ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝን ተፈጥሮአዊ ፍሰት እንድትጠብቅ የቀረበላትን ጥያቄ ውድቅ አደረገች

0
879

የግብፅ፣ የሱዳን እና የኢትዮጵያ የውሃ ሚኒስትሮች በዓለም ባንክ እና በአሜሪካ ታዛቢነት ከሚያደርጓቸው አራት ስብሰባዎች በሦስቱ ላይ ግብፅ ስታነሳ የቆየቸውን የአባይ ወንዝን ተፈጥሮአዊ ፍሰት የመጠበቅ ጥያቄ ኢትዮጵያ በሱዳኑ ጉባኤ ላይ ውድቅ አደረገች።

ግብፅ እንደ አዲስ ‹ተፈጥሮአዊ ፍሰት ይጠበቅልኝ› ጥያቄዋን ማንሰቷ አግባብ እንዳልሆነ ከታኅሳስ 11 እስከ 12/2012 በሱዳን ካርቱም በተካሔደው ጉበኤ ኢትዮጵያ አቋም ይዛ መውጣቷን እና ይህን ጥያቄ መነሳቱም አግባብ እንዳልነበረ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

‹‹እኛ ልንደራደር የምንችለው በገባው የውሃ መጠን ነው፣ ወደ ታች የማፍሰሱም ሃይቁ ላይ ባለው የውሃ መጠን እንጂ በተፈጥሮ አይወሰንም›› ያሉ ሲሆን ‹‹ይህ ተፈጥሮአዊ ፍሰት የሚለው ቃል በተለያዩ ትርጉሞች በተለያዩ ቦታዎች ተጠቅሷል። ለምሳሌ ኢዲስ አበባም ሆነ ካይሮ በነበሩ ስብሰባዎች ላይ ተፈጥሮአዊ ፍሰት የሚል ሃሳብ ጠረጴዛው ላይ ቀርቧል፣ ይህ ደግሞ ተቀባይነት የለውም›› ሲሉ አፅንኦት ሰጥተዋል።

ተፈጥሮአዊ ፍሰት ማለት የአንድ ወንዝ የላይኛው ተፋሰሶች ምንም ዓይነት ውሃ ሳይነኩ ወይም ምንም ሳያለሙ ይላኩ ማለት መሆኑን የሚናገሩት ስለሺ፣ ‹‹ያ ለውሃ ፈሰት እና አስተዳደር መሰረት ይሆናል ብሎ ማሰብ አግባብ አይደለም›› ብለዋል።

‹‹ኢትዮጵያ እስከዛሬም ታለማለች፤ ወደ ፊትም ታለማለች። ስለዚህ የእኛን የመጠቀም መብት ስለሚገድብም ተፈጥሮአዊ ፈሰት የሚል ቃል በፍጹም መነሳት የለበትም ብለን አስረድተናል። ነገር ግን ሱዳን በነበረው ስብሰባ ውሳኔውን መውሰድ ስላልቻሉ በቀጣይ ድርድር ይዘው የሚመጡትን እናያለን›› ሲሉ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና የግብፁ ፕሬዘዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ በሩሲያዋ ሶቼ ከተማ በግድቡ ዙሪያ ባሉ አለመግባባቶች ላይ ለመደራደር በመወሰናቸው እና ግብፅም አሜሪካ በድርድር ታዛቢነት ላይ እንድትገባ በጋበዘችው መሰረት ሦስት ድርድሮች ተከናውነዋል።

በአዲስ አበባ ተጀምሮ በአዲስ አበባ የሚጠናቀቀው ይህ ድርድር፣ ስድስት ይዘቶች አሉት። የመጀመሪያው የድርድሩ መሰረቶች ሲሆኑ፣ የድርድር መርሆዎች፣ የሙሌት እቅድ፣ የግድቡ የውሃ አለቃቀቅ እና ኃይል ማምረት፣ የማስተባበር እንዲሁም የመረጃ መለዋወጥ እንዲሁም የመተግበሪያ ስልቶች ናቸው።

የድርድሩ የመጀመሪያ ኹለት ነጥቦች ያን ያህል ሰፊ የሚባል ውይይት ያልተደረገባቸው ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም የግድቡ ውይይቶች የሚደረግበት ባለ አስር አንቀፅ የድርድር መርህ መኖሩ አንዱ ምክንያት ነው። ይልቁንም የግድቡ የሙሌት እቅድ እንዲሁም የውሃ አለቃቀቅ ሰፋ ያለ ድርድርን አስተናግደዋል።

በካርቱም የተካሔደው እና በሦስቱ አገራት የኢነርጂ ሚኒስትሮች የተመራው ድርድር፣ ከሞላ ጎደል የተለያዩ ስምምነቶች የተደረሱበት ነው። ነገር ግን ቃለ ጉባኤ ሳይፈረም መገባደዱን የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ ተናግረዋል።

