የሸገር ከተማ አስተዳደርን ከአዲስ አበባ ከተማ ለማገናኘት ያለመ ቀጣይ የኮሊደር ልማት እቅድ መውጣቱ ተሰማ

0
1957

ረቡዕ ነሐሴ 15 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕላን እና ልማት ቢሮ በሁለተኛ የኮሪደር ልማት እቅዱ ላይ የሸገር ከተማን ከአዲስ አበባ ከተማ ለማገናኘት የተያዘ እቅድ ስለመኖሩ አዲስ ማለዳ ከደረሳት ሰነድ ተመልክታለች፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በምዕራፍ ሁለት የሚከናወኑ የኮሪደር ልማት ሥራዎችን በከተማዋ የፕላን እና ልማት ቢሮ አማካኝነት ጥናት አካሂዶ ማጠናቀቁን ገልጿል፡፡

በመሆኑም በአጠቃላይ 43 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚኖረው የምዕራፍ ሁለት የኮሪደር ልማት፣ ቦሌ፣ ለሚ ኩራ እና አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተሞችን እንደሚያካትት በጥናት ሰነዱ ላይ ተመላክቷል፡፡

በምዕራፍ ሁለት የኮሪደር ልማት ስራ ላይ ከሸገር ከተማ ጋር የሚዋሰኑ ኮሪደሮችን ወጥ የሆነ ዲዛይን ተዘጋጅቶላቸው በጋራ የሚለሙበትን ማዕቀፍ መፍጠር እንዲሁም ቦሌ ካርጎ ቦሌ ሚካኤል እስከ ቦሌ ድልድይ፣ከሰሚት ለስላሳ ፋብሪካ እስከ ደራርቱ አደባባይ ድረስ የሚያገናኙ መንገዶች ዝርጋታ ከተጀመሩ ስራዎች ጋር የማቀናጀት ስራ እንደሚሰራ ተጠቁሟል፡፡

በአምስት መስመሮች ላይ የኮሪደር ልማቱ እንደሚከናወን የሚገልጸው ሰነድ ከእነዚህ መስመሮች ውስጥ ከፍተኛ ዝርመት ያለው “ከአንበሳ ጋራዥ እስከ መብራት ኃይል ፣ከጎሮ እስከ ኮዬ አደባባይ” የሚደርሰው መንገድ ሲሆን ይህ መስመር 14ነጥብ8 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን መሆኑ አስቀምጧል።

በመጀመሪያው የኮሪደር ልማት ምዕራፍ ላይ የከተማ አስተዳደሩ፤ በድምሩ 48 ኪሎ ሜትር ለሚሸፍነው የመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት 33 ቢሊዮን ብር ወጪ አድርጎ ነበር፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር “የኮሪደር ልማት” ሲል የጠራውን ዋና ዋና መንገዶችን የማስዋብ፣ የእግረኛ መንገድን የማስፋት፣ መዝናኛ ቦታዎችን የመገንባት እንዲሁም የመንገድ ዳር መብራት እና ቴሌኮሚዩኒኬሽን መስመሮችን በዘመናዊ መንገድ የመዘርጋት ሥራ የጀመረው በያዝነው አመት የካቲት ወር ላይ እንደነበር ይታወሳል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here