‹‹ዋናው አገር ሰላም!›› በገና ገበያ

0
907

ሾላ ገበያ የለመደው የበዓል ሰሞን ግርግር የቀረበት ይመስላል። ድምጽን አጉልተው የሚያሰሙ የሙዚቃ ማጫወቻዎች ግን ከዓለማዊ ዘፈኑም ከመንፈሳዊ መዝሙሩም ቀላቅለው ከወዲያና ከወዲህ የበዓሉን ድባብ ሊጠሩ የሚታገሉ ይመስላሉ። እንዳልተሳካላቸው አይቶ መገመት ይቻላል። ጭር ካሉት ሱቆች መካከል አዲስ ማለዳ ወደ አንዱ አቀናች።

ዓለም ከ10 ዓመት በላይ ሾላ ገበያ ውስጥ ቅቤና ቆጮ በማቅረብ የሚታወቁ ብርቱና ታታሪ ሴት ናቸው። ታድያ የገበያውን መቀዛቀዝ የሚገልጹበት ቃላት አጥተው፤ ‹‹ምንም››ን በተለየ ቅላጼ ደጋግመው እየጠቀሱ ነበር የገበያውን ሁኔታ ሊያስረዱ የሞከሩት።

‹‹ምንም ገበያ የለም፤ ጭር ብሏል፤ ምንም ሥራ የለም፤ እንደበፊቱ አይደለም…ምንም ነገር የለም›› አሉ። ቂቤ ከሸኖ እንዲሁም ከሰንዳፋ እና ገበያ ካለበት ንጹህ ያሉትን ዓመታት ለሚያውቋቸው ደንበኞቻቸው ቢያመጡም፤ ደንበኞቻቸው ግን እግራቸውን ቀንሰዋል። ዓለምም ለዓመታት የሚውቁት ከበዓል ሳምንት ጀምሮ የሚሞቀው የደራው የበዓል ገበያ መቀዛቀዝ ከጀመረ ሦስት ዓመት ቢጠጋውም፣ እየባሰ መሔዱ እንግዳ እንደሆነባቸው ያስታውቃሉ።

‹‹ያልተወደደ ነገር የለም፤ ገበያ ላይ የሚያስደስት የለም። ብራችን ስለወረደ ከገበያው ጋር አይገናኝም። አስቸጋሪ ነው! ብቻ ጤና ይስጠን ማለት ነው። ዋናው አገር ሰላም ይሁን ብሎ ጸሎት ማድረግ ነው፤ እንጂ ሌላው ሁሉ ከንቱ ነው!›› አሉ፤ በእናትነትም፣ ተስፋን በጥርጣሬ በሚመለከት እይታም ሆነው።

በ2012 የገና በዓል የሾላ ገበያ ለጋ ቅቤ እስከ 330 እንዲሁም በሳል ቂቤ በ300 ብር እየተሸጠ እንደሆነ አዲስ ማለዳ እስከ እለተ አርብ ታኅሳስ 24 ድረስ ባደረገችው ቅኝት መታዘብ ችላለች። ይህም ከ2012 አዲስ ዓመት ገበያ ጋር ሲነጻጸር ለጋ ቂቤ በኻያ ብር የቀነሰ ሲሆን፣ በአንጻሩ በሳል ቂቤ በኻያ ብር ጭማሬ አሳይቷል።

የተነጠረ ቂቤ ግማሹ ኪሎ 240 እየተሸጠ ሲገኝ፣ ቀደም ካለው ጊዜ ጋር የኻያ ብር ልዩነት አሳይቷል። በ2012 አዲስ ዓመት ገበያም 200 እና 220 ድረስ ይሸጥ ነበር።

በገበያው መካከል አዲስ ማለዳ ካነጋገረቻቸው ነጋዴዎች መካከል፣ የጠላ እህል ለደንበኞቻቸው የሚያቀርቡት አዛውንት መሬቱ ላይ ተቀምጠውና ደገፍ ብለው ደንበኞችን ሲጠባበቁ ነበር። እንደተጫጫናቸው ያስታውቃሉ። ከቡልጋ ነው የማመጣው ያሉትን የጠላ እህል የሚሸጡበት ዋጋ ከአዲስ ዓመት ዋጋ ጋር ሲነጻጸር፣ ቀንሷል ሊባል በሚችል ዋጋ አቅርበዋል። በዚህም ጌሾ 50 ብር፣ ብቅል 60 ብር እንዲሁም እንጨት ጌሾ በ50 ብር እየሸጡ ይገኛሉ።

