤተ ክርስቲያኗ “የውጭው ፈተና ባይቀርላትም ከሱ በላይ ግን በውስጧ የሚነሡ ፈተናዎች ተልእኮዋን በአግባቡ እንዳትወጣ ዕንቅፋት ሆነውባታል”። የወዳጅ ፈታኝ እንደሚብስም በመልዕክታቸው መግለጻቸውን አዲስ ማለዳ ተመልክታለች።

አባ ማትያስ አክለውም “በእግዚአብሔር ቃል የተቃኘ፣ የጸሊአ ሢመትና የጸሊአ ንዋይ መንፈሳዊ ባህሏ ተዘንግቶአል፤ በምትኩም ፍቅረ ሢመትና ፍቅረ ንዋይ ነግሦአል፤ መለያየትና መነቃቀፍ እየሰፉ መጥተዋል፣ ሃይማኖታችንንና ባህላችንን የማይወክሉ ኃይለ ቃላት፣ ኃላፊነት በጐደለው አገላለጽ እየተሰነዘሩ በጎቻችንን አስበርግገዋል፤ ድርጊቶቹ በበጎቻችን ዘንድ የነበረንን ተሰሚነትና ተደማጭነት ሊቀንሱብን እየተንደረደሩ ነው” ብለዋል።

በዚህ የተነሳ ሰዎች ከኦርቶዶክሳዊ ቀኖና እና ሥርዓት ባፈነገጠ መልኩ ራስን በራስ የመሾም አባዜ እየተለማመዱ ነው ያሉት ቅዱስ ፓትሪያርክ ሁሉም ውሉደ ክህነት ለዚህ መልስ መስጠት አለበት ብለዋል። በተጨማሪም “በመልካም አስተዳደርና በቂም በቀል እያሳበቡ ቤተ ክርስቲያንን ለማዳከም ብሎም ለማፍረስ መሮጥ በማናቸውም መመዘኛ ሚዛን አይደፋም፤ ውሃም አያነሣም” ማለታቸውን አዲስ ማለዳ ከቤተ ክርስቲያኗ የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ያገኘችው መረጃ ያሳያል።

ዓቢይ ጉባዔው ወሳኝና ወቅታዊ እንዲሁም ሐዋርያዊና ቀኖናዊ በሆኑ የቤተ ክርስቲያናችን ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ለቤተ ክርስቲያንና ለአገር የሚበጁ ነገሮችን በማየት ጠቃሚ ውሳኔዎችን እንዲያሳልፍ አቡነ ማትያስ አሳስበዋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here