ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ፡ በእሳት ጨዋታ?

0
1821

የዛሬ አራት ወራት በፊት የብሔራዊ ባንክ ገዢ የሆኑት ይናገር ደሴ መንግስት የውጭ ምንዛሬ ስርዓቱን ገበያ-መር ለማድረግ ማቀዱን ይፋ ያደረጉት። በወቅቱ ጉዳዩ የብዙዎችን ትኩረት ባይስብም መንግስት ከአይኤምኤፍ፣ ዓለም ባንክ እና ከሌሎች የልማት አጋሮች ወደ ዘጠኝ ቢሊየን ዶላር ማግኘቱን ይፋ ማድረጉን ተከትሎ ነበር ጉዳዩ የመነጋገሪያ ርዕስ የሆነው።

በአንድ በኩል እንደ አይኤምኤፍ ያሉ ተቋማት የውጭ ምንዛሬ ስርዓቱን ገበያ-መር ማድረጉ የውጪ ንግድን ለመጨመር እና የገቢ ንግድን ለመቀነስ ይረዳል ሲሉ ባለሙያዎች ከዚህ ቀደም የነበሩ ተሞክሮዎችን በመግለፅ ይህንን ለማድረግ አይረዳም ሲሉ ይሞግታሉ።

በተለይም በሰባት ዓመት ተኩል ውስጥ ትልቁ የዋጋ ግሽበት በተመዘገበት ወቅት የውጭ ምንዛሬ ስርዓቱን ፍላጎት እና አቅርቦትን መሰረት ያደረገ ማድረግ አያወጣም ይላሉ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች። አገሪቷ ካለችበት የፖለቲካ ቀውስ ጋር ተዳምሮ ይህንን ዓይነት የምጣኔ ሃብት ማሻሻያ ማድረግ ኢትዮጵያ በቀላሉ የማትወጣበት ቀውስ ውስጥ ሊከታት ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ይገልፃሉ።

የአዲስ ማለዳው ሳምሶን ብርሃኔ የምጣኔ ሃብት እና የፋይናንስ ባለሙያዎችን እንዲሁም የመንግስት ስራ ኃላፊዎችን በማናገር እና መጽሐፍቶችን እና ጥናቶች በማገላበጥ ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕስ አድርጎ አቅርቦታል።

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ዴሞክራሲ ባልጎለበተባቸው አገራት በፖሊሲዎች አቀራረጽ እና ውሳኔ አሰጣጥ ላይ ሕዝብ ያለው ተሳትፎ ዝቅተኛ ነው። በኢትዮጵያ ተግባራዊ የተደረጉ ወሳኝ ኢኮኖሚያዊ ውሳኔዎችም በዚሁ መንገድ የንግዱን ማኅበረሰብ ፍላጎቶችንም ሆነ የዜጎች የኑሮ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ባለማስገባት ይተቻሉ። ቀደም ብለው ከተወሰዱ ተመሳሳይ እርምጃዎችም መንግሥት ልምድ ሲወስድ አይስተዋልም። ታዲያ ይህ ዓይነቱ ድርጊት ብዙዎች በድህነት አረንቋ ውስጥ ሆነው ሕይወታቸውን እንዲመሩ ያደረገ ሲሆን ቀላል የማይባሉ ነጋዴዎችን እና አምራቾችን ኪሳራ ውስጥ ከቷቸው አልፏል።

የኢትዮጵያ ብረታ ብረት አምራቾች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ሰለሞን ሙሉጌታ ይህንን በተግባር ከተገነዘቡት መካከል ናቸው። ለአብነትም የዛሬ ኹለት ዓመት አካባቢ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የብርን የምንዛሬ ዋጋ በ15 በመቶ በቀነሰበት ወቅት የተከሰተውን ያነሳሉ። ‹‹ምንም እንኳን ቀደም ብለው የተደረጉ ተመሳሳይ እርምጃዎች የውጪ ንግድ ገቢ ከማሳደግ አኳያ ያስገኙት ውጤት አነስተኛ ቢሆንም፣ መንግሥት የብር ምንዛሬ ዋጋን ለማዳከም አላመነታም። ይህም፤ ብረትን ጨምሮ የተለያዩ ዕቃዎች ዋጋቸው ወዲያውኑ እንዲጨምር ምክንያት ሲሆን፣ ቀላል የማይባል ጉዳት በንግዱ ማኅበረሰብ ላይ አምጥቶ አልፏል›› ይላሉ ሰለሞን፤ ከተሞክሯቸው ሲያስረዱ።

ታዲያ አሁን የብር ምንዛሬ ዋጋ ማስተካከያውን ተከትሎ የተከሰተው የዋጋ ግሽበት ያመጣው ችግር ሳይሽር፣ መንግሥት በጣም ተለዋዋጭ የሆነ ገበያ-መር የውጭ ምንዛሬ ስርዓት ለመተግበር መወሰኑን ይፋ ማድረጉ እንደ ሰለሞን ያሉ ሰዎችን አስደንግጧል። ይህ ዓይነቱ እርምጃ መጀመሪያ ይፋ የተደረገው ከአራት ወራት በፊት የብሔራዊ ባንክ ገዢ በሆኑት ይናገር ደሴ ነበር። ገዢው ከሮይተርስ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ውስጥ በጣም ተለዋዋጭ የውጭ ምንዛሬ ስርዓት እንድምትተገብር ይፋ አድርገው የነበረ ሲሆን፣ ይህም በገበያው ውስጥ ባለው ፍላጎት እና አቅርቦት ላይ እንደሚወሰን ተናግረው ነበር። እርሳቸው ይህን ይበሉ እንጂ፤ ጉዳዩ በመገናኛ ብዙኀንም ሆነ በማኅበራዊ ሚዲያ መወያያ ርዕስ ሊሆን ቀርቶ ስለ ጉዳዩም በተመለከተ መንግሥትም ቢሆን ያለው ነገር አልነበረም።