በተመሳሳይ ነጭ ሽንኩርት የተወቀጠ በ200 እንዲሁም የተፈለፈለ በ100፣ ኮረሪማ 220፣ ጥቁር አዝሙድ 100፣ ነጭ አዝሙድ 80፣ በሶ ብላ 140 በመሸጥ ላይ ይገኛሉ።

በርበሬ የሚሸጡ በእድሜ ጠና ያሉ እናት፣ በርበሬ እንደ ደረጃው ከ90 ጀምሮ 100 እና 110 እየተሸጠ ነው ብለዋል። ምንም እንኳን ከአዲስ ዓመት የበዓል ገበያ አንጻር በርበሬ የ10 ብር ቅናሽ ቢያሳይም፣ ገበያ መቀዛቀዙን ግን በትካዜ ስሜት ይገልጻሉ። ‹‹በርበሬ ዋጋው ውድ ሆኗል። እየቀነሰ ነው ስንል እየጨመረ ነው። ቢሆንም ዋናው ጤና ነው። አገር ሰላም ይሁን›› ሲሉ የበርበሬ ዛላዎችን እያነሱና እየጣሉ አንገታቸውን በማዳበሪያ ከተቆለለው በርበሬው ሳይነቅሉ።

በዓልን በዓል በማስመሰል በኩል፣ ሙያንም በመፈተን የሚጠራው ዶሮ ወጥ ግብዓቱ ካለው የተወሰነ የዋጋ ለውጥ ባሻገር የዶሮ እንዲሁም የእንቁላል ዋጋ ውድነትም የተለመደ ይመስላል። አዲስ ማለዳ የበዓል የገበያ ዳሰሳዎችን ካከናወነችባቸው በዓላት የ2012 አዲስ ዓመትን እንዲሁ የ2011 ትንሣኤ በዓልን ስንመለከት፤ በአዲስ ዓመት አንድ ዶሮ 250 ብር እንደሆነና ገዘፍ ያሉ ዶሮዎች 300 እና 400 መቶ ሲባሉ፤ እንቁላል በ4 ብር ይሸጥ ነበር። ቀደም ባለው የትንሣኤ በዓል ደግሞ፣ ዶሮ 300 ብር ሲሸጥ፣ ‹‹ያለ እንቁላል አይሆንም ያለው ማነው! ከድንችም ጋር ቢሆን በጥሩ ሁኔታ ሠርቼ አቀርባለሁ›› እስኪባል ድረስ፤ የእንቁላል ዋጋ 4 ብር መግባቱ ጉድ አሰኝቶ ነበር።
አሁን ላይ የዶሮ ዋጋ የተወሰነ የዋጋ ለውጥ ሲያሳይ፤ ትንንሽ የሚባሉ ዶሮዎች 250 እና 300 ሲሸጡ፣ በቀረ እስከ 450 ድረስ ደኅና የሚባሉ ዶሮዎች ሻጭና ገዢ እየተከራኩሩባቸው ይገኛሉ።

ቀይ ሽንኩርት ባለፈው የ2012 አዲስ ዓመት በሾላ ገበያና የተለያዩ ማከፋፈያዎች 25 ብር ሲሸጥ፣ በየመንደሩ 28 ብር ይገኝ ነበር። በዚህ የገና በዓል ግን በአንጻሩ ቅናሽ አሳይቶ ከ15 እስከ በ18 ብር ሲሸጥ ቆይቷል። ሌላው በግ ሲሆን በአዲሱ ዓመት መቀበያ 3 ሺሕ ብር ሲሸጥ፣ ደኅና የሚባለውን በግ ልግዛ ላለ 4 ሺሕ 500 ብር እየተጠራ ነበር። አሁንም ይህ ዋጋ ብዙ ልዩነት አላሳየም። በግ ከ3 ሺሕ 500 እስከ 4 ሺሕ 500 ድረስ እንደ አቋሙ እየተሸጠ ይገኛል።

የ2012 የገና በዓል ከቀደመው አንጻር የሚደነቅ ለውጥ አሳየ ለማለት አይቻልም። ሆኖም የቀደሙ የዋጋ ግሽበቶች እንደ ነበሩ የከረሙ በመሆናቸው፣ ሰውም ጉዳዩን ተላምዶት የቆየ ይመስላል። የበዓሉ ድባብ ቀጥለው በሚመጡት ቀናትና በበዓሉ ዋዜማ ድምቀትን ሊያመጡ፣ የዋጋ ልዩነቶችንም ሊያስተናግዱ ግን ይችላሉ።

