ሕዝብ ገንዘብ እንዲያዘንብ ጨምቆ መያዝ ይቁም!

0
992

የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ከበፊቱ የበለጠ ገንዘብ ለመሰብሰብ የሚያደርጉት ጥረት ከተለያየ አንጻር የቃኙት ተወዳጅ ስንታየሁ፣ ሕዝብን አስጨንቆ ገንዘብ የመሰብሰብ እሳቤ መነሻ ኢሕአዴግን እጠላዋለሁ ሲል ወደ ቆየው ርዕዮተ ዓለም ይገፉታል ይላሉ። ይህም እንቅስቃሴ የሕዝቡን ኑሮ እያከበደው የሚሄድ መሆኑን ጠቁመው፣ በዚህ ላይ ለአገር ደኅንነትም ሊታሰብ ይገባል ሲሉ ያሳስባሉ።

በዚህ ሳምንት በአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ላይ ትራፊኮች በከፍተኛ ቁጥር ተመው በአዲሱ ሕግ መሠረት ከአሽከርካሪው ጎን ባለው ወንበር ላይ ተቀምጠው የደኅንነት ቀበቶ ያላሠሩ ተሳፋሪዎች የያዙ አሽከርካሪዎችን በብዛት ሲቀጡ ታይተዋል። ድርጊቱ እንደ ዘመቻ የተደረገ የሚመስል ይዘት ነበረው። በሂደቱም እያንዳንዱ አሽከርካሪ 250 ብር ተቀጥቷል። ይህ እንግዲህ አሁን አሁን እንደ ድል እየተቆጠረ የተቋማትን ብቃት መለኪያ እየሆነ የመጣው የተሰበሰበ ገንዘብን ማናሪያ ዘዴ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።

የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ከበፊቱ የበለጠ ገንዘብ ለመሰብሰብ የሚያደርጉት ጥረት የሕዝብን የኑሮ ሁኔታ እያከበደው እንደሚገኝ በቀላሉ በመብራት ኃይል አቅርቦት ላይ የተደረገውን ጭማሪ እና የሕዝብን ሮሮ ከግምት በመክተት መረዳት ይቻላል። የነዳጅ ዋጋ በዓለም ገበያ በበርሜል ከ40 የአሜሪካ ዶላር በታች ሆኖ ከዓመት በላይ በቆየበት ጊዜ እንኳን እዚህ ግባ የሚባል ቅናሽ ያልታየበት የነዳጅ ዋጋ ትንሽ ጭማሪ ሲታይ ግን ለመጨመር ያን ያህል ጊዜ አይፈጅም። በትራንስፖርት ዋጋ ላይ እየታየ ያለው ጭማሪም የዚሁ ውጤት ነው።

የዚህ ሕዝብ ገንዘብ እስኪዘንበው ጨምቆ የመያዝ እሳቤ መነሻ ሊሆኑ የሚችሉት አስተሳሰቦች ደግሞ ሥልጣን ላይ የቆየውን ኢሕአዴግን ከአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ዘለል ባለ መንገድ እስከ ቀብሩ ድረስ እጠላዋለሁ ሲል ወደ ቆየው ርዕዮተ ዓለም ይገፉታል።

በሕወኀት መራሹ ኢሕአዴግ ዘመን እንደ ጭራቅ ከተሳሉ ብዙ ነገሮች መካከል ኒዮሊብራሊዝም አንዱ ነው። ከውልደቱ ጀምሮ ሶሻሊዝምን አንግቦ የነበረው ነጻነትን ገፋፊ ሆኖ ወደ ተቃዋሚነት ራሱን ያወረደው ሕውኀት፣ የፈለፈላቸው የአሻንጉሊት እህት ድርጅቶቹ ነፍስ ዘርተው ፈጣሪያቸውን በል (ፈረንጆቹ ፍራንከንስታይን እንደሚሉት) እስኪሆኑበት ድረስ እየተቀየረ ከሔደው የዓለም የፖለቲካ እና ኢኮኖሚ እሳቤ ጋር ራሱን ለማራመድም ሞክሯል። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የምንከተለው ነጭ ካፒታሊዝም ነው ብለው ለፓርቲ አባሎቻቸው ዱብዳ መጣላቸው የሚዘነጋ አይደለም።