ይሁን እንጂ፤ ከኹለት ሳምንታት በፊት የዓለም ዐቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይ.ኤም.ኤፍ) ወደ ሦስት ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ለኢትዮጵያ በሦስት ዓመታት ለመስጠት መስማማቱን ማሳወቁን ተከትሎ፣ ጉዳዩ የብዙዎችን ትኩረት ከመሳብ በላይ የመነጋገሪያ ርዕስ ሆኖ ሰንብቷል። በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የድርጅቱ ዋና ቦርድ ገንዘቡን ለኢትዮጵያ ከማፅደቁ ሰዓታት በፊት፣ ከአይኤምኤፍ ገንዘብ መበደር ከእናት መውሰድ እንደማለት ነው ማለታቸው ብዙ ጥያቄዎችን ሲያስነሳ ሰንብቷል።

ከዚህ ባሻገር ኢትዮጵያ ብድሩን ተጠቅማ ትተገብራቸዋለች ብሎ ድርጅቱ ከጠቀሳቸው የፖሊሲ ለውጦች መካከል አንዱ እና ዋነኛው አገሪቷ ተግባራዊ ታደርገዋለች የተባለው ተለዋዋጭ የምንዛሬ ለውጥ ስርዓት ነው። ለነገሩ በዚህ ረገድ አንዳንድ ምልክቶች መታየት ከጀመሩ ሰንበትበት ብለዋል። ለምሳሌ፥ በባለፉት 30 ቀናት ብቻ፤ መንግሥት በሕጋዊው እና በትይዩ የውጭ ምንዛሬ መገበያያ ዋጋ መካከል የነበረውን የ11 ብር ልዩነት ለማጥበብ የብርን የምንዛሬ ዋጋ ከስድስት በመቶ በላይ እንዲዳከም ያደረገው ሲሆን፣ በአሁኑ ሰዓት አንድ ዶላር በባንኮች እስከ 31.5 ብር በመሸጥ ላይ ይገኛል።

ከታየው ምልክት በላይ ግን የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎችንም ጨምሮ ብዙዎችን ያስፈራው መንግሥት ገበያ-መር ተለዋዋጭ ምንዛሬ ስርዓት ከተገበረ ሊመጣ የሚችለው ‹‹የኢኮኖሚ ቀውስ›› ሲሆን፣ ይህም ቢሆን ግን መንግሥትን ያሳሰበው አይመስልም። ምንም እንኳን የፋይናንስ ሚኒስትር ዲኤታ የሆኑት ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ከኹለት ሳምንት በፊት በቢሯቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ መንግሥት ሙሉ ለሙሉ ገበያ-መር የሆነ የውጭ ምንዛሬ ስርዓት (ዋጋው አቅርቦት እና ፍላጎትን ተመርኩዞ በገበያ የሚወሰን) ለመተግበር ዕቅድ የለውም ቢሉም፣ መልሰው ደግሞ አገሪቷ ያለባትን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ችግር ለመፍታት ተለዋዋጭ የሆነ የውጭ ምንዛሬ ስርዓት (በብሔራዊ ባንክ ሳይሆን በገበያ የሚወሰን) እንተገብራለን ማለታቸው ብዙዎችን አልሸሹም ዞር አሉ አስብሏል።

የውጭ ምንዛሬ ስርዓት እና ችግሮቹ
ግርማ በለጠ (ስሙ የተቀየረ) በአዲስ አበባ የሚገኝ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሲሆን ከደሞዙ ባሻገር ወንድሙ ከአሜሪካ በሚልክልለት ገንዘብ ሕይወቱን ይመራል። ቢያንስ በኹለት ወር ወደ 1 ሺሕ ዶላር አካባቢ ከወንድሙ የሚላክለት ግርማ፣ ገንዘቡን በአዲስ አበባ መውጫ ለገጣፎ አካባቢ ለሚያስገነባው መኖሪያ ቤቱ ይጠቀምበታል። ምናልባትም ግርማ የባንክ ሠራተኛ እንደመሆኑ መጠን የሚላክለትን ገንዘብ የሚቀበለው በሕጋዊ መንገድ ነው ተብሎ ሊታሰብ ይችላል። ነገር ግን እውነታው ከዚህ ተቃራኒ ነው። ለግርማ ባንክ መመንዘር ማለት ትልቅ ኪሳራ ሲሆን በዚህም የተነሳ የሁልጊዜም ምርጫው ትይዩ (በተለምዶ ጥቁር) ገበያው ነው።
ለዚህም ምክንያቱ ግልፅ ነው። በትይዩ ገበያ የአንድ ዶላር ዋጋ ከሕጋዊው ገበያ በ10 ብር ይልቃል። ይህም ግርማን ጨምሮ በብዙዎች ዘንድ ተመራጭ እንዲሆን አድርጎታል። በሕጋዊ እና በትይዩ የውጭ ምንዛሬ ገበያዎች መካከል ይህን ዓይነት ሰፊ የሆነ ልዩነት እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ቋሚ የውጭ ምንዛሬ ስርዓት ባላቸው አገራት ዘንድ የተለመደ ነው።

