ዕረቡ ነሐሴ 29 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) ሁሉም ህንፃዎች የህንፃ ስር የተሽከርካሪ ማቆሚያ አገልግሎት መስጠት የሚችሉት የብቃት ሰርተፊኬት ካላቸው ብቻ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ገለጸ።
ህንፃዎች ይህንን ሰርተፊኬት ለማግኘት የተሽከርካሪ መግቢያ እና መውጫ መለየት፣ የትራፊክ ምልክት መጠቀም፣ ምን ያህል የተሽከርካሪ ማቆሚያ አለው፣ ምን ያህሉ ተይዘዋል የሚለውን ጨምሮ አጠቃላይ ሥርዓቱን ዲጂታል በሆነ መልኩ የሚመዘግብ አሰራር ሊኖራቸው ይገባልም ብሏል።
ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ወደ ሥራ የሚገባው ደንብ ከሦስት ዓመት በፊት የተዘጋጀ እና ከሁለት ወር በፊት የፀደቀ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
ለህንፃ ባለቤቶችም የዝግጅት ጊዜ እንደሚሰጣቸው የተገለጸ ሲሆን ህንፃ ለሚገነቡ ከግንባታ ፍቃድ ለተሽከርካሪ ማቆሚያ የሚል ፍቃድ የወሰዱትን ብቻ እንደሚፈቅድ ተገልጻል።
በአሁኑ ወቅት በመዲናዋ በግለሰቦች የተሰሩ ወደ 300 የሚሆኑ ህንፃዎች የተሽከርካሪ ማቆሚያ አገልግሎት መስጠት ይችላሉ ተብለው መለየታቸውን የባለስልጣኑ ምክትል ዳይሬክተር ኤልያስ ዘርጋ ተናግረዋል።
እነዚህ ህንፃዎች በአጠቃላይ 3 ሺህ ለሚጠጉ ተሽከርካሪዎች አገልግሎት የመስጠት አቅም እንዳላቸው ተጠቁሟል።



