አርብ ነሐሴ 10 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በአርሲ ሀገረ ስብከት፣ በአሰኮ ወረዳ በጢዮ ቀበሌ ጠለታ ጨፋ ከተማ ” የጠለታ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ” አገልጋይ ካህንን ጨምሮ 6 ምዕመና በታጣቂዎች መገደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎችን ዋቢ በማድረግ ማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ዘግቧል።
ካህኑ ሥጋ ወደሙን አቀብለው ምእመናንን እያሳለሙ በነበረበት ሰዓት እንደተገደሉ የገለጸው ዘገባው 3 ምዕመናን ደግሞ ከባድ ጥቃት ደርሶባቸው በህክምና ላይ እንደሚገኙ ገልጿል።
ነዋሪዎቹ ድርጊቱን የፈጸሙት ” ኦነግ ሸኔ ” ተብለው የሚጠሩ ታጣቂዎች ናቸው ያሉ ሲሆን ግድያው የተፈጸመው ከነሐሴ 7 ቀን 2016 ዓ/ም ጀምሮ እንደሆነ ነዋሪዎቹ አመልክተዋል።
ከዚህ ባለፈም ፥ በተለያየ መንገድ ቤተ ክርስቲያኗን ሲረዱ የነበሩ ምዕመናን ተለይተው ሀብት እና ንብረታቸው መቃጠሉንና የአካባቢው ምእመናን ቤታቸውን ትተው በዱር በስጋት ውስጥ እንደሆኑ ተጠቁሟል።
ጥቃቱ ከዚህ ቀደምም ተፈጥሮ እንደነበር አንስተው ” ለበላይ አካል ብናሳውቅም ጩኸታችንን የሚሰማ አጥተናል ” በማለት ጥሪ ማቅረባቸውን የተገኘው መረጃ ያሳያል።



