ከማይዳሰሱ ቅርሶች ምዝገባ በስተጀርባ – ያልተዘመረላቸው ባለሙያ

0
1193

ከነገ ጥር 10/2012 ከተራ ጀምሮ በማግስቱ የጥምቀት በዓል የጊዙ ዑደቱን ጠብቀው ደርሰዋል። የዘንድሮው ጥምቀት ታድያ ከወትሮው ለየት የሚያደርገው አንድ ጉዳይ አለ፤ ይህም በዓሉ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት ዩኒስኮ ላይ በሰው ልጆች ወካይ ዓለማቀፍ ቅርስነት መመዝገቡ ነው። ዩኔስኮ የማይዳሰሱ ቅርሶችን መመዝገብ የጀመረው በአውሮፓውያን አቆጣጠር በ2003 ጀምሮ ሲሆን፣ ኢትዮጵያም ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በመስቀል በዓል፣ የሲዳማ ፊቼ ጫምባላላ፣ የኦሮሞ የገዳ ስርዓትን እንዲሁም አሁን ደግሞ ለአራተኛ ጊዜ የጥምቀት በዓልን ማስመዝገብ ችላለች። ይህን ምዝገባ ስናነሳ ደግሞ የአንድን ሰው ስም አለማንሳት ያስቸግራል፤ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሞያውን ገዛኸኝ ግርማ።

ትውልድና እድገታቸው አዲስ አበባ ነው። የመጀመሪያና ኹለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አዲስ ከተማ ተከታትለዋል። አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በታሪክ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከያዙ በኋላ በመምህርነት አገልግለዋል። መጀመሪያ በብሔራዊ ቤተመጻፍትና ቤተመዛግብት ኤጀንሲ፣ ቀጥሎ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ካገለገሉ በኋላ ወደ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ተዘዋውረዋል። በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሆነው ኹለተኛ ዲግሪያቸው በባህል አንትሮፖሎጂ አግኝተዋል።

እኚህ ብርቱና ታታሪ ስብእና ያላቸው ባለሞያ፣ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣንን ከተቀላቀሉ በኋላ በተመደቡበት የቅርስ ማስመዝገብ ሥራ ላይ ከጅመሩ አንስቶ እስከሁን በስኬት ተራምደዋል። ሥራው ሲጀመር አብረዋቸው የነበሩ ሰዎች ገሸሽ ካም በኋላ እርሳቸው በጽናት እያገለገሉ ተገኝተዋል። የዘንድሮን ጥምቀት የሚያከብሩ ሁሉ፣ በዓሉና አከባበሩ በዓለም የማይዳሰሱ ቅርሶች መዝገብ ላይ ሰፍሯልና፣ እኚህን ባለውለታ ሊዘነጉ አይገባም። የአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬም የጥምቀትን ምዝገባ ሂደትናተያያዥ ጉዳዮችን በማንሳት ከገዛኸኝ ግርማ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጋለች።

የጥምቀት በዓል የምዝገባ ሂደት ምን ይመስል ነበር?

የጥምቀት በዓል በሰው ልጆች ወካይ ዓለማቀፍ ቅርስነት እንዲመዘገብ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን በተለያዩ ኅብረተሰብ ክፍሎች በተደጋጋሚ ለቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ጥያቄ ሲቀርብ ነበር። ለዚህ ምላሽ ለመስጠት አንድን ቅርስ ለማስመዝገብ ለቅርሱ የማስመረጫ ሰነድ ተዘጋጅቶ ለዩኔስኮ መላክ አለበት። ስለዚህ የመጀመሪያ ሥራችን ጥር 2009 የጥምቀት በዓል አከባበሩን ለማስመዝገብ የሚያስችል የማስመረጫ ሰነድ ዝግጅት ተጀመረ።

ሰነዱን ለማዘጋጀት የቪድዮ፣ የፎቶ፣ የቃለመጠይቅ የጽሑፍ መረጃዎች ያስፈልጋሉ። እነዚህን ለማግኘት በመላው ኢትዮጵያ በተለይ በጎንደር፣ አክሱም፣ ላሊበለ እና አዲስ በአባ ጃንሜዳ እንዲሁም ዝዋይና ሌሎችም በዓሉ በደማቅ ሁኔታ ከሚከበርባቸው አካባቢዎች እነዚህን ወሳኝ መረጃዎች ማሰባሰብ በሰፊው ሲከናወን ቆየ።

