ኖክ 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር አጠቃላይ ትርፍ አስመዘገበ

0
768

የነዳጅ ገበያውን ከተቀላቀለ 15 ዓመታት ያስቆጠረው ናሽናል ኦይል ኢትዮጵያ (ኖክ) በተጠናቀቀው የፈረንጆች ዓመት ከግብር በፊት 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር አጠቃላይ ትርፍ ማትረፉ ታወቀ። የኩባንያው የተጣራ ትርፍ ወደ 800 ሚሊዮን ብር የተጠጋ ሲሆን፣ ይህም ከኹሉም ነዳጅ አከፋፋይ እና አቅራቢ ድርጅቶች ትልቁና በድርጅቱም ታሪክ ከፍተኛው ነው ተብሏል።
ከድርጅቱ ምሥረታ አንስቶ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ በመሆን እያገለገሉ የሚገኙት ታደሰ ጥላሁን ከአዲስ ማለዳ እህት መጽሔት ኢትዮጵያን ቢዝነስ ሪቪው ጋር ቆይታ ባደረጉበት ወቅት እንደተናገሩት፣ በፈረንጆቹ 2019 በአገሪቱ የነበረው አለመረጋጋት ኩባንያው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳደረ ቢሆንም በድርጅቱ ታሪክ ከፍተኛ የሚባል ትርፍ ማስመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል።
ከ60 በመቶ በላይ የኖክ ትርፍ የተገኘው ከመኪና ቅባቶች፣ የከሰል ድንጋይ አቅርቦት፣ የምግብ ማብሰያ ጋዝ እና ሬንጅ ሽያጭ ሲሆን፣ ቀሪው ከነዳጅ ዘይቶች ሽያጭ የተገኘ መሆኑ ታውቋል። በተለይም ድርጅቱ የሚያቀርባቸው የመኪና ዘይቶች እና ቅባቶች ጥራታቸው ከፍተኛ መሆኑ ድርጅቱ ትርፋማ እንዲሆን ትልቅ ሚና እንደተጫወተ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገልፀዋል። በተጨማሪም ድርጅቱ ከዚህ ቀደም ያገኘውን ትርፍ ለተጨማሪ ኢንቨስትመንት ማዋሉ ውጤታማ እንዲሆን ምክንያት እንደሆነ ተናግረዋል።
የሼህ አላሙዲን፣ የታዋቂው ባለሃብት አብነት ገብረመስቀል እና የታደሰ ንብረት የሆነው ኖክ፣ በኢትዮጵያ ካሉት ሁሉም የዘይት አቅራቢዎች የላቀ የገበያ ድርሻ ያለው ሲሆን፣ ከሲሶ በላይ እንደሆነ አንዳንድ ሰነዶች ያሳያሉ። ከ215 በላይ ነዳጅ ማደያዎች ያሉት ኖክ፣ ኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ ከአንድ ሺሕ በላይ ኮርፖሬት ደንበኞች ያሉት ሲሆን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድን የአውሮፕላን ነዳጅ አቅርቦት ከ53 በመቶ በላይ እንደሚሸፍን ከኩባንያው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
በኢትዮጵያ የመጀመሪያው አገር በቀል የግል ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የሆነው ኖክ፣ ባለፈው ዓመት ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ ግብር ለመንግሥት የከፈለ ሲሆን፣ ይህም ከከፍተኛ ግብር ከፋዮች ተርታ እንዲሰለፍ አድርጎታል። ከዚህ ውስጥ ግማሽ ቢሊየን ብር የሚጠጋው የትርፍ ግብር ሲሆን፣ ቀሪው ደግሞ የተጨማሪ ዕሴትና ሌሎች የግብር አይነቶች ናቸው።
በያዝነው በጀት ዓመት አንድ ቢሊየን ብር የተጣራ ትርፍ ለማግኘት ያቀደው ኖክ፣ በጅቡቲ ያለውን ንግድ ለማስፋት ከያዘው ዕቅድ በተጨማሪ በአዲስ ኢንቬስትመንት በኬኒያ፣ ሶማሌ ላንድ፣ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳንና ኤርትራ ቅርንጫፎች በመክፈት ዓለማቀፍ የነዳጅ ድርጅት የመሆን ፍላጎት እንዳለው ሥራ አስፈፃሚው ተናግረዋል። በተመሳሳይ ድርጅቱ በአፍሪካ ጎዳና ላይ ከአንድ ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ገንዘብ ዘመናዊ ዋና መሥሪያ ቤቱን ያስገነባ ሲሆን፣ ህንፃው በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ እንደሚመረቅ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 33 ነዳጅ አቅራቢ ድርጅቶች ይገኛሉ። ባለፉት አስርት ዓመታት ውስጥም ቁጥራቸው በሦስት እጥፍ አድጓል። በየዓመቱ የነዳጅ ገበያውን የሚቀላቀሉት ድርጅቶች ቁጥራቸው ቢጨምርም፣ በመንግሥት የተቀመጠው የትርፍ ሕዳግ አነስተኛ መሆን ብዙዎች ከስረው ከገበያ እንዲወጡ ምክንያት እየሆነ እንደሆነም ይታወቃል።

ቅጽ 2 ቁጥር 62 ጥር 2 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here