‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየተደራደርናቸው ነው ያሉዋቸውን ሃይሎች አስመልክቶ የሰጡት ማብራሪያ ግልጽነት የጎደለው ነው›› – ፓርቲዎች

ሰኞ ሐምሌ 29ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎች ጋር መንግሥት ተከታታይ የሆነ ንግግር እያደረገ መሆኑን መናገራቸውን ተከትሎ የተለያዩ አስተያየቶች እየተንጸባረቁ ነው።

አዲስ ማለዳ ይህን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር እንዴት ተመለከታችሁት ስትል ጥያቄ ያቀረበችላቸው የተቀዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ ድርድር መናገራቸው በጎ ቢሆንም አጠቃላይ ሂደቱን በተመለከተ የሰጡት ማብራሪያ ግን ግልጽነት የጎደለው ነው ብለዋል፡፡

የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ የፖለቲካ አቅም ግንባታ ሃላፊ የሆኑት ሙባረክ ረሺድ ከመጀመሪያውም እየተደረጉ ያሉ ድርድሮች ሚስጥር መሆን አልነበረባቸውም ያሉ ሲሆን በአጠቃላይ በሂደቱ ላይ ተአማኒነት ሊፈጥር የሚችል ማብራሪያን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ አላገኘሁም በማለት ገልጸዋል፡፡

ለአብነትም በአማራ ክልል ከፋኖ ሃይሎች ጋር ድርድር እየተከናወነ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል ነገር ግን ከየትኛው የታጣቂ አደረጃጀት ጋር ነው የተነጋገሩት የሚለው ድፍን ያለና ያልጠራ ዋነኛ ጉዳይ ነው ይላሉ፡፡

ይህ በሆነበት ሁኔታ ፖለቲካዊ መፍትሄዎች የሚፈልጉ ጉዳዮች በእንደዚህ አይነት መንገድ ከጅምሩ ያለው ውጤት እንዳይጠናቀቁ መጠንቀቅ ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡

ሌላኛው በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የእናት ፓርቲ አመራሩ አቶ ጌትነት ወርቁ፣ ፖለቲካዊ ድርድሮች የአንድን ወገን ወይም የጥቂቶችን ፍላጎት ብቻ የሚጠቅሙ አለመሆናቸው ሊሰመርበት ይገባል ይላሉ፡፡

በድርድሩ በቀጥታ የሚጠቀመውም ሆነ የሚጎዳው  በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ መሆኑን ከግምት ማስገባት ሊሰመርበት የሚገባው ዋነኛው ጉዳይ መሆኑንም ነው የጠቆሙት ፡፡

ከዚህ አንጻር የፖለቲካ ሃይሎች ለድርድር መቀራረባቸው መልካም ቢሆንም አጠቃላይ የድርድሩ ቅርጽና የሚነሱ ነጥቦችን የመለየት ጉዳይ ዋነኛው የትኩረት ማእከል መሆኑ ሊታወቅ ይገባል በማለት ነው የሚያብራሩት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎች ጋር መንግሥት ተከታታይ የሆነ ንግግር እያደረገ መሆኑን መናገራቸው እንደመልካም ጅማሮ የሚታይ ጉዳይ ቢሆንም አንዱን ጥሎና አንዱን አንጠልጥሎ የሚደረግ የሰላም ውይይት ግን እንደማይሰምር አልተረዱም ይላሉ፡፡

ከታጣቂ ሃይሎች ጋር ለመወያየት ወጥ የሆነ አደረጃጀት አለመኖር ችግር እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ይሁኑ መንግስታቸው ደጋግመው የሚያነሱት ጉዳይ ቢሆንም አሁን እያደረግንው ነው ያሉት ድርድር በምን አግባብ እየተካሄደ ስለመሆኑ ጠለቅ ያለ ማስረጃን አለመስጠታቸው ጉዳዩን በሙሉ ልብ ለማመን ያዳግታልም ብለዋል፡፡

የፌደራል መንግሥቱ ደም አፋሳሹን የትግራይ ጦርነት ለማስቆም ከህወሓት ጋር ድርድር በማድረግ ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ላይ ግጭቱ መቆሙ የሚታወስ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ከሚንቀሳቀሰው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (መንግስት ሸኔ የሚለው) ጋር ታንዛኒያ ውስጥ ለሁለት ጊዜ ንግግር ተካሂዶ ከስምምነት ይደረሳል ተብሎ ሲጠበቅ ያለ ውጤት መጠናቀቁ የሚታወቅ ሲሆን የፋኖ ሃይሎችን በሚመለከት ድርድር እያደረግን ነው በማለት የገለጹት ግን ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here