አቶ ጌታቸው ረዳ ሰሞነኛውን የኤርትራ ሰራዊት እንቅስቃሴ በሚመለከት ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ምን አሉ?

የኤርትራ ሰራዊት በሰሜን ምስራቅ ትግራይ የሚገኙ ከተማዎችን ተቀቆጣጥሮ እየተስፋፋ ነው በአካባቢውም ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት እየፈጸመ ነው የሚሉ መረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ፡፡

በአካባቢው ያለው አሁናዊ ሁኔታስ ምን ይመስላል በሚለው ጉዳይ ላይ የአካባቢውን ነዋሪዎችና ፣የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንትን አነጋግረናል፡፡

በአካባቢው ያሉ ነዋሪዎች የኤርትራ ሰራዊት ከፍተኛ የሆነ የሰብአዊ መብት ጥሰት ዝርፊያ እየፈጸመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለመሆኑ ይህን የነዋሪዎች እሮሮ የክልሉ ጊዚያዊ አስተዳደር እንዴት ያየዋል? በአካባቢውስ ያለው አሁናዊ ሁኔታ ምንድን ነው ስንል ለክልሉ ጊዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ጥያቄ አቅርበናል፡፡

አቶ ጌታቸው በማብራሪያቸው የኤርትራ መንግስት በአካባቢው ላይ ላለፉት አመታት በርከት ያሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በመፈጸም ላይ እንደሚገኝ በመግለጽ ቀደም ሲል የነበረው ችግር ተባብሶ ቀጥሏል ብለዋል፡፡

ከሰሞኑ ስለሚነሳው የኤርትራ መንግስት የመስፋፋትና ተጨማሪ ወረዳና ቀበሌዎችን የመያዝ ጉዳይስ ምን ይመስላል ስንል ተጨማሪ ጥያቄ ያቀረብንላቸው የጊዚያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት አሁን ላይ የኤርትራ ሰራዊት በተጨማሪነት የያዘው የትግራይ መሬት የለም ሲሉ አጭር ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የኤርትራ ሰራዊት ከትግራይ መሬት እንዲወጣ ተደጋጋሚ ንግግሮችን ከፌደራል መንግስቱ ጋር እያደረግን ነው ያሉት አቶ ጌታቸው ይህ ጉዳይ የፕሪቶሪያው ስምምነት አንድ አካል መሆኑ መዘንጋት የለበትም ብለዋል፡፡

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ዙሪያ ከመንግስት ኮሚኒዩኬሽን አገልግሎት ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገቸው ጥረት አልተሳካም፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here