“አሁን ባለው የስልጣን ፉክክር ጥያቄያችን ምላሽ ማግኘቱ ያጠራጥረናል”-የ70 ካሬ የቤት ግንባታ ማህበር አባላት

0
537

👉”ከአስተዳደሩ መመሪያ እስኪሰጥ ምንም ልናደርግ አንችልም”የትግራይ ክልል ቤቶች ልማት

ሃሙስ መስከረም 30 ቀን 2017(አዲስ ማለዳ) በትግራይ ክልል በተለይ በመቀሌ የሚገኙ በተለምዶ የ70ካሬ የቤት ግንባታ ማህበራት ከክልሉ መንግስት ጋር በተስማሙት መሰረት የግንባታ ቦታ እንዳልተሰጣቸው እና ከሰሞኑ በክልሉ ያለው የአስተዳደር ሁኔታ ስጋት ውስጥ እንደከተታቸው ገልጸዋል፡፡

ከሰሜኑ ጦርነት በፊት 2011 ዓ.ም የተደራጁ ከ3ሺ በላይ ማህበራትን ያሳተፈ እና በተለምዶ 70 ካሬ ይባል እንጂ ለመኖሪያ ቤት ግንባታ የሚሰጠው 84 ካሬ.ሜ እንደሆነ አባላቱ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡

60ሺህ 860 አባላትን ያካተተው 3ሺ 43 የቤት ግንባታ ማህበራት በ20 ሺ ብር የመደራጃ ገንዘብ ጀምረው ቀጥሎም 40ሺብር ከከፈሉ በኳላ በየወሩ በባንክ እየቆጠቡ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በፊት በተመሳሳይ መንገድ ተደራጅተው በሁለት ዙር የቤት ግንበታ ቦታ የደረሳቸው መኖራቸውን የገለጹት የማህበሩ አባላት በሶስተኛ ዙር እንዲደርሳቸው ቢደራጁም 2ሺ አንድ መቶ አካባቢ ማህበራት ምንም አይነት ቦታ እስካሁን እንዳልተሰጣቸው ጠቁመዋል፡፡

“የብር አቅም መዳከም የሚታወቅ ነው እስካሁን የከፈልነው ብር አሁን ላይ ያለው አቅም አነስተኛ ነው በመሆኑም ገንዘባችንን ሳይሆን ቦታ እንዲሰጠን ነው የምንፈልገው በመጠበቅ ብዙ አመታትን አስቆጥረናል” ሲሉ በምሬት ገልጸዋል፡፡

አክለውም “የቆጠብነው ገንዘብ ስላጠፉት ነው ቦታውን ሊሰጡን ያልቻሉት” የሚል ስጋት እንዳለባቸው አያይዘው ጠቁመዋል፡፡

የክልሉ መንግስት ግን ከጦርነቱ በኋላ ምንም አይነት ምላሽ እንዳልሰጠ እና ከሰሞኑ ባለው የአስተዳደር አለመግባባት ደግሞ ይበልጥ ነገሩን እንደሚያወሳስበው እና መፍትሄ ለማግኘት ስጋት ውስጥ መሆናቸውን አመላክቷል፡፡

ስለሆነም አባላቱ ከዚህ ቀደም እንደሚሰጠው 84 ካሬ ባይሰጠን እንኳን ቢያንስ ቃል የተገባልን 70 ካሬ ይሰጠን ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

አዲስ ማለዳ ከመንግስት አካላት ምላሽ ለማግኘት ባደረገችው ጥረት የክልሉ የቤቶች ልማት ኤጀንሲ አነጋግራለች፡፡

የትግራይ ክልል ቤቶች ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ ሀላፊ የሆኑት ገብረግዚያብሄር አብርሃ እንደገለጹት “እንደሚታወቀው እስካሁን ሊሰጣቸው ያልቻለው በነበረው የሰላም እጦት መሆኑ ግልጽ ነው” ብለዋል፡፡

‹አክለውም አሁን ባለው ሁኔታ ግን ጉዳዩ በካቢኔ ታይቶ በአስተዳደሩ ውሳኔ ሲያገኝ ነው ወደ ትግበራ የሚገባው እኛም እስካሁን የደረሰን መመሪያ ባለመኖሩ ምንም ልናደርግ አንችልም ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም በተለምዶ 70 ካሬ ማህበራት ቢባልም በመንግስት የሚታወቀው የመኖሪያ ቤት የህብረትስራ ማህበር በመባል እንደሚታወቁ እና በሚወጣው መመሪያ መሰረት እንደሚስተናገዱ ነገር ግን እስካሁን ከአስተዳደር የወጣ መመሪያ አለመኖሩን ሀላፊው ጠቁመዋል፡፡

በክልሉ በሁለት ጽንፍ ያለው የፖለቲካ ውዝግብ በትግራይ ክልል ነዋሪዎች ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ አልቀረም ለዚህ ማሳያም የ70 ካሬ የቤት ግንባታ ማህበራት ሲሆኑ በትናንትናው ዕለት ቅሬታቸውን ለሚመለከተው አካል ለማቅረብ ተዘጋጅተው የነበረ ቢሆንም በዚሁ ምክንያት መጠየቅ አለመቻላቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here