ሀሙስ ጥቅምት 07 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና እንስቲትዩት “ወቅታዊ ጉንፋን እና ጉንፋን መሰል የመተፈንሻ አካላት ህመም” በተመለከተ በጋራ ባወጡት መግለጫ “የክረምት ወራት ወይም የዝናብ ወቅት ማብቃቱን ተከትሎ መስከረምን ጨምሮ በጥቅምትና ህዳር ወራት እንደዚህ አይነት ጉንፋን መሰል ህመም የሚጠበቅ ነው” ብለዋል፡፡
ለጉንፋን ሕመም መከሰት 50 በመቶ ድርሻውን የሚይዘው ሪኖ ቫይረስ ነው ያለው መግለጫው ኮሮና፣ ኢንፍሉዌንዛ፣ ፓራ ኢንፍሉዌንዛ፣ አር ኤስ ቪ(RSV) ቫይረሶች ደግሞ ለጉንፉን መሰል ህመሞች መከሰት ዋና ዋና ምክንያቶች ናቸዉ ብሏል።
በዚሁ ወቅት የተከሰተው ጉንፋን መሰል ህመም በአብዘሃኛው (አር ኤስ ቪ) ቫይረስ መሆኑን የተጠቆመ ሲሆን ባለፈዉ አንድ ወር ዉስጥ ተመርምረዉ አር ኤስ ቪ ከተገኘባቸዉ ታካሚዎች መካከል 84% ያክሉ እድሜያቸዉ ከ5 አመት በታች ነዉ። እንደዚሁም ባለፈዉ ሳምንት ለአር ኤስ ቪ ከተመረመሩት 81 ናሙናዎች 49 (60.5%) ያህሉ ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል።
ሕመሙ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፈውም በቫይረሱ የተጠቃ ሰው በሚያስልበት ወይም በሚያስነጥስበት ጊዜ እንደሆነና በተጨማሪም ሰዎች ቫይረሱ ያረፈበትን የበር እጀታ፣ ጠረጴዛ ወይም በሕመምተኛው የተነካካንን ሰው እጅ ከነኩ በኋላ አፋቸውንና አፍንጫቸውን ሲነካኩ ቫይረሱ ለመተላለፍ በሚፈጠርለት ምቹ ሁኔታ መሆኑን ጠቁሟል።



