‹‹አገራችንን እንዳላገለገልን እንደ ሸንኮራ ተመጠን ተጥለናል››ጡረተኞች 

ዕረቡ መስከረም 08 ቀን2017 (አዲስ ማለዳ) መንግስት በመስከረም ተግባራዊ ይደረጋል ያለውን የመንግስት ሰራተኞች የደሞዝ ማሻሻያን ተከትሎ በጡረታ የሚተዳደሩ አቅመደካሞች ምንም አይነት ማሻሺያ አልተደረገልንም ይህም ለአገር የነበረንን ውለታ ማራከስ ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ቅሬታቸውን አሰምተዋል

“ጡረተኛው አገሩን አገልግሎ ዋጋ ከፍሎ ተረስቷል በችጋር እንዲያልቅ የተፈረደበት ይመስላል” ያሉት ቅሬታ አቅራቢ ጡረተኞቹ እንኳን በጡረታ ክፍያ በዋና ደሞዝ ኑሮ መምራት ከባድ መሆኑ እየታወቀ ይህ ከግምት አለማስገባት የሚያሳዝን ነው ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከወራት በፊት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን በተመለከተ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ዝቅተኛ የሆነ ወርሃዊ ደመወዝ ለሚከፈላቸው ሠራተኞች እስከ 300 እጥፍ ድረስ የደመወዝ ማሻሻያ ይደረጋል ሲሉ ገልጸው እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

ቤተሰቤን በማገኛት የጡረታ ብር ነው የማስተዳድረው ሲሉ ቅሬታቸውን ያቀረቡ አንድ ጡረተኛ አሁን ላይ የማገኘው ጡረታ የኑሮዬን አንድ ሶስተኛ የሚሸፍን አይደለም ሲሉ መጪውን ጊዜ ለእኛ ምን ታስቧል በማለት ጠይቀዋል፡፡

ለመሆኑ የጡረተኞቹ ጉዳይ በአዲሱ የደሞዝ ማሻሺያ መሰረት እንዴት ሊታይ ነው የሚለውን ምላሽ ለማግኘት ወደ መንግስት ሰራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር ተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም አልተሳካም፡፡

አዲሱ የደመወዝ ጭማሪ እንደጠበቅነዉ አይደለም ያሉ የተለያዩ የመንግስት ስራተኞች ጥናቱ በሚኒስትሮች ምክር-ቤት ቀርቦ ከመፅደቁ በፊት በድጋሚ መታየት እንዳለበት ተናግረው ነበር፡፡

ከመስከረም 1 ጀምሮ ተግባራዊ የሆነው አዲሱ የደመወዝ ማሻሻያ ጥናት የሚኒስትሮች ምክር-ቤት ከማፅደቁ አስቀድሞ ሰራተኞችን ማወያየት እንዳለበት እና በድጋሚ መታየት እንደሚኖርበት መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here