አፍሪካ ቦክስ ፌደሬሽን የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴን አሰራር እንደሚቃወም ገለጸ

0
330

ሐሙስ መስከረም 09 ቀን 2017 (አዲስ ማለዳ) የአፍሪካ ቦክስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢያሱ ወሰን የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴን አሰራር እንደሚቃወሙ ገልጸዋል፡፡

አቶ ኢያሱ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ ከቀድሞ አትሌቶች ሀይሌ ገብረስላሴ ፤ ገዛህኝ አበራ እና ታምራት በቀለ ጋር በመሆን ጉዳዩን እየተከታተሉት እንደሆነ እና ጠንካራ አቋም እንደያዙ ተናግረዋል፡፡

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የኦሎምፒክ ኮሚቴውን የባንክ አካውንቶች ማገዱንም አያይዘው ገልጸዋል፡፡ ኦሎምፒክ ኮሜቴው 6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ኦዲት ያላስደረገ መሆኑን በጽሁፋቸው አስፍረዋል፡፡

ከዚህም ውስጥ 156 ሚሊዮን ብር ለ2020 የቶኪዮ ኦሎምፒክ ወጪ የተደረገ 47 ሚሊዮን ብር ደግሞ ለሀገር አቀፍ ውድድሮች የወጣ እንደዚሁም 500 ሺህ ዶላር ለአፍሪካ ውድድሮች ግልጽ ባልሆነ መንገድ የዋለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የምርጫ ማጭበርበር እና ህገወጥ የሰዎች ዝውውር የኦሎምፒክ ኮሚቴው ከተነሱበት ችግሮች መካከል እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡ ይህም የኢትዮጵያን ስፖርት ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል ነው በማለት በመልዕክታቸው አስፍረዋል፡፡

ግልጽነት ያለው እና ሃላፊነት የሚውሰድ አካልን እንፈልጋለን ያሉት ፕሬዝዳንቱ፣ የሚወሰደው እያንዳንዱ እርምጃ አትሌት እና ደጋፊ በስፖርቱ ላይ እምነት እንዲኖረው ለማድረግ ታስቦ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

 

በብሩክ ገነነ

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here