ነገር ግን፤ ለዓመታት መንግሥት የውጭ ምንዛሬ ስርዓቱን ከማስተካከል ወይንም የውጭ ምንዛሬ ማስገኛ መንገዶችን ከማስፋት እና ተያያዥ ተግዳሮቶችን ከመፍታት ይልቅ በትይዩው እና በሕጋዊው የውጭ ምንዛሬ ዋጋ ልዩነት ተጠያቂ ያደርግ የነበረው ሕገወጥ መንዛሪዎችን ነበር። ልዩነቱን ለማጥበብ መንግሥት በብዛት ይተገብር የነበረው አስተዳደራዊ እርምጃዎችን ሲሆን፣ ግባቸውን ከመምታት አኳያ የተሳኩ አልነበሩም። ከብሔራዊ ባንክ 200 ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ኢትዮጵያ ሆቴል አካባቢ ያሉትን የትይዩ የውጭ ምንዛሬ ማዕከላት ጨምሮ በሕገወጥ መንዛሪዎች ላይ እስር እና ሌሎች እርምጃዎችን መንግሥት ቢወስድም በሕጋዊው እና በትይዩው ገበያ መካከል ያለውን ልዩነት ግን ማጥበብ አልተቻለም።

ምንም እንኳን ባለፉት 15 ዓመታት የኢትዮጵያ መንግሥት የምከተለው ፖሊሲ መንግሥት-መር ተንሳፋፊ የውጭ ምንዛሬ ስርዓት (managed floating forex regime) ነው ቢልም፣ እንደ አይኤምኤፍ እና ዓለም ባንክ ያሉ ተቋማት ቋሚ ከሆነው የውጭ ምንዛሬ ስርዓት (fixed forex regime) የተለየ አይደለም ሲሉ ይሞግታሉ። ተቋማቱ ይህ ስርዓት በትይዩዉ እና በሕጋዊው ገበያ መካከል ያለውን ልዩነት እንዳሰፋውም ይናገራሉ። በማስረጃነት ባለፉት አምስት ዓመታት የብር ምንዛሬ የተዳከመው በአማካኝ አምስት በመቶ መሆኑ የውጭ ምንዛሬ ስርዓቱ ምን ያህል ቋሚ እንደነበር ማሳያ ነው ሲሉ ያቀርባሉ። ይህም የብር የምንዛሬ ዋጋ ያለቅጥ እንዲጠነክር እንዲሁም አገሪቷም በዓለም አቀፍ ንግድ ልውውጥ ላይ ያላት ተፎካካሪነት በጣም አናሳ እንዲሆን ማድረጉን ይሞግታሉ።

የብር ምንዛሬ ዋጋ መጠንከር ነው ወይስ ሌሎች መዋቅራዊ ችግሮች ናቸው የውጭ ንግድ ገቢ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳደሩት የሚለው አከራካሪ ቢሆንም፣ አገሪቷ ከውጭ ንግድ የምታገኘው ገቢ በጣም አናሳ መሆኑ ግልፅ ነው። ለምሳሌ፥ ባለፉት ዐስር ዓመታት፤ የውጭ ንግድ ገቢ ከሦስት ቢሊዮን ዶላር ፈቅ ያላለ ሲሆን በተመሳሳይ ወቅት ለገቢ ንግድ የወጣው ወጪ በአምስት ዕጥፍ አድጎ በባለፈው በጀት ዓመት መጨረሻ ወደ 15 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ደርሷል። ይህም የአገሪቷ ንግድ ሚዛን እንዲሰፋ እና የውጭ ምንዛሬ እጥረት ችግር እንዳይፈታ ምክንያት ሆኗል። በርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ የውጭ ንግድ ገቢም ሆነ የንግድ ሚዛኑ ባይሻሻልም፣ ወደ አገሪቷ የሚገባው የውጭ ምንዛሬ ፍሰት ለውጥ አሳይቷል።

የአንድ ወር የገቢ ንግድ ወጪን የማይሸፍን የውጭ ምንዛሬ ክምችት የነበራትን አገር ተረክበው የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ከተለያዩ አበዳሪዎች እና ለጋሾች ጋር በፈጠሩት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ክምችቱን ወደ ሦስት ወር ማሳደግ መቻላቸውን ይፋ ለማድረግ ብዙም ጊዜ አልፈጀባቸውም ነበር። ለአብነትም፤ ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ያገኙትን የኹለት ቢሊዮን ዶላር እና ከሳዑዲ አረቢያ ያገኙትን የግማሽ ቢሊዮን ዶላር አፋጣኝ ዕርዳታዎች መጥቀስ ይቻላል። ግና የወጪ ንግድ ገቢን ጨምሮ ሌሎች የውጭ ምንዛሬ ገቢዎች እዚህ ግባ የሚባል ዕድገት ካለማሳየታቸው ጋር ተዳምሮ የውጭ ምንዛሬ እጥረቱ ሊፈታ አልቻለም።

ይባስ ብሎ፤ አንዳንድ ባንኮች ለውጭ ተጓዦች የሚሰጡትን ኹለት መቶ ዶላር እስከ ማቋረጥ ደርሰው የነበረ ሲሆን፣ ከችግሩ መስፋት የተነሳ አንዳንድ አስመጪዎች የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ሲሉ የተለያዩ ምርቶችን ከሚገባው በላይ ዋጋ ከአገር ውስጥ አምራቾች በመግዛት ከዓለም ዐቀፍ ዋጋ ባነሰ ወደተለያየ አገር እስከ መላክ ደርሰው ነበር። ታዲያ በዚህ መካከል ነበር መንግሥት የውጭ ምንዛሬ ችግሩን እና ሌሎች የማክሮ-ኢኮኖሚ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የአገር በቀል ማሻሻያ ፕሮግራም ይዞ ብቅ ያለው። ከዚህም ውስጥ አንዱ ተለዋዋጭ የምንዛሬ ስርዓት መተግበር ሲሆን፣ የውጭ ምንዛሬ ፍሰትን ከመጨመር አኳያ ትልቅ ሚና ይጫወታል ተብሎ ይጠበቃል።

