ማክሰኞ መስከረም 21 ቀን 2017 (አዲስ ማለዳ) ምሽቱን ኢራን በእስራኤል ላይ ከፍተኛ የሚሳኤል ድብደባን ፈጽማለች። ኢራን ከ180 በላይ የባለስቲክ ሚሳኤሎችን ተኩሳለች የተባለ ሲሆን ብዙዎቹ ቢከሽፉም በእስራኤል ምድር ላይ የወደቁ ሚሳኤሎች መኖራቸዉ ግን ከስፍራው የቀጥታ ስርጭት ዘገባ ከሚሰሩ የዜና አዉታሮች መረዳት ተችሏል።
አሁን ላይም ኢራን በእስራኤል ላይ 2ኛ ዙር ጥቃት ካልፈጸመች በቀር የመጀመሪያው የአየር ጥቃት ቆሟል ተብሏል።
በጥቃቱ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በቴላቪቭ ጃፋ በተባለ ስፍራ በትንሹ 6 ሰዎች ሞተዋል ተብሏል።
ኢራን ጥቃቱን በእስራል ላይ ያደረገችዉ በሁለት አቅጣጫዎች ነዉ ።
ቴልአቪቭ ፤ ለቴርሃን ጥቃት ምን አይነት ምላሽ ትሰጣለች የሚለዉ አሳሳቢዉ ጉዳይ ሲሆን ጦርነቱን ሀያላኑ ሀገራት እንዳይቀላቀሉት አስግቷል።
የእስራኤል መከላከያ ሀይል በበኩሉ ከ 180 በላይ ሚሳኤሎች መተኮሳቸዉን እንዳረጋገጠ ተዘግቧል።
እስራኤል የኢራን የአየር ጥቃት መቆሙን ተከትሎ ዜጎች ከሚሳኤል መሸሸጊያዎች እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፋለች።
እስራኤል ሶስት የአየር ጥቃት መከላከያ ያላት ሲሆን ሶስቱን የጸረ ሚሳኤል መከላከያን የጣሱ የኢራን ሚሳኤሎች ግን በእስራል ላይ ቀላል የማይባል ጉዳት እንደሚያደርሱ ኤቢሲ ኒውስ ዘግቧል።


