የቤኒሻንጉል ክልል አዲስ ፓርቲ ለመመሥረት ዝግጅት ላይ የነበሩ ሰዎችን አሰረ

0
610

የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ የክልሉ ፖሊስ ድርጊቱን እንዲያስቆም ደብዳቤ ጽፈዋል

የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ የክልሉ ፖሊስ ድርጊቱን እንዲያስቆም ደብዳቤ ጽፈዋል

የቤኒሻንጉል ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ‹‹ቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ›› የተሰኘ አዲስ ፓርቲ ለመመሥረት በዝግጅት ላይ የነበሩ 10 ግለሰቦች ላይ የእስር ማዘዣ በማውጣት ሰብሳቢውን ጨምሮ አራት ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር አዋለ።
የፓርቲዉ ምክትል ሰብሳቢ ጌታሁን መርጋ፣ የሕግ ባለሙያ የሆኑት ጌታቸዉ ወድሻ፣ የድርጅት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ጉዮ ፈረደን (ዶ/ር) ሐሙስ ታኅሳስ 30/2012 መታሰራቸውን የቦሮ ፓርቲ የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ ዮሐንስ ተሰማ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ጥር 01/2012 በፓርቲው የቡለን ወረዳ የወጣቶች ኃላፊ የሆኑት ታምራት ጎዶሶ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጨምረው ገልጸዋል።
የፓርቲዉ አመራሮች በቁጥጥር ስር የዋሉት በአሶሳ ዩንቨርሲቲ ችግር እንዲፈጠር አድርጋችኋል በሚል የነበር ቢሆንም፣ ጥር 01/2012 ሐሳቡ ተቀይሮ ‹‹የክልሉ ምክር ቤት የፋይናንስና ገንዘብ ቋሚ ሰብሳቢ በሆኑት በአብደላሂ ሀጂ ግድያ እጃችሁ አለበት›› ተብሎ መምጣቱን ጠቅሰዋል።
ፓርቲዉ በምርጫ ቦርድ ለመመዝገብ በሚደርገዉ ሂደት በምርጫ አዋጁ መሰረት መስፈርቱን አሟልቶ እውቅና ለማግኘት በአሶሳ ጽሕፈት ቤት ለመክፈት በተሰባሰቡበት ወቅት፣ በክልሉ ፖሊስ እንደታገዱ ዮሐንስ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል። የክልሉ ፖሊስ ፓርቲዉ የሚያደርገውን ትግል ከመጀመሪያዉ ጀምሮ ጫና እያሳደረበት ነው ሲሉም ቅሬታቸውን አሰምተዋል።
ቦሮ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ የሽናሻን ሕዝብ ወክሎ የሚንቀሳቀስ በምሥረታ ላይ ያለ ክልላዊ ፓርቲ መሆኑን የገለጹት ዮሐንስ፣ ፓርቲዉ እንደ ድርጅት መቋቋም ከጀመረበት ቀን ጀምሮ ብዙ አባሎቻቸዉ እንደታሰሩባቸዉ እና አሁንም ሕጋዊ እውቅና ለማግኘት የሚያደርጉትን ሂደት ለማደናቀፍ ጫናዎች እንደበዙበቸዉ ተናግረዋል።
‹‹በአሁኑ ጊዜም ቀሪ የፓርቲዉ አመራሮችን እኔን ጨምሮ ለማሰር የክልሉ ፖሊስ እየፈለገን ነው›› በማለት ከክልሉ ተሸሽገው እንደሚገኙም ተናግረዋል። አክለውም በክልሉ ዴሞክራሲያዊ አካሄድ አለመኖሩን ጠቅሰዉ ‹‹ምንም አይነት የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳይቋቋሙ እንዲሁም ነፃ የፖለቲካ ምህዳር አንዳይበለፅግ ጭቆና ይደረጋል›› ሲሉ ጠቅሰዋል።
ቦሮ ፓርቲ የሽናሻን ሕዝብ ወክሎ በመጪው ምርጫ ለመወዳደር በምርጫ ቦርድ እውቅና ለማግኘት አስፈላጊዉን ሁሉ አሟልቶ እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ መሆኑን የሚገልፁት ዮሐንስ፣ ‹‹ክልሉ ይህንን እንቅስቃሴያችንን አስተጓጉሎታል›› ብለዋል።
የፓርቲዉ የድርጅት ኃላፊ አመንቴ ገሽ በቁጥጥር ስር የዋሉት አባሎቻቸው ለምን እንደተያዙም ሆነ ቀሪዎቹ ለምን እንደሚፈለጉ እንደማያውቁ ገልፀው፣ የተያዙት አባሎቻቸውንም መጠየቅ እንዳልቻሉ ገልፀዋል።
ጉዳዩን ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማሳወቃቸዉን ተከትሎ፣ የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ የክልሉ ፖሊስ ድርጊቱን እንዲያቆም ደብዳቤ መጻፋቸዉን በስልክ እንደነገሯቸዉ ለአዲስ ማለዳ ተናግርዋል። ‹‹ክልሉን የሚያስተዳድረዉ ገዢ ፓርቲ የድርድር ጥያቄ አቅርቦልን ባለመቀበላችን ጫና አሳድሮብናል›› ብለዋል።
ክልሉ የክልሉን አፈ ጉባኤ ሀብታሙ ታዬ እና የአገር ሽማግሌዎችን እየላከ ‹‹የፓርቲ ምሥረታውን ትታችሁ ከእኛ ጋር በአባልነት ሥሩ›› የሚል ጥያቄ ይቀርብላቸው እንደነበር ዩሐንስ ለ አዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 62 ጥር 2 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here