የውጭ ምንዛሬ መዋጮ – ቀጣዩ የባንኪንግ ዘርፍ ገዳይ

0
961

አካባቢያዊ እንቅስቃሴዎች የግለሰብ አእምሮ ይወስኑታል፤ ይህ የሆነው ሁላችንም ከተፈጥሯችን በተጨማሪ የአካባቢያችን ውጤቶች ስለሆንን ነው። ይህም አእምሮ የተዘራበትን እንደሚያበቅል ያሳያል የሚሉት መላኩ አዳል፤ ውስብስቡን የአንጎል፣ የአእምሮና የሕዋሳትን አሠራር ከውጫዊና አካባቢያዊ ተጽእኖ አንጻር ቃኝተውታል። እናም የሐሰት ትርክት እየነገሩ ይህን ተፈጥሮ ላልሆነ ተግባር የሚያውሉ በሕግ የሚጠየቁበት ማዕቀፍ ያስፈልጋል ሲሉ ይሞግታሉ። ሐይማኖትም ሥነ ምግባር ከማነጽ ጀምሮ የተለያዩ በጎ ጎኖች ያሉት ቢሆንም፤ ሰው ጠያቂና ምክንያታዊ እንዲሆን ለማስቻል ሊያካትቷቸው የሚገቡ ጉዳዮች አሉ ሲሉ ያጨምራሉ።

የውጭ ምንዛሬ መዋጮ ባንኮችን እንዲሁም አገሪቱን ችግር ላይ እየጣለ ይገኛል የሚሉት አብ ጌታሁን፣ በዚህ ጽሑፍ ብሔራዊ ባንክ ለጉዳቱ የሰጠው ትኩረት እምብዛም ነው፤ መዋጮው እያመጣና ሊያመጣ የሚችለውን ጣጣ ባንኩ በውሉ እንዳልተረዳውም ሲሉ ይሞግታሉ። የምንዛሬ መዋጮ መመሪያም ያስከትላል ያሉትንም ችግር በዝርዝር ያስቀመጡ ሲሆን፣ ብሔራዊ ባንክ መዋጮ አምጣ አታምጣ ፍልሚያ ውስጥ ከመግባት የአገሪቱ ውጭ ምንዛሬ የሚሰፋበትን አሠራር መቃኘቱ ያዋጣዋል ሲሉ ሐሳባቸውን ያካፍላሉ።
መግቢያ
ከኢኮኖሚ ተኮር ተልዕኮዎች በተጨማሪ የፋይናንስ በተለይም ደግሞ የባንኮችን ደኅንነት የማረጋገጥ ጥልቅ ኃላፊነት በብሔራዊ ባንክ ላይ መውደቁ ይታወቃል። ባንኩ፣ በባንኪንግ ኢንዱስትሪው የግሉ ዘርፍ መሳተፍ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የጎላ ድርሻ እያበረከተ ቢመጣም፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚወጡት የፖሊሲ አቅጣጫዎችና መመሪያዎች የባንክ ኢንዱስትሪው ሊጓዝ የሚገባውን መስመር የተከተለ ነው ለማለት አያስደፍርም። ብዙ የባንክ ባለሙያዎች የሚስማሙበት ነገርም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየወጡ ያሉ መመሪያዎች አፋኝና ለሴክተሩ ዕድገት እንቅፋት መሆናቸውን ሲሆን፣ የችግሩ ክብደት እያነጋገረ ይገኛል።
ለምሳሌ የብሔራዊ ባንክ የህዳሴ ቦንድ ግዢ ለብዙ ዓመታት ባንኮች ላይ የተጣለ ዱብ ዕዳ እንደነበርና የባንኮቹ የመክፈል አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ ፈተና ሲገጥመው በመመሪያው መነሳቱ የሚታወስ ነው። ጥሩነቱ መመሪያው የባንክ ኢንዱስትሪው ሊደርስበት የሚችለውን ያህል እንዳይጓዝ ቢያደርገውም የባንኮች ህልውና ላይ የነበረው ተፅዕኖ ከባድ የሚባል አልነበረም። የዚህ ጽሑፍ ዓላማ የህዳሴ ቦንድ ግዢ ባንኮች ላይ የነበረውን ተፅዕኖ የመተንተን ሳይሆን ከቦንድ በላይ የባንኮችን እንዲሁም አገሪቱን ችግር ላይ እየጣለ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ መዋጮ (ሰረንደር) በተመለከተ ይሆናል።
