ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በቀጣይ የሀገሪቱ ርዕሰ ብሄር ሆነው መቀጠል እንደማይፈልጉ ተሰማ

0
342

ቅዳሜ መስከረም 25 ቀን 2017 (አዲስ ማለዳ) ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጥቅምት ላይ የሚጠናቀቀውን የስራ ዘመናቸውን ተከትሎ በርዕሰ ብሄርነት መቀጠል እንደማይፈልጉ ተሰምቷል።

ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ለበርካታ ወራት በስራ ድርሻቸው ዙርያ በሚፈፀሙ አንዳንድ ድርጊቶች እና ከስራ አስፈፃሚው አካል ጋር ባላቸው ጤናማ ያልሆነ ግንኙነት ደስተኛ እንዳልነበሩ ሰምቻለሁ ሲል መሠረት ሚድያ ዘግቧል።

በመጪው ሳምንት የመጀመርያ ቀናት ይህን ያለመቀጠል ውሳኔያቸውን ለስራ አስፈፃሚው አካል ያሳውቃሉ ተብሎም ይጠበቃል።

በዛሬው እለት በኤክስ (ትዊተር) ገጻቸው ላይ “እነ ጥላሁን ገሠሠ: ቴዲ አፍሮ: አሊ ቢራ:ማህሙድ አህመድ..ድንቅ ድምጻውያን መካከል ናቸው::”የሰው ልጅ ሆዱ ሲከፋው ጊዜም እንደ ሰው ሲገፋው:መሄጃ መውጫ ሲጠፋው ዝምታ ብቻ ነው ተስፋው”ይላል ማህሙድ “ዝምታ ነው መልሴ”ን ሲያዜም::ለአንድ ዓመት ሞከርኩት” የሚል ፅሁፍ አስፍረው ነበር።

ይህን ተከትሎ የፕሬዝደንት ፅ/ቤት ሀላፊው አቶ ፍቃዱ ሰቦቃ “የፕሬዝደንት ሳህለ-ወርቅ ኦፊሴላዊ አካውንት አለ፣ እኛ አስተያየት መስጠት የምንችለው በእሱ ዙርያ ነው። የተባለው ፅሁፍ በግል አካውንት ላይ ስለተለጠፈ ቢሯችንን አይመለከትም” ብለዋል።

ይህ ፅሁፍ በበርካቶች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኖ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በመዘዋወር ላይ ይገኛል ።

ፕሬዚዳንቷ ባጋሩት ጽሁፍ በስራቸው ላይ አንዳች እክል እንደገጠማቸው አመላካች እንደሆነም በርካቶች አስተያየታቸውን በማጋራት ላይ ይገኛሉ።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here