በእርግጥ ከዓመት በፊት በዓለም ባንክ በተደረገ ጥናት መሰረት ኢትዮጵያ የምትከተለው ቋሚ የሆነ የውጭ ምንዛሬ ስርዓት እንደ ዶላር ያሉ ዋነኛ ዓለም ዐቀፍ መገበያያዎች ፍሰት ከመቀነስ አኳያ ትልቅ ድርሻ እንደነበረው የተገለፀ ሲሆን፣ ከሌሎች አገራት ጋር ያለውን ንግድ እና የካፒታል ፍሰት ገድቦታል። ይህም አገሪቷ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተፎካካሪነት ሲገድበው፣ የንግድ ጉድለት ሰፊ እንዲሆን አድርጎታል ይላል ጥናቱ። እንደ ዓለም ባንክ ገለፃ፤ እስከ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ድረስ የኢትዮጵያ ገንዘብ ከ32 በመቶ በላይ ያለቅጥ የተለቀ ሲሆን (overvalued) ይህም የትይዩ ገበያው እንዲስፋፋ ምክንያት ሲሆን የዶላር ፍላጎት ከአቅርቦቱ አንፃር የላቀ እንደሆነ ማሳያ ነው።

በዚህም የተነሳ አገሪቷ ላይ ያለውን የውጭ ምንዛሬ ፍላጎት ለማሳካት ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ ዕደላ (rationing) ላይ ጥገኛ እንዲሆን ምክንያት እንደሆነ ጥናቱ ይገልጻል። ከዚህ ባሻገር፤ በሥራ ላይ የውጭ ምንዛሬ ስርዓቱ ብርን ያለቅጥ እንዲገዝፍ በማድረጉ በኢትዮጵያ መዋቅራዊ ሽግግርን እንዳደናቀፈ ጥናቱ ያሳያል። በተለይም የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ እንዳያድግ እንቅፋት የሆነ ሲሆን፣ ይህም አዳዲስ ድርጅቶች የውጪ ንግድ ላይ እንዳይሰማሩ በማድረጉ የውጭ ምንዛሬ ፍሰት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል ይላል ጥናቱ።

ኢትዮጵያ ምን ዓይነት የውጭ ምንዛሬ ስርዓት ብትከተል ያዋጣታል?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከመጡ በኋላ የተወሰዱ የተለያዩ እርምጃዎችን ተመልክቶ ኢትዮጵያ ኒዮ ሊብራል ኢኮኖሚ ተከታይ ሆናለች ቢባል ስህተት ላይሆን ይችላል። ይህንን እሳቤ ለማጠናከር እየተወሰዱ ያሉ የተለያዩ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን መመልከት ይቻላል። ወሳኝ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ወደ ግል እንዲዛወሩ የተጀመረው እንቅስቃሴ፣ ለዳያስፖራው እና ለውጭ ባለሃብቶች ዝግ የነበሩ ዘርፎች (መገናኛ ብዙኃንን ጨምሮ) በከፊልም ሆነ ሙሉ ለሙሉ ለውድድር ክፍት መሆናቸው እና ከዋሽንግተን ስምምነት የተቀዳ የሚመስለው የአገር በቀል ሪፎርም አጀንዳውን መጥቀስ ይቻላል። በተጨማሪ መንግሥት ቀስ በቀስ ነፃ እና ገበያ መር እንዲሁም ወድድርን መሰረት ያደረጉ ለማድረግ ካሰባቸው ዘርፎች መካከል አንዱ የውጭ ምንዛሬ ገበያው ነው።

መንግሥት ቃሉን ጠብቆ የውጭ ምንዛሬ ስርዓቱን ተለዋዋጭ ካደረገው ዶላርን ጨምሮ የእያንዳንዱ የውጭ ምንዛሬ ተመን የሚወሰነው በየቀኑ ገበያ ውስጥ ባለው ፍላጎት እና አቅርቦት ላይ ሲሆን፣ ዋጋውም በመንግሥት ያልተገደበ ይሆናል። አይኤምኤፍን ጨምሮ የዚህ ዓይነቱ ስርዓት ደጋፊዎች እንደሚሉት፣ በገበያው መሰረት የውጭ ምንዛሬ ተመኑ ተለዋዋጭ ከሆነ የአጭር ጊዜ የካፒታል ፍሰት የሚቀንስ ሲሆን የገበያ ተሳታፊዎችን በነፃነት እንዲነግዱ እና ተጋላጭ እንዳይሆኑ ያደርጋል።

በተጨማሪ፤ ከዛሬ ኹለት ዓመት በፊት በአይኤምኤፍ ታትሞ የወጣ ጥናት እንደሚያሳየው፣ ይህ ዓይነቱ ስርዓት መንግሥታት ትኩረታቸውን ዋጋ ግሽበት፣ ሥራ እጥነት መቀነስ ላይ እና የአገር ኢኮኖሚ ማረጋጋት ላይ እንዲያደርጉ ይረዳቸዋል። ገበያ-መር የውጭ ምንዛሬ ስርዓት አገራት ዓለም ዐቀፍ ንግድ ላይ በነፃነት እንዲሠሩ ይረዳቸዋል የሚለው ጥናቱ፣ መንግሥታት እንደ በጀት ያሉ የፊሲካል ፖሊሲ መሣሪያዎችን እንዲሁም የገንዘብ ፖሊሲዎችን ውጤታማ በሆነ መልኩ እንዲጠቀሙ ትልቅ ሚና ይጫወታል ሲል ያትታል።

ከዚህ ባሻገር፤ የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ስርዓትን በተመለከተ ባለፈው ዓመት የወጣ የዓለም ባንክ ጥናት ኢትዮጵያ ለምን ተለዋዋጭ የሆነ የውጭ ምንዛሬ ስርዓት መተግበር እንዳለባት ያትታል። እንደ ጥናቱ ገለፃ ከሆነ ይህ ዓይነቱ ስርዓት ብርን ተወዳዳሪ እና ርካሽ የሚያደርገው ሲሆን፣ በአገሪቷ ምጣኔ ሃብት ላይ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት፣ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ እና በአጠቃላይ ምርታማነትን ለማሻሻል አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል። የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ገቢ የግብርና ምርቶች ላይ ጥገኛ መሆኑን ያወሳው ጥናቱ፣ ገበያ-መር ተለዋዋጭ የውጭ ምንዛሬ ስርዓት የብርን ዋጋ በማዳከም አገሪቷ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ተፎካካሪ እንድትሆን በማድረግ የውጪ ንግድ ገቢ እንዲጨምር እንዲሁም የገቢ ንግድ ወጪ እንዲቀንስ ያደርጋል ይላል።