አዲስ ማለዳ መታዘብ እንደቻለችው ግን፣ ከበዓሉ ድባብ መቀነስ፣ ከዋጋ መጨመርና ከኑሮ ውድነቱ በላይ በገበያው ለዓመታት ደንበኞቻቸውን ሲያስተናግዱ የቆዩ፣ የገበያውን ድምቀትና ሙቀት ሲያጣጥሙ የኖሩ ነጋዴዎች ሁሉ፤ ገበያው ጭር ብሎባቸዋልና ‹‹ዋናው ሰላም ነው፤ አገራችንን ሰላም ያድርግልን!›› የምትል ሐረግ ከንግግራቸው አልተለየችም። ይህም ለገበያ ድምቀትና ለበዓል ድባብ ክስተት፣ የአገር ሰላምና ደኅንነት የሁሉ መሠረት እንደሆነ እንደተረዱና ስጋትም እንደገባቸው ያሳብቅባቸዋል።

የገና ሥጦታ እና የገና ዛፍ
በሾላ ገበያ፣ ገበያው የደራለትና የሞቀለት የገና ዛፍና ጌጣጌጦች ገበያ ይመስላል። የዓለም የቅቤ መሸጫ መለስተኛ ሱቅ ቀዝቅዛ ብትታይም፤ ከፊት ለፊት የሚገኘው የገና ዛፍና ጌጣጌጦችን ከበረንዳው የደረደረ ሱቅ ገቢ ወጪ ደንበኛው ጥቂት አይደለም። በእርግጥ ሁሉም ገዝቶ የሚሔድ አልነበረም።

የገና ዛፎቹ ቀለማቸው ቢመሳሰልም ዋጋቸው የተለያየ ነው። እንደ ምግብ ባለመሆናቸው ሻጮች ተከራክረውና ተደራድረው ለሚገዟቸው ደንበኞች ዋጋቸውን በእጥፍ እስከ መቀነስ ሲደርሱም አዲስ ማለዳ ታዝባለች።
1200 ብር የተባለው አንድ ሜትር ከሃምሳ ርዝማኔ ያለውን የገና ዛፍ ለመግዛት የቆሙ ሴቶች፣ ሲከራከሩ ቆይተው ዋጋው 950 ቢደርስላቸውም፣ ከዛም አልፎ 800 ይሁን ብለው ሲሟገቱ ቆዩ። አልተስማሙም። ‹‹ውድ ነው! ለልጆቼ ደስታ ስል ነው የምገዛው። አንድ ጊዜ የተገዛውም ለተወሰኑ ዓመታት ሊያገለግል ስለሚችል ለጊዜው ባለው ያከብራሉ›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

እናም ዛፉን ትተው ማስጌጫዎች 50 እና 60 ብር ሸምተው ከገበያው ወጥተዋል። ጌጣጌጦቹም ዝቅተኛ ዋጋቸው 50 ብር ሲሆን፣ እስከ 500 ብር የሚደርሱ እንዳሉ ለመታዘብ ተችሏል።

ከዛ በተረፈ የፕላስቲክ የገና ዛፎች 3 ሜትሩ በ5000፣ 2 ነጥብ 4 ሜትሩ 2500፣ 1.5 ሜትሩ 800 ብር ሲሸጡ ነበር። ከግብይቱ መካከል በአንዱ ሱቅ በር ላይ ቆሞ የሚታዘዘውን እየሰማ ደንበኞችን የሚስተናግደው ወጣት፤ የገና ዛፍ ገበያው ቀዝቅዟል ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።

በእርግጥ ከሌላው ገበያ አንጻር የገና ዛፍ መሸጫ ሱቆች ገበያ የደመቀላቸው ቢመስሉም፣ ከቀደመው ጊዜ ይልቁንም ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ እንደተቀዛቀዘ ነው ወጣቱ የገለጸው። ለእርሱ ግን የዚህ ምክንያቱ የዋጋ መጨመር ወይም የኑሮ ውድነት የፈጠረው ጫና አይደለም። ይልቁንም ‹‹የሃይማኖት ተቋማት የገና ዛፍ ባህላችን አይደለም፤ አትጠቀሙ በማለታቸው ነው ገበያው የቀዘቀዘው›› ብሏል።

ቅጽ 2 ቁጥር 61 ታኅሣሥ 25 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here