በዚህ ውይይት በተለይም የግድቡን ሙሌት በተመለከተ ድርድር የተደረገ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ በኩል ግድቡ ከአራት እስከ ሰባት ዓመት ይሞላ የሚል ሰንጠረዥ ቀርቧል። የግብፅ ተደራዳሪዎች ግን በአምስት እርከን ይሞላ የሚል ሰንጠረዥ አምጥተዋል። እንደ ሚኒስቴሩ ገለፃም፣ እነዚህ ሰንጠረዦች ተመሳሳይ የሆነ የሙሌት እቅድ ያላቸው ሲሆን እዛ ውስጥ ግን የሚታዩ መሰረታዊ የሆኑ ልዩነቶች አሉ።

በኢትዮጵያ ወገን በተለይም ግድቡ መሞላት ከጀመረ ጀምሮ ባሉ የመጀመሪያው እና የኹለተኛ ዓመት የማመንጨት መጠን ላይ መድረስ ይገባዋል የሚል ሐሳብ ተንፀባርቋል። ይህም የግድቡ ሙሌት ከተጀመረ በኋላ ባለው ኹለተኛ ዓመት የግድቡ ኹለት ተርባይኖችን ወደ ሥራ ሊያስገባ የሚችል ውሃ ወደ ግድቡ መግባት ይገባዋል ሲሉ የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች አቋም ይዘዋል።

በ1913 ተከስቶ እንደነበረው ድርቅ ዓይነት ተከስቶ የአባይ ወንዝ መጠን 20 ቢሊዮን ቢሆን አልያም፣ የግድቡ ሙሌት መሃል ድርቅ ቢያጋጥም ታችኛው ተፋሰስ አገር የሆነቸው ግብፅ እንዴት ትሆናለች የሚል ጥያቄም በመኖሩ በድርድሩ ወቅት ‹ድርቅ› የሚለውን ቃል የመተርጎም ሙግት ተካሒዷል። በኢትዮጵያ ዘንድ ድርቅ መባል ያለበት የውሃ ፍሰቱ ከ 35 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ በታች የሚፈስ ከሆነ ነው የሚል አቋም የተያዘ ሲሆን፣ ይህም የተሰላው በሃይድሮሎጂ ሳይንስ መሰረት መሆኑን ስለሺ ይናገራሉ።

ግብፅ በበኩሏ የውሃ ፍሰቱ ከ 40 ቢሊዮን ሜትር ኩብ በታች ከሆነ ይህ ድርቅ ሊባል ይገባል ስትል ሞግታለች። ይህም ነጥብ ያልተቋጨ እና አሁንም በድርድር ላይ ያለ ነው።

ጥቁር አባይ በዓመት የሚሰጠው የውሃ መጠን በአማካኝ 49 ቢሊዮን በመሆኑ ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝ አማካኝ የውሃ ፍሰት 38 እስከ 52 ያለው ነው፤ ከዛ በላይ ያለው ከፍተኛ ጎርፍ ያለበት፤ ከዛ በታች ያለው ደግሞ ድርቅ ሆኖ እንዲወሰድ ተከራክራለች። ግድቡ ውስጥ ያለው የውሃ አስተዳደር በድርቅ ሰዓት ለታችኛው ተፋሰስ አገራት የሚለቀው የውሃ መጠን እና የመሳሰለው ጉዳይ የሚወሰነው የአጠቃላይ የአባይ ዓመታዊ የውሃ ፍሰት ከ 35 ቢሊዮን ሜትሪክ ኩብ በታች ከሆነ ብቻ ነው የሚል አቋም ተይዟል።

ይህ ድርቅ ግን በሙሌቱ መካከል ቢያጋጥም እንዴት እንወጣዋለን የሚለው ላይም ሌላ ድርድር አለ። ይህም ኢትዮጵያ ውሃውን እየሞላች የሚያጋጥም ስለሆነ አያሳስበንም ሲሉ ስለሺ ገልፀዋል።

‹‹ይህ ድርድር አያስፈልገውም፣ መጠየቅም የለባችሁም በሚል ሐሳብ አንስተናል። ነገር ግን እንደ አጋጣሚ ሆኖ የአስዋን ግድብ መዝጊያው በውሃ እጥረት መሥራት ባይችል እና ተርባይኖቻችን እንዳይጎዱ ልታዩልን ይገባል የሚል ሐሳብ ተነስቷል›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ ድርድሩ ከአባይ ግድብ በዘለለም አስዋንንም ያጠቃለለ እንደሆነ ፍንጭ ሰጥተዋል።

የውሃ ልቀቱ የሚፈለግ እና በየጊዜው የግድቡ የውሃ ይዘት እንዲታደስ ፍላጎት እንዳለ፤ ነገር ግን ይህ የግድቡን ኃይል የማመንጨት አቅም የሚጎዳ መሆን እንደሌለበትም ይናገራሉ። ይህም ድርቁ ከአንድ ዓመት ቢዘል የሚለውን ከግምት ውስጥ በማስገባት የተለያዩ ስሌቶች መቅረባቸውን እና በዛ ላይም የተለያዩ ድርድሮች መካሔዳቸው ተገልጿል።