እነዚህን መረጃዎች ካገኘን በኋላ ወደ እነሱ ቋንቋ መተርጎም፣ ማጠናቀርና መተንተን ተካሄደ። ከዛ በኋላ በማስመረጫ ሰነዶች የሚካተቱ አምስት ጉዳዮች አሉ። በአንደኛው ቅጽ ስለ ጥምቀት አከባበር ሰፊ መረጃ ሰጠን። ለምሳሌ ስለምንነቱ፣ ታሪካዊ አመጣጡ፣ የአከባበር ሂደቱ፣ ለማኅበረሰብ የሚያበረክተው ፋይዳ፣ ከትውልድ ትውልድ እያንዳንዱ የራሱን ፈጠራ እያከለበት እንዴት እያስተላለፈው እንደመጣ (ለምሳሌ የአሁኑ ትውልድ እንደሚታየው ታቦታት ሲያልፉ ምንጣፍ የማንጠፍ፣ የማጽዳትና አካባቢን የማስዋብ እንቅስቃሴን አክሏል) በዓሉ እንዲሁ እየተከበረ የመጣ አይደለም። ሃይማኖታዊ ቀኖናው ተጠብቆ ግን አዳዲስ ነገሮች እየታከሉበት ስለሆነ በዚህ ላይ ሰፊ መረጃ ሰጠን። ባለቤቱ ማን እንደሆነ፣ ስጋት ቢያጋጥመው ምን መደረግ እንዳለበት፣ የጥበቃ መርሃ ግብር ሁኔታዎች በዚህ ሰነድ ተካተተ።

ቀጥሎ ስለ በዓሉ አከባበር ምንነት ለዓለም ሕዝብ የሚያስተዋውቅ የሃይማኖት አባቶችን፣ የቅርስ ባለቤቶችን ተሳትፎ የሚያሳይ የዐስር ደቂቃ ዘጋቢ ፊልም በኢንግሊዘኛ ተዘጋጀ። ከአከባበሩ ጋር ተዛምዶ ያላቸው ዐስር ፎቶዎች በተቀመጡ መስፈርቶች መሠረት ተመርጠው መግለጫ/ካፕሽን ተሰጠ።

ሌላው የጥምቀት በዓል አከባበር በኢትዮጵያ ደረጃ ቅርስ ሆኖ መመዝገቡን የሚያሳይ ሰነድ በኢንግሊዘኛና አማርኛ ቋንቋ ተዘጋጀ። ሌላው በሂደቱ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ ከፍተኛ መሆን አለበት። ለዚህም ኅብረተሰቡ በዓሉ የማንነቴ መገለጫ ነው፣ ጠቀሜታ ይሰጠኛል ብሎ አከባበሩ እንዲመዘገብለት ጥያቄውን በጽሑፍ ያቀረበበት ሂደት ነበር።

ሰነዱ በዚህ ሁኔታ ተዘጋጅቶ መጋቢት 2010 ከተጠናቀቀ በኋላ ለሃይማኖት አባቶች፣ ለዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት ለአስተያየት ቀርቦ በተሰጠው ግብዓት መሠረት ሰነዱ ከዳበር በኋላ፣ ፓሪስ ለሚገኘው የዩኔስኮ ጽሕፈት ቤት ተላከ። ሰነዱ የተሟላ በመሆኑን ካሳወቅን በኋላ፣ ዩኒስኮ በጠቅላላ የተካተቱትን በድረ ገጹ ላይ በመልቀቅ ለሕዝብ አስተያየት ክፍት አደረገ።

ቀጥሎ የዩኔስኮ ማስመረጫ ሰነዶች ገምጋሚ አካል ያሉትን አምስት መስፈርቶች ማሟላት አለማሟላቱን ሲገመግም ቆይቶ ረቂቅ ውሳኔውን አስተላለፈ። አከባበሩን በተመለከተ የተላለፈው ረቂቅ ውሳኔ ላይ የጥምቀት በዓል ማስመረጫ ሰነድ መስፈረት አንድ፣ አራትና አምስትን ሙሉ ለሙሉ ያሟላ መሆኑን፣ መስፈርት ኹለትና ሦስት ላይ ግን አልተሟሉም ያሉትን ጠቅሶ ማብራሪያና አሳማኝ መከራከሪያ ነጥብ እንዲቀርብ ጠየቀ።