ስለመመሪያው ምንነት
መመሪያው አገሪቱ ካጋጠማት የውጭ ምንዛሬ እጥረት ጋር ተያይዞ የወጣ ሲሆን ባንኮች ከሚያገኙት ማንኛውም አይነት የውጭ ምንዛሬ 30 በመቶ ያህሉን ለብሔራዊ ባንክ እንዲያስገቡ የሚያስገድድ ነው። መመሪያው ሁሉንም የውጭ ምንዛሬ ግኝቶች (ከብሔራዊ ባንክ የሚገዛውን ጨምሮ) በስሌቱ ውስጥ ከማካተቱም በላይ ብሔራዊ ባንክ ለባንኮች ታሳቢ የሚያደርግበት የምንዛሬ መጠን በግዢ ዋጋ (buying rate) ላይ የተንተራሰ ነበር። እያደር ባንኮች ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት የአማካይ ዋጋ (mid rate) እንደሚከፈል የተሻሻለ ቢሆንም፣ በየጊዜው ባንኮች የሚያቀርቡትን የይነሳልን ጥያቄ ችላ ያለ ነበር።
የመመሪያው ዓላማ
የመመሪያው ዓላማም መንግሥት ከውጭ የሚያስገባቸውን የነዳጅ፣ የማዳበሪያና መድኀኒት የመሳሰሉትን መደጎም ላይ ያጠነጠነ ሲሆን፣ ለአፈፃፀሙም ጠንከር ያለ መቀጮና ማስፈራሪያ ያዘለ አንቀፆችን ያካተተ ነው። ለምሳሌ ማንኛውም ባንክ ወሩ በገባ በአምስት ቀናት ውስጥ በወሩ ያገኘውን የውጭ ምንዛሬ የብሔራዊ ባንክ ቋት ውስጥ ካላስገባ በቀን 10 ሺሕ ዶላር እንደሚቀጣ ይደነግጋል።
የመመሪያው ዓላማ ምንም ይሁን ምን፣ በባንኮች ያለው ይሁንታና የተቀባይነት ደረጃ ዝቅ ያለ ከመሆኑም ባሻገር ባንኮች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አግባብ አለመሆኑን ሲያነሱ ግን ሳይደመጡ የታየበት ነው። ችግሩ የባንኮቹ ጥያቄ ማቅረብና ሰሚ ማጣት ሳይሆን፣ ችግሩ ያለው መመሪያው እያመጣ ያለው እንዲሁም ሊያመጣ የሚችለው ችግር አለማስተዋሉ ነው። የሚገርመው የችግሩ መገለጫዎች አሁንም በባንኪንግ ሴክተሩ ውስጥ በግልፅ የሚታዩ ቢሆኑም ጆሮ ዳባ ልበስ መባሉ ነገ የፋይናንስ ሴክተሩንና የአገር ኢኮኖሚን ላይነሳ ሊያደቅ እንደሚችል አለመጤኑ ነው።
መመሪያው እያመጣቸው ያሉ ችግሮች
የመመሪያው ዓላማ ቅዱስም ይሁን እርኩስ፣ በጊዜ ሂደት እየፈጠራቸው የሚገኙ ችግሮች እጅግ አስከፊ ደረጃ ላይ መሆናቸው በጣም አሳሳቢ ነው። ጥቂቱን ለመግለፅ፡

  1. የባንኮችን የውጭ ምንዛሬ ሀብትና ዕዳ ልዩነት (open position) እያሰፋ እየሄደ ነው
    ባንኮች የሚያገኙትን የውጭ ምንዛሬ እንደ ሀብት የማይዙት ሲሆን ከዚህ ሀብት ውስጥ የተወሰነውን የውጭ ምንዛሬ ለደንበኞቻቸው ሲደለድሉት ቀሪውን ለክፍያ የሚያቆዩት ነው። አሁን ካለው የውጭ ምንዛሬ ዕጥረት አንፃር የብዙ ባንኮች የውጭ ምንዛሬ ሀብትና ዕዳ ልዩነት ቅናሽ (negative) ላይ ያለ ሲሆን፣ ይህን አሳሳቢ የሚያደርገው ልዩነቱ እየሰፋና ብሔራዊ ባንክ ካስቀመጠው የ15 በመቶ ወሰን ርቆ መገኘቱ ነው። ይህም ማለት ባንኮች ካላችው የውጪ ምንዛሬ ሀብት በላይ ነገን ብቻ በማሰብ ከአቅም በላይ የደለደሉት መሆኑን ነው።