ይህንን በጥናቱ ላይ በቁጥር ያስቀመጠው የዓለም ባንክ፣ የብርን ዋጋ በአንድ በመቶ ማዳከም የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የወጪ ንግድ ገቢ በ1 ነጥብ ዜሮ ስድስት የሚያሳድግ ሲሆን፣ ከግብርና ምርቶች የሚገኘው የወጪ ንግድ ገቢ ደግሞ በ0 ነጥብ 33 በመቶ እንዲያድግ ያደርጋል። በአጠቃላይ ሲቀመጥ፤ በጥናቱ መሰረት የብር ዋጋ በአንድ በመቶ ከተዳከመ፣ የውጭ ንግድ ገቢ በዜሮ ነጥብ አምስት በመቶ ማሳደግ የሚቻል ሲሆን፣ የገቢ ንግድን ወጪ ደግሞ በ0 ነጥብ 6 በመቶ መቀነስ ይቻላል። ይህም የንግድ ሚዛንን በ1 ነጥብ 1 በመቶ ያሻሽላል።

ምንም እንኳን የዓለም ባንክ ይህን ዓይነት አዎንታዊ ለውጥ ብርን በማዳከም ማምጣት እንደሚቻል ቢያስረዳም የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች በዚህ ሐሳብ አይስማሙም። የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አየለ ገላን (ዶ/ር) በዚህ ሃሳብ ከማይስማሙት መካከል ናቸው። ምክንያታቸውንም ሲያስረዱ፣ የዛሬ ኹለት ዓመት መንግሥት የተገበረውን 15 በመቶ የብር ቅናሽ ያነሳሉ። ‹‹ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ መንግሥት የብርን ዋጋ ካዳከመ በኋላ የተገኘው ውጤት አዎንታዊ አልነበረም፥ የውጪ ንግድ ገቢን ሊጨምር እንዲሁም የገቢ ንግድ ወጪን ሊቀንስ አልቻለም›› ይላሉ። መንግሥት ተለዋዋጭ የውጭ ምንዛሬ ስርዓትን ከተገበረ ብርን በየቀኑ ማዳከም ከመሆኑ ውጪ አገሪቷ ልታተርፍ የምትችለው ከቁጥጥር ውጪ የሆነ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ነው የሚሉት አየለ፣ መጀመሪያ ምርታማነት ማሳደግ እና ወደ ውጪ የሚላኩ ምርቶች አቅርቦት ማስተካከል ግዴታ ነው ይላሉ።

በተመሳሳይ እንደ የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ጌታቸው ተክለማርያም ገለፃ ደግሞ፤ ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ መንግሥት የብርን የምንዛሬ ዋጋ ማዳከሙን ተከትሎ የተገኙ ውጤቶች ግባቸውን አለመምታታቸው የገንዘብ ፖሊሲን በመጠቀም የወጪ ንግድ ገቢን ማሳደግ እንደማይቻል ማሳያ ናቸው ይላሉ። ለአብነትም አንድ ወደ ውጪ የሚላክ ምርት የሚያልፍበት ሰንሰለት መታየት እንዳለበት ያነሱት ጌታቸው፣ ይህንን ለማድረግ ከሚወጣው ወጪ ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው እንደ ሎጂስቲክ፣ ጉምሩክ እና ሌሎች የትራንስፖርት ወጪዎች ሲሆኑ የውጭ ምንዛሬ አስተዋፅኦ ከዚህ ውስጥ አናሳ መሆኑን ያነሳሉ።

በዚህ ሐሳብ የሚስማሙት የፋይናንስ ባለሙያው አብዱልመናን ሙሐመድ፣ መንግሥት ቀደምት ተሞክሮዎችን በመገምገም የአይኤምኤፍ እና የዓለም ባንክ ምክሮችን ዝም ብሎ መቀበል እንደሌለበት ያነሳሉ። ‹‹ለምሳሌ ከኹለት ዓመት በፊት በአይኤምኤፍ እና የዓለም ባንክ ግፊት መንግሥት የብርን ዋጋ በ15 በመቶ ቢያዳክምም አገሪቷ ከዋጋ ግሽበት ውጪ ያገኘችው አዎንታዊ ውጤት አልነበረም፤ እርምጃውም ግቡን አልመታም›› ይላሉ አብዱልመናን።
በእርግጥ የአይኤምኤፍ ተቀባይነት በዓለም ዐቀፍ ደረጃ መውረድ ከጀመረ ሰንበትበት ብሏል። በድርጅቱ ምክር ቀውስ ውስጥ ከገቡ አገራት መካከል አርጀንቲናን ለአብነት ማንሳት ይቻላል። ምንም እንኳን የዛሬ አራት ዓመት ገደማ በአይኤምኤፍ ምክር መሰረት የወጪ ንግድ ገቢ ለመጨመር እና የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመፍታት አርጀንቲና ገበያ-መር ተለዋዋጭ የውጭ ምንዛሬ ፖሊሲ ብትተገበርም፣ የተገኘው ውጤት ከዚህ በተቃራኒ ከመሆኑም በላይ አገሪቷ የምጣኔ ሃብት ቀውስ ውስጥ እንድትገባ ምክንያት ሆኗል።

