አግባብ ያለው የጸረ ተዋህሲያን መድሃኒቶች አጠቃቀም

0
296

ይህ መረጃ ከየጤና ወግ በጎ አድራጎት ድርጅት ጋር በመተባበር የቀረበ ነው

በ20ኛው ክፍለ ዘመን ላይ በህክምናው ዘርፍ ከተገኙት ትልልቅ ግኝቶች ውስጥ የፅረ-ተውሃስያን መድሃኒቶች ገበያ ላይ መዋል ለህክምናው ዘርፍ መጠነ ሰፊ አስተዎጾ በማበርከቱ ይታወቃል። ከዚህም ውስጥ የአሌክሳንደር ፍሌሚንግ በ1928 የነበረው የመጀመሪያው የአንቲባዮቲክ ግኝት(ፔንሲሊን)  በፈር-ቀዳጅነት ይጠቀሳል። በዚህ ምክንያት ለህክምና አና ለቀዶ ጥገና ዘርፎች ቀላል የማይባል አስተዋጾ በማበርከት ሚሊየኖችን ከበሽታ እና ከሞት መታደግ ተችሏል።

ይሁን እንጂ ከ1940`ቹ በኋላ አለም አቀፋዊ በሆነ መልኩ ቀደም ብለው በሽታ አምጪ ተህወሲያንን በመግደል ወይም እንዳይራቡ በማድረግ የተለያዩ በሽታዎችን ሲያክሙ የነበሩት መድሃኒቶች በጊዜ ሂደት ተህዋሲያኑ ባሳዩት መድሀኒትን የመላመድ ባህሪ ጥቅም አልባ ሲሆኑ ተስተውሏል። ይባስ ብሎ ደግሞ ከ1970`ቹ ጀምሮ አዲስ የሚገኙት የፀረ ተህዋሲያን መድሀኒት አይነቶች እየቀነሱ መምጣት ችግሩን የከፋ አድርጎታል።

የተህዋሲያን መድሀኒቶችን  መለማመድ ምን ማለት ነው?

በበሽታ አምጪ ተህዋሲያን አማካኝነት የሚፈጠሩ ህመሞችን ለማከምም ሆነ ለመከላከል የሚሰጡ መድሀኒቶች በቀድሞ  መጠን ወይም ከዛ በላይ በሆነ መጠን ተስጥቶ ተህዋሲያኑ የማይሞቱ ወይም መራባታቸውን የማያቆሙ ሲሆን ተህዋሲያኑ መድሀኒቱን  መቋቋም ችለዋል ወይም ተለማምደዋል ይባላል።

የባክቴሪያ መድሃኒቶችን መለማመድ (Antibiotic Resistance) ከተከሰት በኋላ ምን አይነት ጉዳቶች ሊያስከትል ይችላል?

የባክቴሪያ የአንቲባዮቲክ መድሃኒቶችን መለማመድ እና መቋቋም ከሚያመጣቸው ጉዳቶች ውስጥ የጤና እክል (ህክምናውን ጥቅም አልባ ከማድረግ እስከ ህልፈተ ህይወት)፣ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ (የህክምናውን ወጪ በማስወደድ እና የታካሚዎች የህክምና ላይ ቆይታን በመጨመር) ጥቂቶች ናቸው። የበሽታው  ጽኑነት ፣ የባክቴሪያው በሽታ አምጪነት እና  የታካሚው ለተላላፊ በሽታዎች በልዩ ሁኔታ ተጋላጭ መሆን ጉዳቱ እንዲጨምር ያደርገዋል።

ከአሁኑ ተገቢው እርምጃ ካልተወሰደ አንቲባዮቲክን የተለማመዱ ባክቴሪያዎች በሚፈጥሩት ህመም ምክንያት በ2050  የ10 ሚሊዮን ሰዎችን ህይወት በአመት እንደሚቀጠፍ እና በኢኮኖሚው ደግሞ 100.2 ትሪሊየን ዶላር ኪሳራ እንደሚያስከትል ይገመታል።

ባክቴሪያዎች  የአንቲባዮቲክ መድሃኒቶችን መለማመድን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር  ምን  ማድረግ አለበት?

እንደ ታካሚ…

  • የአንቲባዮቲክ መድሃኒቶችን የጤና ባለሙያ በሚያዝበት ጊዜ እና አግባብ ብቻ መውሰድ ።
  • መድሃኒት ተጠቅመው የሚተርፈውን ለሌሎች ሰዎች አለማጋራት። ለራስም በሌላ ጊዜ ያለ ሃኪም ትዕዛዝ አለመውሰድ።
  • እጅ በመታጠብ፣ ተላላፊ በሽታ ከተያዙ ሰዎች ጋር ቅርበት ያለው ንክኪ ባለማድረግ እና ክትባቶችን በመከተብ የኢንፌክሽኖችን ስርጭት መግታት።
  • ምግብ በንጽህና ማዘጋጀት እና ከተቻለ ደግሞ አግባብ በሌለው መልኩ አንቲባዮቲክ አየተሰጣቸው ያደጉ እንስሳትን አለመመገብ።

እንደ የጤና ባለሞያ…

  • የእጆቻቸውን፣ የምርመራ መሳሪያዎችን እና የምርመራ ክፍሎችን ንጽህና በመጠበቅ የኢንፌክሽን ስርጭትን መቀነስ።
  • አንቲባዮቲክ መድሃኒት ሲያዙ ለትክክለኛው በሽታ መድሃኒት በትክክለኛው መጠን እና ጊዜ እንዳዘዙ ማረጋገጥ።
  • የአንቲባዮቲክ መድሃኒቶችን ትክከለኛ አወሳሰድ ለታካሚዎች ማሳወቅ።
  • ስለ አንቲባዮቲክ እና ባክቴሪያ መለማመድ ግንዛቤ ማስጨበጥ።
  • ስለተላላፊ በሽታዎችና ስርጭታቸው እንዲሁም የመከላከያ መንገዶችን በበቂ ሁኔታ ማስተማር (ለምሳሌ፦ ክትባት መከተብ፣ እጅ መታጠብ፣ ሲያስነጥሱ አፍ እና አፍንጫ መሸፈን፣ጥንቃቄ ይጎደለው የግብረ-ስጋ ግንኙነት አለማድረግ )

ማጠቃለያ

ተህዋሲያን መድሀኒቶችን ለመቋቋም የሚያስችላቸው ለውጥ ማደበራቸው  አይቀሬ በመሆኑ አግባብ ያለው የፀረ ተህዋሲያን መድሀኒቶችን በመጠቀም ጉዳቱን ከወዲሁ መቀነሱ ተገቢ ነው።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here