    ይህ የ15 በመቶ ወሰን በብሔራዊ ባንክ ብቻ የተቀመጠ መለኪያ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ይዘት ያለው ነው። ከዚህ ወሰን በላይ የውጭ ምንዛሬ ሀብትና ዕዳ ልዩነት ያለው ባንክ፣ በውጭ ምንዛሬ ዋጋ ለውጥ ምክንያት ሊጠቃ ወይም ጨርሶ ሊጠፋ እንደሚችል በዓለም ላይ ያለው ተሞክሮ ያሳያል። ይህንን ለመከላከል የተለያዩ ማስታገሻዎች (hedging) መውሰድ የግድ ቢልም፣ በኢትዮጵያ ሁኔታ የገንዘብ ገበያው ባለመዳበሩ ምክንያት ጨርሶ የሚታሰቡ አይደሉም። ስለዚህ ተጋላጭነቱ ሙሉ በሙሉ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።
    የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በስፋት እንደታዘበው የብዙ ባንኮች የውጭ ምንዛሬ ዕዳና ሀብት ልዩነት ካላቸው ካፒታል ጋር ያለው ጥምረት ከ40 በመቶ (ከሚጠበቀው ሦስት እጥፍ) በላይ እንደሚገኝ ነው። ይህም የሚያሳየው የባንኮች የውጭ ምንዛሬ ዕዳ ከሀብታቸው በላይ እየሄደና ከውጭ ምንዛሬ ዋጋ ልዩነት ጋር ተያይዞ ከሚመጣው ኪሳራ እንዲሁም ያለባቸውን ዕዳ የመክፈል አቅም እየተዳከመ መምጣቱን ነው።
  2. ለግል ዘርፉ (private sector) የሚከፋፈለውን የውጭ ምንዛሬ እንዲቀንስና ዕጥረት እንዲፈጠር /እንዲባባስ ጉልህ ድርሻ እያደረገ ነው፣
    የመመሪያው ተግባራዊነት ተፈፃሚ የተደረገው የግል ባንኮች ላይ ብቻ ከመሆኑ አንፃር ቀድሞውንም በችግርና በወረፋ ሲስተናገድ የነበረው የግል ዘርፍ የባሰ በውጭ ምንዛሬ እጥረት እንዲሰቃይ እያደረገ መሆኑ አሳሳቢ ነው። ችግሩን የሚያጎላው የእጥረቱ ሁኔታ ብቻ ሳይሆን የወረፋ መብዛት፣ ከዚህ ጋር ተያይዞም የውጭ ምንዛሬው የሚታደልባቸው ዘርፎች መለያየት በብዙ የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ እየተስተዋለ ነው።
    ለምሳሌ ባንኮች የሚያገኙትን የውጭ ምንዛሬ 30 በመቶ ለብሔራዊ ባንክ፣ ወደ 5 በመቶ ለኢትዮጵያ መርከብ ድርጅት እንዲሁም ቀሪውን 30 በመቶ ለኤክስፖርት ሪቴንሽን ሂሳብ ውስጥ ካስገቡ በኋላ፣ ለግል ዘርፉ ሊያከፋፍሉ የሚችሉት 35 በመቶውን የውጭ ምንዛሬ ብቻ ነው። ጉዳቱ በዚህም አያበቃም፤ ከ35 በመቶ ውስጥ 50 በመቶ ለተመረጡ ሴክተሮች (ማኑፋክቸሪንግ የመሳሰሉት) መስጠት ሲገባው ቀሪው 50 በመቶ ብቻ ለሌላ የሚውል ነው።