ይህ ፖሊሲ ከተተገበረ በኋላ በሦስት አስርት ዓመታት ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ 53 በመቶ የሚደርስ የዋጋ ግሽበት የተመዘገበ ሲሆን ውሃ፣ መብራት እና ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶች እንዲወደዱ ምክንያት በመሆኑ ብዙዎች በድህነት አረንቋ ውስጥ እንዲማቅቁ ምክንያት ሆኗል። በተጨማሪም፤ የአርጀንቲና መገበያያ ገንዘብ የሆነው ፔሶ ተገማች እንዳይሆን ያደረገው ሲሆን፣ ይህም ዜጎች በአገራቸው ምጣኔ ሃብት ላይም ሆነ ገንዘብ ላይ እንዳይተማመኑ አድርጓቸዋል። ችግሩን ለመፍታት ከዛሬ ኹለት ዓመት በፊት አይኤምኤፍ ወደ 58 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ብድር ለአገሪቷ ቢሰጣትም ከዚህ ችግር ልትወጣ አልቻለችም።

የአርጀንቲና መንግሥት ፖሊሲውን ተግባራዊ ሲያደረግ ቀደም ብለው ስለ አይኤምኤፍ የተሰጡ ምክሮችን ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ ነበረ። በ2002 የኖቤል ተሸላሚ ምጣኔ ሃብት ልሂቅ ጆሴፍ ስቲግሊዝ ባወጡት መጽሐፍ (Globalization and Its Discontents) ላይ፣ በተቋሙ ግፊት በአንዳንድ አዳጊ እና ድሃ አገራት ላይ የተተገበሩ የምጣኔ ሃብት ለውጦች ውጤት ካለማስገኘታቸውም በላይ ከፍተኛ ክስረት አስከትለዋል ብለው ነበር። እንደ ስቲግሊዝ ገለፃ፣ በተለይ በአይኤምኤፍ ብድር ለማግኘት እንደ ቅድመ ሁኔታ የተቀመጡ የምጣኔ ሃብት ማሻሻያዎች – ማለትም ነፃ የካፒታል ገበያ እና የንግድ ዝውውር፣ ፕራይቬታዜሽን፣ ለውጭ ኢንቬስቴሮች ክፍት የሆነ ኢኮኖሚ እና ገበያ-መር የውጭ ምንዛሬ ስርዓት – ድሃ አገራት ምጣኔ ሃብት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ በማሳደሩ ዜጎች በድህነት እንዲማቅቁ ምክንያት ሆኗል።

በተመሳሳይ፤ ታዋቂው አሜሪካዊ የምጣኔ ሃብት ልሂቅ ዊሊያም ኢስተርሊ በ2006 ባወጡት መጽሐፍ ላይ እንደገለፁት፣ ምንም እንኳን አይኤምኤፍ የምሥራቅ እስያ አገራት እና ሜክሲኮ ገብተውበት ከነበረው የምጣኔ ሃብት ቀውስ እንዲወጡ ትልቅ ሚና ቢጫወትም፣ ድርጅቱ ደሃ አገራት ላይ በተግባር እንዲውሉ ሲገፋፋ የነበሩ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች መሬት ላይ ካለው እውነታ ጋር ያልተጣጣሙ እና የአገራቱን ወቅታዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያላስገቡ ናቸው።

ከዚህ ባሻገር፤ የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ጌታቸው ተክለማርያም አይኤምኤፍ ፋይናንስ ከማቅረብ አኳያ ያለውን የበላይነት በመጠቀም እንደ አየርላንድ፣ ግሪክ እና ቱርክ ያሉ አገራትን ወሳኝ የሆኑ ዘርፎች ለውጭ ባለሃብቶች እና ድርጅቶች ክፍት እንዲያደርጉ ከፍተኛ ግፊት አድርጎ እንደነበር ያወሳሉ። ኢትዮጵያም ቢሆን ተመሳሳይ ችግር ውስጥ ልትገባ እንደምትችል ስጋታቸውን የገለፁት ጌታቸው፣ ይህም የአገሪቷን የፖሊሲ ነፃነት ሊጋፋ እንደሚችል ጠቁመዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ሌላኛው አሳሳቢ ችግር ባለፈው ወር በሰባት ዓመት ተኩል ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከፍተኛ የሆነው የዋጋ ግሽበት ጉዳይ ሲሆን፣ የአገሪቷ ፍላጎት የሚሟላው ከውጭ በሚመጡ እቃዎች ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ ተለዋዋጭ ገበያ-መር የውጭ ምንዛሬ ከተተገበረ ሊያባብሰው እንደሚችል ግልፅ እንደሆነ ጌታቸው ያነሳሉ። ‹‹አገሪቷ ከትልልቅ ማሽነሪ አንስቶ እስከ መሠረታዊ ሸቀጣ ሸቀጦች (ስኳር፣ ዘይት እና ስንዴ) ከውጭ የምታስገባ መሆኑ፣ አሁን ባለው ዋጋ ግሽበት ላይ ቤንዚን እንደ ማርከፍከፍ ነው›› ይላሉ ጌታቸው።

በተመሳሳይ የኦሮሚያ ነፃነት ግንባር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ቀጀላ በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ። በቂ የሚባል የውጭ ምንዛሬ ክምችት በገበያተኞች እጅ ላይም ሆነ ባንኮች እና መንግሥት ጋር እንደሌለ ያወሱት ቀጀላ፣ አገሪቷ በእንደዚህ ዓይነት ችግር ውስጥ ሆና ገበያ-መር የሆነ ተለዋዋጭ የውጭ ምንዛሬ ስርዓት መተግበር ዋጋ ግሽበት ሊያመጣ እንደሚችል ግልፅ ነው ይላሉ። ይህም ዜጎች በአገሪቷ ገንዘብ ላይ ተስፋ እንዲቆርጡ፣ ድህነት እንዲባባስ እና የውጭ ምንዛሬ ፍላጎት የበለጠ እንዲጨምር ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ያነሳሉ።

