ሕብረት ባንክ የቀድሞዉን ዋና ሥራ አስፈፃሚ በሽልማት አሰናበተ

0
556

ሕብረት ባንክ ባለፈዉ ቅደሜ ታኅሳስ 25/2012 የባንኩ የቀድሞ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበሩት ታዬ ዲበኩሉን በሂልተን ሆቴል በተካሄደ ደማቅ የሽኝት ፕሮግራም ማሰናበቱን አስታወቀ።

በዝግጅቱ ላይ የአሁኑ የባንኩ የቦርድ ኃላፊ ዛፉ ኢየሱስ ወርቅ እና ከፍተኛ የባንኩ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች መገኘታቸዉ የተገለፀ ሲሆን፣ ለቀድሞ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ታዬ ምስጋና እና ለባንኩ ላበረከቱት አስተዋፅኦ ሽልማት እንደተበረከተላቸው ተገልጿል።

ባንኩ በዛፉ ኢየሱስ ወርቅ እና የባንኩ ዋና ሥራ አስፈፃሚ በሆኑት መላኩ ከበደ በኩል የእውቅና ሰርተፍኬት መስጠቱም ተመላክቷል። በሽኝት ፕሮግራሙ ታዬ በባንኩ በነበራቸው የሥራ ጊዜ ሲገለገሉበት የነበረውን (V8) ተሽከርካሪ እና የባንኩ አርማ የታተመብት የአንገት ወርቅ በሽልማት ማበርክቱን በመግለጫዉ ጠቅሷል። ታዬ በበኩላቸው በሽኝት ፕሮግራሙ ላይ ለባንኩ ያላቸዉን መልካም ምኞትና የስኬት ጉዞ በመናገር፣ ወደፊት ከባንኩ ጎን ለመቆም ያላቸዉን የቁርጠኝነት አቋም ገልጸዋል። በማንኛዉም ጊዜ ሕብረት ባንክ የእርሳቸውን እገዛ በሚፈልግበት ሰዓት ድጋፍ እንደሚያደርጉ መናገራቸውንም ባንኩ ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

ታዬ በባንክ ኢንዱስትሪ ዉስጥ ከ 30 ዓመታት በላይ ያገለገሉ ሲሆን፣ በሕብረት ባንክ በፕሬዝዳንትነት እስከ ተሾሙበት ጊዜ ድረስ በምክትል ፕሬዝዳንትነት አገልግለዋል። በፕሬዝዳንትነትም ከ6 ዓመት ተኩል በላይ አገልግለዋል።

ሕብረት ባንክ እንደ አዉሮፓዉያን የዘመን አቆጣጠር በ2018/2019 የበጀት ዓመት 752.3 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን የወጡ ሪፖርቶች ያመላክታሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 62 ጥር 2 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here