ቅዳሜ ጥቅምት 2 ቀን 2017 (አዲስ ማለዳ) አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 74ኛ የምስረታ ዓመቱ ላይ ሆኖ የቀድሞ ምሩቃኑን በማሰባሰብ ዩኒቨርሲቲያቸውን እንዲጎበኙ፣ ትዝታቸውን እንዲያድሱና በሚችሉት ሁሉ የዩኒቨርሲቲው የለውጥ አካል እንዲሆኑ የሚያስችላቸውን ዕድል አመቻችቷል።
በዚህም በርካታ የቀድሞ ምሩቃን በዩኒቨርሲቲው ተገኝተው የመርሀ ግብሩ አካል ሆነዋል።
በቀድሞ ምሩቃኑ መርሀ ግብር ላይ የተገኙት ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ፥ ከእውቀት ወደ ወረቀት የሚደረገው ሩጫ የትውልድ የዕውቀት ክፍተት ፈጥሯል፤ ይህን መሙላት እና ዕውቀት ላይ ማዕከል ያደረገ ስራ መስራት ይገባል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ የሚጠቀስ ትልቅ ተቋም ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ለሀገር የሚተርፍ እውቀት የሚመረትበት ተቋም እንዲሆን የሚደረገውን ርብርብ መንግሥት ያግዛል ሲሉ አረጋግጠዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቻንስለር ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ፥ ዩኒቨርሲቲዎቻችን የመማር ማስተማር ነፃነታቸው ተጠብቆ ስለ ሀገርና ስለ ዓለም ችግሮች የሚጨነቁ፣ የሚመራመሩ እና መፍትሄ የሚያፈልቁ፤ ተማሪና መምህራንን የሚይዙ እንዲሆኑ ማድረግ ይኖርብናል ሲሉ በመርሀ ግብሩ ላይ ተናግረዋል።
ይህን ለማረጋገጥም የቀድሞ ተመራቂዎች የየዩኒቨርሲቲዎቻቸው የለውጥ ጅማሮ ፊት አውራሪ በመሆን ተቋማቱን ማገዝና መደገፍ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።