ጌታቸው የውጭ ምንዛሬ ፖሊሲ ገበያ-መር ከተደረገ ታፍኖ የነበረ ፍላጎት በግልፅ ሊወጣ እንደሚችል ያነሱ ሲሆን፣ ለማይጨበጡ ትንበያዎች እና ለገበያ መዋዠቅ ሊያጋልጥ እንደሚችል ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል፤ የፋይናንስ ባለሙያው አብዱልመናን ይህን ዓይነት የውጭ ምንዛሬ ስርዓት ለውጥ ከተተገበረ ከውጭ የሚገቡ ዕቃዎችን ከማስወደድ እና ዋጋ ግሸበትን ከማባባስ በተጨማሪ የአገሪቷ ብድር ላይ አሉታዊ ጫና ሊያደርግ እንደሚችል አውስተዋል። በተለዋዋጭ የውጭ ምንዛሬ ስርዓት ውስጥ የብር የምንዛሬ ዋጋ መዳከሙ አይቀርም ያሉት አብዱልመናን፣ ይህም የብድር ጫናውን የበለጠ ጠንካራ ሊያደርገው እንደሚችል ተናግረዋል። ስርዓቱ ተገማች ያልሆነ የውጭ ምንዛሬ ተመን ኢትዮጵያ እንዲኖራት ሊያደርግ ይችላል ያሉት አብዱልመናን፣ ይህም ባለሃብቶች በአገሪቷ ላይ ያላቸው መተማመን እንዲወርድ እንዲሁም የኢንቬስትመንት ፍሰትን ሊቀንሰው እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

በተመሳሳይ የምጣኔ ሃብት ባለሙያው እና ተመራማሪው ተኪኤ ዓለሙ (ዶ/ር) የውጭ ምንዛሬ ፖሊሲውን ተለዋዋጭ ለማድረግ ውሳኔ ያሳለፉት የመንግሥት አካላት በዶላር የሚከፈላቸው ካልሆነ በስተቀር የሚያመጣው ውጤት በግልፅ ዋጋ ግሽበት መሆኑ እየታወቀ ተግባራዊ ማድረጉ አገሪቷ ከገባችበት የፖለቲካ ቀውስ ጋር ተዳምሮ የበለጠ አዘቅት ውስጥ ዜጎችን ሊከት እንደሚችል ያስጠነቅቃሉ።

በሌላ በኩል፤ የነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ ዋና ሊቀመንበር ለሆኑት አብዱልቃድር አደም ‹‹መንግስት ገበያ-መር የውጭ ምንዛሬ ስርዓት በሶስት ዓመታት ለመተግበር ማሰቡ ትክክለኛ ውሳኔ ቢሆንም ምርታማነትን ማሳደግ እንዲሁም የአቅርቦት ችግሮችን በቅድሚያ መፈታት እንዳለበት›› ያሳስባሉ። በተመሳሳይ የፋይናንስ ባለሙያ የሆኑት መክብብ ገብረኪዳን ‹‹ወዲያውኑ ባይሆንም ኢትዮጵያ ከገባችበት የኢኮኖሚ ዝቅጠት አንፃር ገበያ-መር የውጭ ምንዛሬ ስርዓት ከመተግበር ውጪ አማራጭ የላትም›› ያሉ ሲሆን ‹‹ይህንን ተከትሎ ግን ሊከሰቱ የሚችሉ ቀውሶች ሊኖሩ እንደሚችል›› ስጋታቸውን ገልፀዋል። በተለይም፤ እንደ መድሃኒት ያሉ ወሳኝ ከውጭ የሚገቡ ዕቃዎች ዋጋቸው ማሻቀቡ አይቀሬ ነው ይላሉ።

ገበያ-መር ተለዋዋጭ የውጭ ምንዛሬ ፖሊሲ ለመተግበር ምን ያስፈልጋል?
የሌሎች የአፍሪካ አገራት ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት ተንሳፋፊም ሆነ ገበያ-መር ተለዋዋጭ የውጭ ምንዛሬ ስርዓቶች ተቀባይነታቸው እየጨመረ መጥቷል። ለምሳሌ፥ እ.ኤ.አ. ከ1995 እስከ 2008 ባለው ጊዜ ውስጥ 35 በመቶ ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገሮች ገበያ-መር ተለዋዋጭ የምንዛሬ ፖሊሲ የነበራቸው ሲሆን፣ በ2008 ዓለም ዐቀፍ የገንዘብ ቀውስ ከተከሰተ በኋላ ግን ይህ እውነታ ተቀይሯል። ነገር ግን ቁጥሩ እያሽቆለቆለ የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ሰዓት ኬኒያን ጨምሮ ከኹለት ደርዘን በላይ አገራት የሆነ የውጭ ምንዛሬ ስርዓት ያላቸው አላቸው። ሌሎች የአፍረካ አገራት ደግሞ ቅይጥ እና መንግሥት-መር የሆነ ቋሚ ስርዓት ተከታይ ናቸው።

በዚህ ረገድ፤ ግብፅ በቅርቡ ገበያ-መር የውጭ ምንዛሬ ስርዓት ከተገበሩ አገራት መካከል ስትሆን ይህም ከአይኤምኤፍ ወደ 12 ቢሊዮን ዶላር የዛሬ ሦስት ዓመት አካባቢ እንድታገኝ ረድቷታል። አገሪቷ ይህንን ካደረገች በኋላ በ70 ዓመታት ውስጥ ትልቁ የዋጋ ግሽበት ተመዝግቦ የነበረ ሲሆን፣ ወደ 36 በመቶ አካባቢ ደርሶ ነበር። ምንም እንኳን ይህ የካፒታል ገበያ ለውጭ ባለሃብቶች ክፍት ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ ግብፅ የውጭ ምንዛሬ ክምችቷን በሦስት ዓመታት ውስጥ በእጥፍ አሳድጋ 45 ቢሊዮን ዶላር እንድታደርስ ምክንያት ቢሆንም፣ የኑሮ ውድነት ጣራ እንዲነካ እና ድህነትም እንዲስፋፋ አድርጓል።