ሌላው በካርቱም ተካሔዶ በነበረው ድርድር ላይ የአስዋን ግድብ የውሃ ከፍታ በ 165 ሜትር ላይ እንዲጠበቅል እና ዓመታዊ የአባይ ወንዝ የውሃ ፍሰት ደግሞ 49 ቢሊዮን ሜትሪክ ኩብ ላይ እንዲጠበቅ ግብጽ ያቀረበችው ጥያቄ እንዲጣል ተደርጓል። ስለሺ እንደተናገሩት የሱዳኑ ድርድር በዚህ ረገድ ውጤታማ የነበረ እና የመጨረሻውን የትብብር መልክ ያመጣ ነው።

የህዳሴ ግድብ ዋና ሥራ ኃይል ማመንጨት ነው የሚሉት ሚኒሰትሩ፣ ከዛ በኋላ የሚቀሩ ጥቃቅን ስራዎች በተለይም ለኅብረተሰቡ ንፁህ ውሃ ማቅረብ ይሆናል ወይም አነስተኛ መስኖ ማቅረብ ሊሆን ይችላል።

ከዛ በኋላ ግን ውሃውን ወደታች ማሳለፍ የኢትዮጵያ እቅድ መሆኑን አብራርተው፣ ግድቡ ድንበር ላይ መሆኑም የግድቡ ልቀትን እንደሚያረጋግጥ ተናግረዋል። ‹‹ተፈጥሮአዊ ፍሰት ይጠበቅ ማለት በሌላ መንገድ ‹ውሃ አትለነኩም› ማለት ስለሚሆን አንቀበለውም›› ሲሉ ለጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል። የግብፅ ተደራዳሪዎች ሌሎች በኢትዮጵያ የለሙ ግድቦችን አትጠቀሙ ማለት አይደለም፣ ሌላም አይልማ ማለት አይደለም፤ ነገር ግን ቃሉን እንጠቀም ይላሉ።

በሱዳን ካርቱም የነበረው ጉባኤ የተሳካ እና ብዙ ያልጠሩ ነገሮች የጠሩበት ነበር ሲሉ ስለሺ ተናግረዋል። እስከዛሬ ከነበረው ይልቅ የተሻለ ቅን ልቦና የታየበትም ነው።

በአዲስ አበባ የሚደረገው አራተኛ እና የመጨረሻው የድርድር ጉባኤ ስኬታማ የማይሆን ከሆነ ከአምስት አመት በፊት ሶስቱ አገራት ያጸደቁት የመርሆዎች መግለጫ (Declaration of Principles ) አንቀፅ 10ን ወደ ሥራ ለማስገባት ሦስቱም አገሮች መስማማት አለባቸው። አንቀፅ አስር ሦሰት አማራጮችን የሚያቀርብ በአደራዳሪ ማደራደር እና በአገር መሪዎች ቀርቦ ድርድር የሚደረገበት ይገኙበታል።

ኢትዮጵያም ለስትራቴጂ ሲባል ለጊዜው አቋሟን የማትገልጽ ሲሆን፣ ነገር ግን በጥር መጀመሪያ በአዲስ አበባው ስብሰባ በስኬት እንደሚጠናቀቅ እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

ዓለም ባንክ እና አሜሪካ ኢትዮጵያን የሚጨቁኑ እና ሌላውን የሚጠቅሙ አስመስሎ ማቅረብ ትክክል አለመሆኑንም ስለሺ ተናግረዋል። ጉዳዩን የማያውቅ አዲስ አገር ገብቶ የሚያደራድር አለመሆኑን አስረድተው ግብጽ ባቀረበችው መሰረት የሚያደራድሩ ሳይሆን የሚታዘቡ መሆናቸውን ገልፀዋል። ከዚህ በፊት በትንንሽ ነገሮች ክርክሮች የሚከሩበትን አካሄድ በመቀየር ዲፕሎማሲያዊ እና የሰከነ ውይይት የሚደረግበት እንዲሆን ማድረጉንም ተናግረዋል።
ከዓለም ባንክ እና ከአሜሪካ በተጨማሪም የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊን ጨምሮ ሌሎች አለማቀፍ ተቋማት እንደሚከታተሉት እና ኢትዮጵያም እውነት ይዛ ስለምትከራከር ያን ያህል አያሳስባትም ብለዋል።

በዋዜማ ራዲዮ ሚኒስትሩ በተለይ ተፈጥሯዊ የውሃ ፍሰትን በተመለከተ ከባለሞያዎች እና ከተደራዳሪዎች ጋር መጋጨታቸውን መዘገቡን አስተባብለው፣ የተነሱት አቋሞች የእኔም ናቸው ብላዋል። ከስብሰባው ረግጦ የወጣ ሰው የለም ያሉት ኢንጂነሩ፣ ከዚህ ቀደምም የኢትዮጵያን የመደራደሪያ ነጥቦች ከቡድናቸው አባላት መካከል አፈትልኮ መውጣቱን ተናግረው ይህ አሳሳቢ ነው ብለዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 60 ታኅሣሥ 18 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here