    የእጥረቱን ልክ ያየው ብሔራዊ ባንክ፣ መመሪያውን ከሚያስተካክል ይልቅ ባንኮች ወረፋውን የሚቀንሱበት ስልት ላይ ነው የተጨነቀው። ለምሳሌ በአንድ ጊዜ አንድ ነጋዴ ማስመዝገብ የሚችለው ኹለት የኢምፖርት ማመልከቻ ብቻ እንደሆነ በቅርቡ ደንግጓል። ይህም የውጭ ምንዛሬ እጥረቱን የሚቀንስ ሳይሆን፣ ወረፋን የማስተካከል ዓላማ ሲኖረው፣ በእጥረቱ ምክንያት የሚፈጠርን አዲስ ወረፋ ማስቀረቱ አጠራጣሪ ነው።
  3. ባንኮች በጊዜ መክፈል የሚገባቸውን ዕዳ መከፈል የማይችሉበት ደረጃ ላይ እየደረሱ ነው፣ ይሄም ነገ የአገር ዕዳ የሚሆን ነው፣
    በባንክ የውጭ ምንዛሬ አደላደል አዐራር መሠረት ትልቁ ሙያ የውጭ ምንዛሬ መደልደል ሳይሆን፣ በድልድሉ ምክንያት የሚመጣውን ዕዳ በጊዜው መክፈል መቻል ነው። ይህም ማለት አንድ ነጋዴ ከውጭ ያስመጣው ዕቃ አገር ከገባ በኋላ ክፍያ በጊዜው ሊፈፀምለት ይገባል። የብሔራዊ ባንክ ሕግ የኢምፖርት ዶክመንት በመጣ በሦስት ቀን ጊዜ ውስጥ መከፈል ይገባል ቢልም፣ ባንኮች ከ6 ወር በላይ ሳይከፍሉ ያስቀመጡት የውጭ ምንዛሬ ዕዳ እንዳለባቸው ጉልህ ሀቅ ነው።
    የሚገርመው የመንግሥት ባንክ የሆነው የንግድ ባንክ እንኳ ከዓመት በላይ ያልከፈላቸው ዕዳዎች በመዝገቡ ላይ የሚገኙ መሆኑ ነው። በግል ባንኮች ጉዳቱ ምን ያህል ገዝፎ እንደሚገኝ መገመት አይከብድም። በተለይም በ‹ሌተር ኦፍ ክሬዲት› የገቡ ዕቃዎች ክፍያ በዓለም ሕጎች መሰረት በጊዜ መክፈል መቻል ቢገባቸውም አለመደረጉ፣ ብዙ የውጭ ነጋዴዎች ከአገራችን ነጋዴዎች ጋር የመሥራት ፍላጎት እየቀነሰም እየመጣ ነው። በተጨማሪም የዚህ ዕዳ መከማቸት ነገ የባንኮችን የመክፈል አቅም መፈታተን ብቻ ሳይሆን አለመቻል ማምጣቱ የማይቀር ሲሆን፣ ይህም የአገሪቱ ዕዳ ሆኖ የሚቀጥል ነው። በጊዜ የመፍትሔ እርምጃ ካልተወሰደ ጉዳቱ በጣም በጣም አሳሳቢ ነው።
  4. የጥቁር ገበያው የውጭ ምንዛሬ ዋጋ መጠን እንዲጨምር አስተዋፅኦ እያደረገ ነው፣
    በአሁኑ ወቅት በባንክና በጥቁር ገበያ መካከል ያለው የውጭ ምንዛሬ ዋጋ ልዩነት እየሰፋ መምጣቱ ይታወቃል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት የዋጋ ልዩነቱ እስከ 10 ብር ድረስ በዶላር የደረሰ ሲሆን የብሔራዊ ባንክ ልዩነቱን ለማጥበብ የብር ዋጋን በየጊዜው እንዲያሽቆለቁል እያረገ ነው። በተለይ በቅርቡ እየሰወደ ያለው የብር ዋጋ ባልተለመደ ሁኔታና መጠን እንዲያንስ የማድረጉ ሂደት የራሱ ውጤት ቢኖረውም፣ በኹለቱ ገበያዎች መካከል ያለውን ልዩነት ሊያጠብ ግን አይችልም። ምክንያቱም ችግሩ ያለው ከውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ችግር እንጂ ከዋጋ ልዩነቱ ባለመሆኑ ነው።
