👉 ” ለቡድናዊ ጥቅም ሲባል በህዝብ ቁማር መጫወት መቆም አለበት ” ሶስቱ ፓርቲዎች
ዓርብ ነሐሴ 10 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በትግራይ የሚንቀሳቀሱት ባይቶና፣ ሳወት እና ናፅነት የፓለቲካ ፓርቲዎች በጋራ በሰጡት መግለጫ ፤ ” በህወሓት አመራሮች መካከል የተፈጠረው ህገ-ወጥ እንቃስቃሴና ፍጥጫ ተው መባል ይገባዋል ” ብለዋል።
በህወሓት አመራሮች የተፈጠረው ውጥረትን ተከትሎ በህዝቡ የሚታየውን መረበሽ ያወገዙት ሦስቱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ” ህግ እየጣሱ በህዝብ ካባ ስም ለመደበቅ የሚደረገውን እንቅስቃሴ እናወግዛለን ” ሲሉ ገልጸዋል።
” ለቡድናዊ ጥቅም ሲባል በህዝብ ቁማር መጫወት መቆም አለበት ” ያሉት ፓርቲዎቹ ደርጅታዊ ይሁን ቡድናዊ ጉዳይ ከህዝብ ህልውና ጋር ማገናኘትን እንፀየፈዋለን እንዲቆምም እናሳስባለን ነው ያሉት።
ፓርቲዎቹ መሰል የህዝብ ሰላም፣ ህልውናና ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ፣ ህገ-ወጥ ፓለቲካዊ ተግባር ሲታይ የሚመለከተው የፀጥታ አካልና ህዝብ ፍትሀዊ በሆነ መንገድ በአስቸኳይ የማስቆም ሃላፍነቱን መወጣት አለበት ብለዋል።
ፓርቲዎቹ አክለውም የተፈጠረው ፓለቲካዊ አለመረጋጋት ዋነኛ መፍትሄው ሁሉም የፓለቲካ ሃይሎች በእኩልነት የሚሳተፉበት መንግስት በአስቸኳይ መመስረት ነው ስለማለታቸው አዲስ ማለዳ ከፓርቲዎቹ የጋራ መግለጫ ተመልክታለች።