ትላልቅ የመንግሥት የግንባታ ፕሮጀክቶችን እንደ እድገት ማምጫ መንገድ አድርጎ ለያዘው የኢሕአዴግ መንግሥት ይህ እውን ሊሆን የሚችለው በዓለም አበዳሪ አካላት ከፍተኛ ትብብር ነበር። በመሆኑም የቻይና የገቢና የወጪ ንግድ ባንክ እንዲሁም የተለምዶ ተጠርጣሪዎቹ የዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አገሪቷን በብድራቸው በመሠረተ ልማት ሊገነቡ ፈጥነው ተገኙ። በተለይ የመጨረሻዎቹ ኹለቱ በምዕራባውያን የሚመሩ ድርጅቶች የታወቁትን የኒዮሊብራል ፖሊሲዎቻቸው ተቀባይነት አግኝተው እንዲተገበሩ ደፋ ቀና አሉ።

ይህ ሶሻሊዝምን አምኖ ሕይወቱን ሊሰጥ ከነበረ፣ ጓዶቹን ላጣ እና ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር ለተገዳደለ ቡድን በቀላሉ የሚዋጥ አልነበረም። በመሆኑም መለስ ዜናዊ እነዚህን ዓይነት ነገሮችን ይቃወሙ እንደነበር በሰፊው ከመነገሩም በላይ፣ ወደ ቻይና ዐይናቸውን የጣሉበትም ምክንያት ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል። ይሄ ሁሉ አካሔድ ግን እነዚያን ኒዮሊብራል ፖሊሲዎች ምዕራብ ዘመም ከሆነው ዓለም አቀፍ ኃይል ተቀብለው ተግባራዊ ማድረጋቸው አልቀረም።

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ብድር ሲሰጥ ከሚያስቀምጣቸው የፖሊሲ መስፈርቶች መካከል ማኅበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ወደ ግል ማዞር፣ የገንዘብ የመግዛት አቅምን ማዳከም፣ ለየዘርፉ የሚደረጉ ድጎማዎችን ማቆም፣ የኢኮኖሚ ዘርፎችን ለውጭ ባለሃብቶች ክፍት ማድረግ፣ ውጪ ንግድን ማስፋፋት፣ ታክስ የመሰብሰብ አቅምን መጨመር፣ መሠረተ ልማትን ማስፋፋት የሚሉት ዋነኞቹ ናቸው።

በኢትዮጵያ ባለፉት ኻያ ዓመታት የተካሄዱትን ነገሮች ብናይ፣ የመንግሥት ተቋማትን ወደ ግል ማዞር በሰፊው እንደተሠራበት መገንዘብ እንችላለን። ከታኅሳስ 2010 በፊት ባሉት 20 ዓመታት ውስጥ 377 የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በ47 ቢሊዮን ብር ወደ ግል እንደዞሩ የኢትዮጵያ ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ገልጾ ነበር። የገንዘብ የመግዛት አቅምን ስናይ ደግሞ ኢሕአዴግ ሥልጣን ላይ ሲወጣ 2.07 ብር የነበረው የአንድ ዶላር ምንዛሬ ዛሬ 33 የደረሰ ሲሆን በቅርቡ 44 ድረስ ከፍ እንደሚል ይጠበቃል።

