ሐሙስ ነሐሴ 30 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) ግብፅ እና ሶማልያ በቀጠናው እያደረጉት ያለውን ወታደራዊ እንቅስቃሴ ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር ሀይል የምስራቁን የአየር ክልል በንቃት በተጠንቀቅ እየጠበቀ እንደሚገኝ አስታውቋል።
በኢትዮጵያ አየር ሃይል የተሰጠውን ሃገራዊ ግዳጅና ተልዕኮ ለመወጣት በላቀ የዝግጁነት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የአየር ምድቡ አዛዥ ኮሎኔል ደረጀ ቡሽሬ ገልፀዋል፡፡
አዛዡ የ3ኛው አየር ምድብ የሃገራችንን ብሎም የምስራቁን የአየር ክልል በንቃት እየጠበቀ የሚገኝ የሃገር መከታና መመኪያ የሆነ ምድብ ነው ያሉ ሲሆን “ወደፊትም ኢትዮጵያን ከውስጥም ይሁን ከውጭ ፀረ ሰላም ኃይሎች ለመጠበቅ በላቀ የዝግጁት ደረጃ ላይ ይገኛል” ብለዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር የምስራቅ ዕዝ በተሟላ ወታደራዊ ዝግጁነት ላይ እንደሚገኝም ተመላክቷል።
“በተለያዩ ዘመናት ሀገራችንን ለመውረርና የሽብር ጥቃት ለመፈፀም የሚሞክሩ ሀይሎችን በመከላከል በመስዋዕትነት የተረከቡትን አደራ ለማስቀጠል እስከ ህይወት መስዋዕትነት ለመክፈል በተሟላ የዝግጁነት ደረጃ ላይ ይገኛሉ” ሲል የሀገር መከላከያ አስታውቋል።