ይሁን እንጂ ለግብፅ ስኬት ዋነኛ ምክንያት ከነበሩት ውስጥ የውጭ ምንዛሬ ክምችት ከፍተኛ የነበረ መሆኑ የመጀመሪያው ሲሆን፣ ኹለተኛው ወደ 22 ቢሊዮን ዶላር የነበረው የወጪ ንግድ ገቢ (ቱሪዝምን ሳይጨምር) እንዳያድግ እንቅፋት የነበሩ ችግሮችን የአገሪቷ መንግሥት በአፋጣኝ ቀደም ብሎ መፍታት መጀመሩ መሆኑን የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ያነሳሉ። ሦስተኛው ምክንያት ደግሞ የውጭ ባለሃብቶች በግብጽ እንዲቆጥቡ የካፒታል አካውንትን ክፍት ማድረጓ ነው። ገበያ-መር የምንዛሬ ስርዓት ከመተግበራቸው በፊት ግብጾቹ የውጭ ምንዛሬ ክምችታቸው ከ16 ቢሊዮን ዶላር ወደ 22 ቢሊዮን ዶላር ከፍ እስኪል ጠብቀው ነበር።

ነገር ግን ኢትዮጵያ ገበያ-መር ተለዋዋጭ የምንዛሬ ፖሊሲ ከተገበረች እንደዚህ ይሳካላታል ብሎ ማሰብ እንደሚከብድ ነው የተለያዩ ባለሙያዎች ትንታኔ የሚያሳየው። ለዚህም ዋነኛ ምክንያቱ በቅድሚያ ሊተገበሩ የሚገባቸው ማሻሻያዎች ስላሉ ሲሆን፣ የመጀመሪያው አገሪቷ ያላትን የውጭ ምንዛሬ ክምችት ማሳደግ ነው። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኢኮኖሚክስ የትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር አጥላው ዓለሙ (ዶ/ር) ገለፃ መሰረት፣ ገበያ-መር የውጭ ምንዛሬ ስርዓት ከመተግበሩ በፊት ገበያ ውስጥ የሚንቀሳቀሰውን የውጭ ምንዛሬ እና የመንግሥትን ክምችት መጨመር ያስፈልጋል።

‹‹ይህን መንግሥት ማድረግ ሳይችል የውጭ ምንዛሬ ስርዓቱን ከለወጠው ከውጭ የሚገቡ ዕቃዎችን ዋጋ ይጨምረዋል፤ የአገር ውስጥ አምራቾችም የጥሬ እቃ ፍላጎታቸውን የሚያሟሉት ከውጭ በማስገባት በመሆኑ ምርታማነታቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይፈጥራል። ይህም የአገሪቷን ተፎካካሪነትም ይበልጥ ያዳክመዋል እንጂ ሊያስተካክለው አይችልም›› ይላሉ።

ጌታቸው በተመሳሳይ፣ መንግሥት ገበያ መሰረት አድርጎ የሚለዋወጥ የውጭ ምንዛሬ ስርዓት ለመተግበር በቅድሚያ የወጪ ንግድ ገቢ መጨመር፣ ሌሎች የውጭ ምንዛሬ ማስገኛ መንገዶችን ማስፋት እና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን መተካት ላይ መሥራት እንደሚገባው ይመክራሉ። ከውጭ ምንዛሬ እጥረት ይልቅ የወጪ ንግድን ከማሳደግ አኳያ ዋነኛ ተግዳሮት የሆኑ መዋቅራዊ ችግሮች መፍታት ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ የሚገልፁት ጌታቸው፣ ያለበለዚያ አንዴ የውጭ ምንዛሬ ስርዓቱ በገበያ መመራት ከጀመረ ሊከሰቱ የሚችሉ ቀውሶችን መፍታት ቀላል አይሆንም ይላሉ።

በተለይም ስርዓቱ በገበያ የሚመራ ከሆነ የብር የምንዛሬ ዋጋ መዋዠቁ ስለማይቀር፣ ይህንን ለማስተካከል በቂ እና ዘላቂ የውጭ ምንዛሬ ፍሰት እና ክምችት ማስፈለጉ አይቀሬ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፤ ይህ ሳይረጋገጥ የፖሊሲው ለውጥ ከተደረገ የውጭ ምንዛሬ ገበያው ከመንግሥት ቁጥጥር ውጭ ሊሆን እንደሚችል ጌታቸው ያስጠነቅቃሉ።
የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አየለ በሌላ በኩል መንግሥት ጥንድ የሆነ የውጭ ምንዛሬ ፖሊሲዎች መተግበር እንዳለበት ይመክራል። ትይዩ የውጪ ምንዛሬ ገበያ ሕጋዊ በማድረግ ኢ-መደብኛው የምንዛሬ ገበያ ከባንኮች ጋር አብሮ እንዲሠራ በማድረግ ኹሉም ተዋናዮች አሸናፊ የሚሆኑበት ስርዓት መፍጠር ይቻላል ይላሉ አየለ። ከኹለት አስርት ዓመታት በላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ተኪኤ በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ። ‹‹የትይዩ ገበያውን ሕጋዊ በማድረግ ፉክክር ያለበት የውጭ ምንዛሬ ገበያ በመፍጠር ፍሰቱን ማስተካከል ይቻላል›› ሲሉም ይመክራሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 60 ታኅሣሥ 18 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here