    ከላይ እንደተገለፀው የብሔራዊ ባንክ መምሪያ በግልፅ ለግሉ ሴክተር የሚከፋፈለውን የውጭ ምንዛሬ ለሌላ ዓላማ በመዋሉ እጥረቱ የሚቀጥል ሲሆን፣ ምንም ዓይነት የዋጋ ማሻሻያ በባንክ ሴክተር ላይ ቢደረግ እጥረቱ እስካልተፈታ ድረስ የጥቁር ገበያ የውጭ ምንዛሬ ዋጋ ማደጉ የማይቀር ነው። ይህም ለግሉ ዘርፍ የሚውለውን የውጭ ምንዛሬ በባንኮች ሳይሆን ወደ ጥቁር ገበያ እንዲገባ እያደረገ የሚሔድ በመሆኑ፣ የችግሩን ጥልፍልፎሽ የከፋ ያደርገዋል።
  5. የባንኮች የማበደር ዋጋ (ወለድ) ና የኢምፖርት ኮሚሽን እንዲጨምር አስተዋፅኦ ማድረጉ
    [ይህም የዋጋ ግሽበቱ ዋነኛ መንስኤ ነው] የመመሪያው አንዱ ይዘት ባንኮች ከሚያመጡት የውጭ ምንዛሬ 30 በመቶውን በገዙበት ዋጋ (የመግዣ በኋላም አማካይ ዋጋ) ለብሔራዊ ባንክ እንዲያስረክቡ የሚያስገድድ ነው። ይህም ባንኮች የውጭ ምንዛሬን ለማግኘት ያወጡትን ወጪ ከግምት ውስጥ ያላስገባ ነው። ለምሳሌ አንድ ባንክ ከኤክስፖርት ዘርፍ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ለኤክስፖርተሩ በቅናሽ ወለድ ማበደር ይጠበቅበታል።
    ነገር ግን ከኤክስፖርተሩ የሚገኘውን ውጭ ምንዛሬ 30 በመቶ ብሔራዊ ባንክ በገዛበት ዋጋ እንዲያቀርብ ሲያስገድድ፣ የኪሳራው መጠን መስፋቱ ግልፅ ነው። ይህንን ለመሸፈን ባንኮች የሚወስዱት እርምጃ ኹለት ነው፣ አንደኛ ለሌሎች ዘርፎች የሚበድሩበትን የብድር ወለድ መጨመር ወይም፣ ኹለተኛ አስመጪዎች ላይ የኮሚሽን ክፍያ መጨመር። የእነዚህ ኹለቱ አስተዋፅኦ ዛሬ ብሔራዊ ባንክ ራሱ ሊቆጣጠረው ያልቻለውን የዋጋ ግሽበት የሚያስከትል ወይም የሚያባብስ ነው።
  6. ባንኮች ከውጭ ምንዛሬ ጋር የተገናኙ ሪፖርቶችን እንዲደብቁና በግልጽ እንዲያቀርቡ የገፋፋ ነው፣
    ከላይ እንደተገለጸው የባንኮች የውጭ ምንዛሬ ሀብትና ዕዳ መጠን ከመስፋት ጋር በተገናኘ ለብሔራዊ ባንክ የሚቀርቡ ሪፖርቶች የሚያካትቱ ባንኮች የብሔራዊ ባንክ ወሰንን አክብረው እንደሚሠሩ ቢሆንም፣ ውስጡን ለቄስ እንደሚባል ነው። አንድም የብሔራዊ ባንክ ካለው ባንኮችን የማገዝ ሳይሆን የመቅጣት አባዜ የተነሳ ባንኮች ሪፖርታቸውን በግልፅ ቢያስቀምጡ የሚደርስባቸውን ቅጣት በመፍራት ሲሆን ሌላው ደግሞ ነገሮች ከአቅማቸውና ከቁጥጥራቸው በላይ ስለሔዱም ጭምር ነው። ለዚህም ዋነኛው ተዋናይ ብሔራዊ ባንክ ራሱ መሆኑ አሳዛኝ ከመሆኑም በላይ፣ ከባንኮች ጋር ያለው የድብብቆሽ ጨዋታ ነገ አገራዊ ችግር ሊፈጥር መቻሉ አሳሳቢ ነው።
  7. ከውጭ ምንዛሬ ዋጋ ልዩነት ጋር የሚመጣን ኪሳራ እየጨመረ ይገኛል