ነዳጅ እና ሌሎች ድጎማ የሚደረግባቸው ምርቶች ላይ ይደረግ የነበረው ድጎማ በአብዛኛው መነሳቱ አሁን ውሉ የጠፋውን የኑሮ ውድነት ካባባሱት ውሳኔዎች መካከል የሚጠቀስ ነው። የነጻ ገበያ መታወጅ እና የአገሪቱን ገበያ ለወጭ ባለሃብቶች ለመክፈት (ከጥቂት እንደ ባንክ ያሉ ዘርፎች ውጪ) የተወሰዱ እርምጃዎች  የኢኮኖሚ ተፅዕኖም ጉልህ ነው።

ውጪ ንግድን ማስፋፋት፣ ታክስ የመሰብሰብ አቅምን መጨመር እና መሠረተ ልማትን ማስፋፋት ደግሞ በአገሪቱ አምስት ዓመት መርሃ ግብሮች ውስጥ ዋና የልማት ፖሊሲ አቅጣጫ ሆነው ባለፉት ኻያ ዓመታት ወደ ፊት መምጣታቸው እነዚህን እርምጃዎች ዓለም አቀፎቹ የገንዘብ ተቋማት በዚህ ጊዜ ካደረጉት ግፊት ጋር የሚገጣጠም ነው። ዓለም አቀፍ ድርጅቶቹ የውጪ ንግድን ማስፋፋትን የሚያበረታቱበት ዋነኛው ዓላማ ከፍተኛ ገንዘብ አዋጪዎችና መሪዎች የሆኑት የበለፀጉት አገሮች በውጪ ንግድ መልክ ጥሬ እቃዎች በዓለም ገበያ ላይ በስፋት ከቀረቡ ዋጋቸው ዝቅ ብሎ ድርጅቶቻቸው ስለሚያገኟቸው ይህንን ለማመቻቸት ነው።

ታክስ የመሰብሰብ አቅምን መጨመር ደግሞ ብድርን የመክፈል እድልን ከፍ ከማድረጉም በተጨማሪ የመደበኛውን ኢኮኖሚ በማጠናከር በቀላሉ በዓለም አቀፍ አሠራሮች ጫና ስር እንዲወድቅ እድል የከፍታል። መሠረተ ልማትን ማስፋፋት ደግሞ እንደ ባንክ እና ሌሎች የከተማ ሕይወት አካል የሆኑ ተቋማትን እና አሠራሮችን ለሁሉም ሕዝብ ተደራሽ በማድረግ በተዘዋዋሪ የዓለም አቀፍ ድርጅቶቹ ተጽኖ ስር በተሻለ እንዲወድቁ ይጋብዛል።

ኒዮሊብራሊዝም ውድድርን እንደ ሰው ልጆች ዋነኛ መገለጫ ባሕሪይ የሚያይ ርዕዩተ ዓለም ሲሆን ይህ ባሕሪይ በዴሞክራሲያዊ ሁኔታ የሚገለፀው በመግዛት እና በመሸጥ እንደሆነ ይደነግጋል። ውድድርን መገደብ የሰው ልጅን ነጻነት እንደመገደብ አድርጎም ከመውሰዱ ባሻገር ዜጎችን እንደ ሸማች አድርጎ የሚመለከት ነው።

በመንግሥት አገልግሎት ተቋማት (ቀበሌ፣ ጤና ጣቢያ፣ የተለያዩ ቢሮዎች) የምንመለከተው ተገልጋዮችን ለተለያዩ አገልግሎቶች ሰበብ እየፈለጉ የማስከፈል አዝማሚያ ሕዝብን እንደ ሸማች አድርጎ የመመልከት ውጤት ነው። ሕዝብ ታክስ በመክፈሉ ከመንግሥት በዜግነት የሚያገኛቸው አገልግሎቶች እጅጉን ቀንሰዋል። በዚህ ረገድ በጉልህ የሚጠቀሱት የትምህርት እና የጤና አገልግሎቶች እንኳን በእኛ አገር በጥቂቱ ብቻ ነው በነጻ የሚገኙት።

