ልማት ባንክ ባለፉት አምስት ወራት 3.9 ቢሊዮን ብር ብድር አስመለስ

0
893

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የብድር አሰጣጥ እና አመላለስ ስርዓቱን በማስተካከል በ 2012 በጀት ዓመት አምስት ወራት ከ 3 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ የተበላሸ ብድር ማስመለስ መቻሉን አስታወቀ።

ልማት ባንኩ በ 2010 እና 2011 የሰጣቸው የተበላሹ ብድሮች መጠን ባንኩን ኪሳራ ውስጥ ከተውት የቆየ ሲሆን፣ በወቅቱም ከ 40 ቢሊዮን ብር በላይ ከሚሆን ገንዘብ ውስጥ እስከ 18 ቢሊዮን የሚደርሰው የተበላሸ እንደነበር ይታወሳል። ይህንንም ተከትሎ በተደረገ የአመራር ለውጥ እንዲሁም በብድር አሰጣጥ እና አመላለስ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራቱ የተገለፀ ሲሆን፣ ብድራቸውን መክፈል ያልቻሉ ድርጅቶችን ንብረት እስከመውረስ የሚደረስ እርምጃ ተወስዷል። ይህ እርምጃም ለተሰበሰበው ብር ከፍተኛ መሆን ጉልህ ሚና እንደነበረው ባንኩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታውቋል።

ከእነዚህም ውስጥ ድርጅቱ በቱርክ ባለሀብቶችና ከልማት ባንክ በተገኘ ብድር በ 2000 የተቋቋመና ከ4 ሺሕ 500 በላይ ለሚሆኑ ሠራተኞች የሥራ ዕድል የፈጠረ የጨርቃ ጨርቅ አምራች ፋብሪካ በደረሰበት ኪሳራ የባንኩን ብድር አለመመለሱን ተከትሎ፣ ልማት ባንኩ በመረከብ በማስተዳደር ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።

በያዝነው በጀት ዓመት የመጀመሪያ አምስት ወራት ባንኩ 3.13 ቢሊየን ብድር አፅድቋል። ከዚህም ውስጥ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ 59 በመቶ፣ የፋይናንስ አገልግሎት 28 በመቶ፣ የግብርና 6.6 እና ሌሎች ዘርፎች 6.68 በመቶ ድርሻ መያዛቸውን እና ለእነዚሁ ዘርፎች 3.75 ቢሊየን ብር ብድር የተለቀቀና አፈፃፀሙም 81 በመቶ መድረሱ ተገልጿል።

በዚሁ በጀት ዓመት ሦስት ወራት ውስጥም ከኪሳራ በመውጣት 213.77 ሚሊዮን ብር አትርፎ የነበረው ባንኩ፣ የተበላሸ ብድር ምጣኔውን ከ 39 በመቶ ወደ 33 በመቶ መቀነስ ችሎ ነበር። አጠቃላይ የሀብት መጠኑ 84.1 ሚሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ 7 ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር ካፒታል እንዳለው ከባንኩ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

ቅጽ 2 ቁጥር 62 ጥር 2 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here