    ከውጭ ምንዛሬ እጥረት ጋር የሚመጡ ጉዳቶች ዘርፈ ብዙ ናቸው። ከላይ የተገለጹት ችግሮች የከፋ ገፅታዎች ቢሆኑም፣ በቁጥር ተለክቶ ሊቀመጥ የሚችለው የውጭ ምንዛሬ ሁኔታ ጋር ተገናኝቶ የሚከሰተው ኪሳራ ነው። አሁን ያለው የባንኮች ዕዳ ከሀብታቸው መብለጥ፣ ብሔራዊ ባንክ አሁን እየተደረገ ካለው ብርን የማውረድ አካሄድ አንፃር ሲታይ፣ ባንኮችን ወደ ኪሳራ የሚዳርግ ነው። በተለይ ባንኮች ለብሔራዊ ባንክ የሚደጉሙት የውጭ ምንዛሬ እንደ ሀብት የማይቆጠር ከመሆኑ አንፃር፣ የባንኩን የውጭ ምንዛሬ ሁኔታ (currency position) የሚያናጋ በመሆኑ ወደ ኪሳራ መውሰዱ የማያጠራጥር ነው።
    ከላይ ከተጠቀሱት ችግሮች ውጭ ብዙ መተንተን ቢቻልም ዋነኛው ነገር የውጭ ምንዛሬ አሰራር ላይ የሚወጡ መመሪያዎች እንደ አገር ውስጥ አገልግሎት ዘርፍ ላይ አንደሚወጡት አይደሉም። ምክንያቱም የውጭ ምንዛሬ ጋር የተገናኙ ጉዳዮች ድንበር ተሻጋሪ ከመሆናቸው አንፃር ችግሮች ሲፈጠሩ በቀላሉ ለመመለስ አስቸጋሪ ናቸው። የሴክተሩን ብሎም የአገርን ገፅታ ከማበላሸታቸው ባሻገር፣ ሊያደርሱ የሚችሉት የፋይናንስ ጉዳትም ቀላል አይሆንም። አንዳንድ የባንክ ባለሙያዎች ችግሩን ቀድሞ በመረዳት ጥያቄያቸውን ቢያቀርቡም፣ ሰሚ በማጣታቸው ብሔራዊ ባንክና መንግሥት የባንኪንግ ሴክተሩ ውስጥ ለሚከሰቱ ችግሮች ሙሉ ኃላፊነት ሊወስድ ይገባል።
    እየሰለቸ የመጣውን ባንኮችን በውሃ ቀጠነ ሰበብ የመቅጣት፣ ጥያቄያችሁን ለምን አቀረባችሁ ትችቶች ቀርተው አገርን ሊጎዱ የሚችሉ ድርጊቶች በተለይ ከባንክ ባለሙያዎች ሲነሳ ማዳመጥና ማስተካከል ግድ ይላል። በወጣው ይውጣው ብሎ ችግሮቹን ለባንኮች አመራር ላይ መጫን፣ ችግር ሲመጣም እነሱን ለመቅጣት መሯሯጡ መቅረት ይገባዋል። በዚህ ጉዳይ በጭንቀት እየኖሩ ላሉ የባንክ ባለሙያዎችም ሊታሰብበት ይገባል።
    ብሔራዊ ባንክ እጁን ሰብስቦ አምጣ አታምጣ ፍልሚያ ውስጥ ከመግባት የአገሪቱ ውጭ ምንዛሬ የሚሰፋበትን አሠራር መቃኘቱ አዋጭ ነው። ስለዚህ ብሔራዊ ባንክ ከባንኮች የሚወስደውን የውጭ ምንዛሬ ጊዜ ሳይወስድ ማቆም ይገባዋል። ማቆምም ብቻ ሳይሆን ባንኮቹም እስከ አሁን ላከማቹት ዕዳ የሚውል የውጭ ምንዛሬ ማከፋፈል አስፈላጊ ነው። ክፍፍሉም ባንኮች ባላቸው ወረፋ መጠን ሳይሆን ባላቸው የዕዳ ክምችት መጠን ታይቶ መከፋፈል ይገባዋል። መንግሥት ባንኮቹን ሊታደጋቸው የሚገባበት ሰዓት አሁን ነው። በቆየ ቁጥር አገርም ሴክተሩም ጥልፍልፎሽ ውስጥ መውደቃቸው አይቀሬ ነው። ወደፊትም ብሔራዊ ባንክን እንደ አዲስ ማዋቀርና በሙያው ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች ማጠናከር ሳይረሳ ማለት ነው።

አብ ጌታሁን፤ በባንኩ ዘርፍ የበርካታ ዓመታት ልምድ ያላቸው ባለሙያ ሲሆኑ በኢ-ሜይል አድርሻቸው abgetahun@yahoo.com ላይ ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 61 ታኅሣሥ 25 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here