የከፍተኛ ትምህርት እና የጤና አገልግሎት ክፍያን እንደዋቢ ማንሳት ይቻላል። ከዚያ በተጨማሪ ውሃ እና የመብራት ኃይል አገልግሎትን የመሳሰሉት አገልግሎቶች ደግሞ በተጨማሪ ክፍያ እንኳን አሉ ለማለት እስኪከብድ ተዳክመዋል። በደኅንነት መኖር የማይቻልበት ሁኔታ እየተፈጠረ መምጣቱ ሲታሰብ ደግሞ፣ መንግሥት በታክሱ ምን እየሠራ እንዳለ ጥያቄ የሚያስነሳ ይሆናል።

ይህ እሳቤ በመንግሥት ደረጃ እየሰረጸ ሲሔድ ደግሞ የሕዝብንም አመለካከት መበረዙ አልቀረም። በእየመኖሪያ ሰፈሩ የሚገኙ የነዋሪዎች ማኅበሮች እንኳን ከአባላቶቻቸው የሚቻላቸውን ገንዘብ መሰብሰብ እንዳለባቸው እንጂ አባላቱን አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸው የሚያስቡ አይደሉም። በተለያዩ ጊዜያት አጥር ለማሰሪያ፣ ለመንገድ ንጣፍ፣ ለመብራት እና ለሌሎችም ጉዳዮች የሚጠይቋቸው በሺዎች የሚቆጠሩ መዋጮዎች የሕዝብን አቅም ያገናዘቡ ናቸው ለማለት ይከብዳል። በዚህ ላይ በአከራይ ስሜት ላይ የተመረኮዘው የቤት ኪራይ ጭማሪ፣ ከታሪፍ በላይ የሆነ የትራንስፖርት ክፍያ እና የነጋዴ ፈጣሪን ያለመፍራት ሲደመር ሕዝብ ገንዘብ ማንጠባጠቡን እንዳያቆም ተደርጎ ከሁሉም አቅጣጫ እንደተጨመቀ ያሳያል።

ከላይ ለመዳሰስ የተሞከሩት የኢሕአዴግ ፖሊሲዎች እና የተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ከኒዮሊብራል አስተሳሰቦች የተቀዱ መሆን ከለውጡ ወደዚህ ባለው ጊዜ በታየው ይበልጥ ሊብራል የሆነ አካሔድ በአብዛኛው ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቋሚ ነው። በለውጡ መንግሥት ከኒዮሊብራል አስተሳሰብ ጋር የማይሔደው ተግባር የታክስ ጭማሪ ነው።

ኒዮሊብራሎች ታክስ እንዲቀንስ እና በአጠቃላይ መንግሥት መጠኑ አንሶ ተቆጣጣሪ እና አሸማጋይ እንዲሆን የሚመክሩ ናቸው። ነገር ግን የቀድሞው ኢሕአዴግም ሆነ ከእርሱ ወጥቶ እርሱን በልቶ ሌላ ማንነት የያዘው መንግሥት በአናሳ መንግሥት የማያምኑ መሆን ለዚህ እንደምክንያትነት ሊነሳ ይችላል።

የዚህ ርዕዮተ ዓለምን እና ከእርሱ የሚመነጩ ፖሊሲዎችና ተግባራትን በንቃት ጠንቅቆ ያለመለየት ችግር ዋነኛ ተጠቂ እየሆነ ያለው ሕዝብ ነው። በመሆኑም ይህ የሚያደርገውን ነገር በቅጡ ያለማወቅ ችግር የሚታይበት መንግሥት ሁኔታዎችን የሚያባብሱ ትላልቅ እርምጃዎችን ምርጫው እንዲጠናቀቅ ከመውሰድ መቆጠብ አለበት። እስከዚያው ግን ሕዝብን ጨምቀው ትንፋሽ ያሳጡትን እርምጃዎች ግምት ውስጥ አስገብቶ መሔዱ ለአገር ደኅንነትም ወሳኝ ነው።

ተወዳጅ ስንታየሁ minitew2@gmail.com

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here