ገምጋሚው አካል ያቀረበውን ረቂቅ ውሳኔ ተመልክቶ የመጨረሻ ውሳኔ የሚሰጠው የማይዳሰሱ ቅርሶች ጥበቃ የበይነ መንግሥታት ኮሚቴ ነው። ይህ ኮሚቴ ከጠቅላው 24 ተመራጭ አባላት ያሉት በየ4 ዓመቱ የሚለወጥ ነው። በየዓመቱ ስብሰባዎችን ያካሂዳል፤ የግምገማ ውሳኔ ይሰጣል። ዘንድሮም በኮሎምቢያ ዋና ከተማ ቦጎታ ላይ 14 ኛውን ጉባኤ አካሂዷል። ኢትዮጵያ በዚህ ጉባኤ አልተሟሉም በተባሉት ጥያቄዎች በቂ ምላሽና አሳማኝ መከራከሪያ ነጥብ ይዛ ቀርባለች።

ምንድን ነበሩ አልተሟሉም የተባሉት ነጥቦች?

የጥምቀት በዓልን ለማስመዝገብ ከተዘጋጀው የማስመረጫ ሰነድ መስፈርት ኹለት ላይ፤ ኢትዮጵያ የጥምቀት በዓል መመዝገብ ለሌሎች የማይዳሰሱ ቅርሶች ህልውና ቀጣይነትና ጠቀሜታቸውን ከማስተዋወቅ አንጻር የሚያበረክተው አስተዋጽኦ በአጥጋቢ ሁኔታ አልቀረበም የሚል ነበር፤ እንደጉድለት የታየው።

በዚህ ላይ ኢትዮጵያ በሰጠችው ምላሽ፣ የጥምቀት በዓል መመዝገብ ከአከባበሩ ጋር የተያያዙ እሴቶችና ጠቀሜታዎችን ሌሎች ሕዝቦች ልምድ እንዲቀስሙ፣ ቅርሶቻቸውን እንዲጠብቁና እንዲያስተዋውቁ የሚያበረታታ መሆኑን በማስመረጫ ሰነዱ ላይ ተገልጿል ብላ ተከራክራለች።

ሦስተኛው መስፈርት ላይ ደግሞ ከመመዝቡ ጋር ተያይዞ ከሚያገኘው እውቅና ጋር በተገናኘ በቀጣይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ቱሪስት ይመጣል፤ የቱሪስት መስህብም ይሆናል። እናም ከቱሪዝም ፍሰት መጨመር ጋር የሚገናኝ የቅርሱን ህልውና ለስጋት የሚዳርጉ ክስተቶችና አጋጣሚዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ያንን ለመቆጣጠር ለመከታተል የሚያስችል ስልት አላስቀመጠችም የሚል ነው።

በእኛ በኩል በተሰጠው ምላሽ ጥምቀት በዓል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን፣ የባህልና ቱሪዝም ቢሮዎች፣ ኅብረተሰቡ በቅንጅት ሆነው የሚመሩትና የሚቆጣጠሩት በመሆኑ ቱሪስቶች በበዓል አከባበሩ ላይ የሚያደርሱት አሉታዊ ተጽእኖ ካለ ያንን መቆጣጠር የሚያስችል መርህ ግብር የተቀረጸ መሆኑን ጠቀስን። አንዱ መንገድ የኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ከቱሪዝም ቢሮዎች ጋር በመሆን የምትቆጣጠርበት ነው።

ሌላው በዚሁ ቱሪስቶችን ከሚያስተናግዱ ሆቴሎች፣ አስጎብኚ ድርጅቶች ጋር በመሆን አሁንም ተሪስቶች ቅርስ ላይ የሚያስከትሉት አሉታዊ ተጽእኖ ካለ፣ ያንን ለመቆጣጠር በቀጣይ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ፤ ያም በሰነዱም ላይ እንደተጠቀሰ አንስታ ኢትዮጵያ ተከራክራለች።

እንግዲህ መጨረሻ ውሳኔ የሚሰጠው የማይዳሱ ቅርሶች ጥበቃ በይነ መንግሥታት ኮሚቴ አባላት ሰፊ ውይይትና ክርክር ካደረጉ በኋላ አዎንታዊ አስተያየት በመስጠታቸው፤ ታኅሳስ 1 ቀን 2012 በሰው ልጆች ወካይ ዓለም አቀፍ ቅርስነት ሊመዘገብ ችሏል።

