መንግስት የድርድርና ውይይት ጉዳይን ከፖለቲካ ፍጆታነት በዘለለ መልኩ እየተመለከተው አይደለም ተባለ

👉 በአማራና ኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ሃይሎች መንግስት ሃቀኛ የድርድር መንገድን እየተከተለ አይደለም ብለዋል

ሰኞ ሐምሌ 29ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ)ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሺያን በሚመለከት በቅርቡ በሰጡት ማብራሪያ ላይ በኦሮሚያና አማራ ክልል ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ሃይሎች ጋር መንግስታቸው ድርድር መጀመሩን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
የፌደራሉ መንግሥት በአገሪቱ ሰላም ለማስፈን በአማራ እና ኦሮሚያ ክልል ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎች ጋር ተከታታይ የሆነ ውይይት እያደረገ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአማራ ክልል ከሚገኙ የፋኖ አደረጃጀት ሃይሎች ጋር ተደጋጋሚ ንግግር እየተደረገ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች በርካታ ቡድኖች መሆናቸው እና አንድ አለመሆናቸው የንግግር ጥረቱ ላይ እክል መሆኑንም ደጋግመው ሲጠቅሱ ተደምጠዋል።

ይህን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ተከትሎ ምላሽ የሰጡትና ከፋኖ አደረጃጀት መሪዎች አንዱ የሆኑት አቶ ዘመነ ካሴ ከብልጽግና መንግስት ጋር የተደረገ ምንም አይነት ድርድር የለም ብለዋል፡፡

በጎጃም አካባቢ የሚንቀሳቀሰውን የፋኖ አደረጃጀት እንደሚመሩ የሚነገርላቸው ዘመነ መነጋገርና ለድርድር መቅረብ መልካም የፖለቲካ ባህል ቢሆንም ለዚህ የሚሆን ምቹ ሁኔታ አሁን ላይ በመንግስት በኩል ስለሌለ ለድርድር አልተቀመጥንም ሲሉ በተንቀሳቃሽ ምስል በስተላለፉት መልዕክት ጠቁመዋል፡፡

እሳቸው የሚመሩት የፋኖ አደረጃጀት ከየትኛውም የመንግስት አካል የእንደራደር ጥያቄ እንዳልቀረበለት የገለጹት የፋኖ መሪው በአማራ ክልል በተመሰረተው የሰላም ካውንስልም ሆነ በምክክር ኮሚሽኑ ሙሉ እምነት እንደሌላቸውና የአማራ ህዝብ ችግርም በእነዚህ ተቋማት ይፈታል ብለው እንደማያምኑ አክለዋል፡፡

በተመሳሳይ የድርድር ሃሳብ ቀርቦለታል የተባለው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (መንግስት ሸኔ ብሎ የሚጠራው) ታጣቂ ሃይል አዛዥ የሆኑት ኩምሳ ድሪባ (ጃል መሮ) የኦሮሞን ህዝብ ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ ለሚደረጉ ድርድሮችም ሆነ ውይይቶች እኛ ዝግጁ ነን ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

ይሁን እንጂ መንግስት ሃቀኛ የመነጋገሪያ መንገዶችን ከመፈለግ ይልቅ የድርድር ጉዳይን ለፖለቲካ ፍጆታነት እየተጠቀመበት ነው ሲሉም ከሰዋል፡፡

እስካሁን ከታጣቂ ሃይሉ ጋር የተደረጉ ድርድሮች ውጤት ያላስመዘገቡት መንግስት በሰጥቶ መቀበል መርህ ስለማያምን ነው ያሉት ጃል መሮ አሁንም ለሰላም የሚከፈሉ ዋጋዎችን ለመክፈል በእኛ በኩል ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here