የውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በሦስት ዓመት በአንድ ቢሊዮን ዶላር አሽቆለቆለ

0
434

በ 2009 አራት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ዶላር ሆኖ የተመዘገበው የውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንት፣ በ 2011 ወደ ሦስት ቢሊዮን መውረዱን ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ። የባንኩ ሪፖርት እንደሚያመላክተው፣ በኢትዮጵያ ፈሰስ ሲደረግ የነበረው የውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በ 2010 የ አራት መቶ ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ አሳይቶ የነበረ ሲሆን፣ በ 2011 ግን የሰባት መቶ ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ በማሳየት ከፍተኛ ማሽቆልቆል አሳይቷል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አበበ አበባየሁ እንደሚሉት፣ በ2009 ወደ አገር ውስጥ የተሳበው የውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንት አራት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ዶላር ሲሆን ይህም ኢትዮጵያ አስመዝግባው የማታውቀው ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰት ነበር። ይህም በአፍሪካ ከግብፅ ቀጥሎ ከፍተኛው የውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ሆኖ መመዝገቡን የሚናገሩት ኮሚሽነሩ፣ በቀጣይ ዓመታት ግን በአገሪቱ ባጋጠሙ የተለያዩ ችግሮች አፈፃፀሙ መቀነሱን ተናግረዋል። ባለፉት ኹለት ዓመታት በዓለም አቀፍ ደረጃ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ቅናሽ አሳይቷል፤ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ ባደረጉት የታክስ ማሻሻያ አሜሪካንን ሲያሳድግ ኢትዮጵያን ጨምሮ ያላደጉ አገሮችን መጉዳቱን አበበ በምክንያትነት ያነሳሉ።

በተመሳሳይ ወቅት በኢትዮጵያም የነበረው የፖለቲካ ሁኔታ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንቱ ፍሰት እንዲቀንስ የራሱን ድርሻ አበርክቷል የሚሉት አበበ፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ስንል ከውጭ የመጣው ኢንቨስትመንት ብቻ ሳይሆን አገር ውስጥ ኢንቨስት ያደረጉ እና አዳዲስ የማስፋፊያ ፈቃድ አውጥተው የሚሠሩትን እንደሚጨምርም ኮሚሽነሩ ይናገራሉ። ኮሚሽኑ በተለያዩ ጊዜያት ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር መግባቢያ ሰነዶችን ከተፈራረመ በኋላ በቀጥታ ወደ ሥራ ለመግባት ጊዜ የሚጠይቅ በመሆኑ፣ የራሱ ሚና እንዳለው ኮሚሽነሩ ያስረዳሉ። ለአብነት በተሽከርካሪ ኢንደስትሪ ለመሰማራት የመግባቢያ ሰነድ ከተፈራረሙት ኩባንያዎች መካከል አንዱ የሆነው ቮልስ ዋገን፣ በቀጥታ ወደ ሥራ አለመግባቱን እንደ ምሳሌ ያነሳሉ። ‹‹በጋራ የሚሠሩ ጥናቶች እና መሬትን ጨምሮ ሌሎች መሟላት ያለባቸው ነገሮች ሲዘገዩ ወደ ሥራ የመግባቱን ጉዳይ እንደሚያዘገየው ግልጽ ነው›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

‹‹የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የውጭ ምንዛሬ ችግርን ይቀርፋል። ይህ ካልሆነ ግን ኢኮኖሚው ላይ ጫና የሚያሳድር በመሆኑ መንግሥት አገር በቀል የሪፎርም ሥራዎች እየሠራ ነው። በኢንደስትሪው ዘርፍ የሚታዩ ችግሮችን ለኢንቨስትመንት ምቹ ለማድረግ የኃይል አቅርቦት ችግርን ለመፍታት ኮሚሽኑ እየሠራ ነው ሲሉም አበበ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል። በአዲሰ አበባ ዩኒቨርስቲ የምጣኔ ሃብት መምህር አጥላው ዓለሙ ‹‹ሪፖርቱን ማንም ይፋ ያድርግም አያድርግ፣ በአሁን ወቅት አስገራሚ የሚሆነው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንቱ ላይ ጭማሪ ቢታይ ነው›› ይላሉ።

‹‹ምክንያቱ ደግሞ አገሪቱ አሁን የተረጋጋች አለመሆኗ ነው። ኢትዮጵያ ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት አመቺ እና ብዙ ያልተሠራባት አገር ብትሆንም፣ ከጸጥታ ችግር በተጨማሪ አገሪቱ ባለባት የእዳ ጫና ምክንያት በባለሃብቶች ላይ ግብር የመቆለል አዝማሚያዎች ስላሉ፤ ይህም የውጪ ባለሃብቶች እንዲፈሩ ያደርጋቸዋል።›› ሲሉ አክለዋል። መንግሥት የጸጥታ ሥራውን በሚገባ መሥራት አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነው የሚሉት አጥላው፣ ከቃል ይልቅ ሥራዎች ላይ ማተኮር አስፈላጊ መሆኑንም ይናገራሉ።

የዓለም ባንክ መረጃ እንደሚያሳየው፣ በአፍሪካ ከሰሃራ በታች ያሉ አገራት መዋዕለ ነዋይን ለማፍሰስ አመቺ ባለመሆናቸው የኃይል አቅርቦት ችግሮች መሻሻል አላሳዩም። ይሁን እንጂ እንደ ናይጄሪያ እና ኬንያ ያሉ አገራት የውጭ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ ለውጥ ያሳዩ ናቸው ብሏል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here