ሰኞ ጥቅምት 11 ቀን 2017 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር 37ኛ መደበኛ የምክር ቤት ስብሰባውን ማጠናቀቁን ገልጿል።
የማህበሩ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዮሐንስ በንቲ በስብሰባ ላይ የ2016 ዓ.ም የስራ አፈፃፀምና የኦዲት ሪፖርት ካቀረቡ በኋላ ሰፊ ውይይት መደረጉን ማህበሩ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
በውይይቱም መምህራንን እየተፈታተነ ያለው ከፍተኛ የኑሮ ውድነት፣ረጅም ጊዜ አገልግሎት ያላቸው መምህራን የደረጃ እድገት ወይም የእርከን ጭማሪ አለመኖር፣በአንዳንድ ክልሎች የመምህራን ደሞዝ በጊዜ አለመከፈል ብሎም እየተቆራረጠ መከፈል፣ያለመምህራን ዕውቅናና ፈቃድ በተለያዩ ምክንያቶች የደሞዝ መቆረጥ ችግሮት መነሳታቸው ተጠቁሟል፡፡
በተጨማሪም ቀደም ብሎ የተጀመረው የመምህራን የመኖሪያ ቤት እና የመሥሪያ ቦታ በሚፈለገው ፍጥነት እየተከናወነ ያለመሆን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ደግሞ ጭራሽ አለመጀመሩ፣በትርፍ ሰዓት ክፍያ ላይ ተደራራቢ ግብር መቆረጡ፣የመጽሐፍትና ሌሎች ግብአቶች እጥረት እና የክረምት መምህራን ስልጠናና ያጋጠሙ ችግሮች በተሳታፊዎች በአስተያየት እና በጥያቄ መልክ ተነስተዋል።
የትምህርት ሚንስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ኮራ ጡሹነ ከመምህራን ጥቅማ ጥቅም ጋር በተያያዘ እየታየ ያለው ጥያቄ የተጀመረው የትምህርት ሴክተር ሪፎርም ተጠናቆ ተግባራዊ ሲሆን ብዙ ጉዳዮች እንደሚፈቱ ገልፀዋል ።