ኢትዮጵያ የኮሚቴውን አባላት ድጋፍ እንድታገኝ ከውጪ ጉዳይ ሚኒስቴርና በዩኔስኮ የኢትዮጵያ ቋሚ መልእክተኛ ጋር በትብብር ተሠርቷል፤ ድጋፍ እንዲሰጡ ለማድረግ። ጥያቄው ራሱ ከመከራከራችን በፊት የሚቀርብልን ከኮሚቴ አባል አገራት በአንዱ ነው። ያ አባል አገር ኢትዮጵያ የጥምቀት አከባበርን በሚመለከት እንዲህ ዓይነት ማብራሪያ ማቅረብ ፈልጋለች፤ አሳማኝ መከራከሪያ አቀርባለሁ ብላለች ብሎ ለኮሚቴው አመራር የሚያቀርበው የኮሚቴው አባል ነው።

ለዚህም የኮሚቴው አባል ናትና ጅቡቲ እንድታቀርብ ተደረገ። ሌሎች እንደ ሴኔጋል፣ ሞርሺስ፣ አዘርባጃን፣ ፊሊፒንስ፣ ኩዌት፣ የመሳሰሉ አገራትም እርሷን ደገፉ።

እናም በዚህ ሁኔታ እኛም ሐሳቡን ካቀረብን በኋላ ከፍተኛ ውይይትና ክርክር ነበር። ምክንያቱም በሰነዱ ላይ ከመርህ ያፈነገጡ አንዳንድ ሐሳቦችና የቃላት አጠቃቀሞች ተስተውለዋል የሚል ነው። የሴቶች ተሳትፎም ጎልቶ አልወጣም የሚል ሐሳብ ሲቀርብ ቆይቷል። በመጨረሻ ቅርሱ መመዝገብ ያለበት ለየት ያለ ቅርስ ስለሆነ ነው በሚል፤ የተሰጠው ምላሽም ገምጋሚው አካል ያቀረበውን ጥያቄ የመለሰ ስለሆነ ይመዝገብ ተብሎ ውሳኔው ተላለፈ።

በሁሉም የማይዳሰሱ ቅርሶች ምዝገባ ላይ ትልቁን ሥራ ሠርተዋል። የትኛው ከባድ ነበር?

ሥራው ከባድ ነው፤ ፈታኝም ነው። የመስቀል በዓል እንደ አዲስ ነው የጀመርነው፤ ልምድም አልነበረም። የገዳ ስርዓትን ራሱ ማስመዝገብ በጣም ከባድ ሂደት ነበር። የሚቃወሙ ቡድኖች ነበሩ፤ መመዝገብ የለበትም ብለው ለዩኔስኮ ክስ ያቀረቡም ነበሩ። ለዛ አሳማኝ ምላሽ ማቅረብ አስፈልጎናል። የጥምቀትም እንደዛው ነው። ግን ልምድ እየተገኘ ሲመጣ ያንን መጠቀም ስላለ ክብደቱ ይቀንሳል። ስለሚዳሰሱ ቅርሶች ምዝገባ ግን በዝርዝር ማንሳትና ማነጻጸር አልችልም።

ግን በጥቅሉ ቀላል አይደለም፤ ከባድ ነው። እንዲህ ዓይነት ነገሮች ላይ ራስን አሳልፎ ሰጥቶ የማይሠራ ከሆነ አስቸጋሪ ነው። እንደ ቢሮ ሥራ ነካ ነካ ተደርጎ የሚተው አይደለም። ርብርብና መሰጠት የሚያስፈልገው ሥራ ነው።

ብዙዎች ቅርሶችን በተለይም የሚታወቁትን የማስመዝገቡ ዓላማ ምንድን ነው ብለው ይጠይቃሉ። ምን ጥቅም አለው ቅርሶች በዩኔስኮ መመዝገባቸው?

የማስመዝገብ ዓላማ ለቅርሶቹ የተሻለ ጥብቃና እንክብካቤ እንዲደረግ ነው። ከቅርሶቹ ጋር የተያያዙ እሴቶችና ጠቀሜታዎችም አሉ። ለምሳሌ ጥምቀት በዓል ላይ የተለያዩ ኅብረተሰብ አካላት የሚጠያየቁበት፣ የሚረዳዱበት፣ ወጣቶች የሚተጫጩበት ነው። የተለያዩ ባህላዊ ዘፈኖች ይከወናሉ፣ ሕዝቦች አንድ ላይ ይሆናሉ። ሕዝብን ከማቀራረብና ከማስተዋወቅ፤ ለሰላም ለፍቅርና ለእርቅ እንዲሁም ለአንድነት ትልቅ አስተዋጽኦ ያላቸው ናቸው፤ እነዚህ ቅርሶች። መመዝገቡ እነዚህን ፋይዳዎች አጠናክሮ ለመስቀጠል ያስችላል።

ሌላው ወጣቱ ትውልድ የተመዘገበውን ቅርስ ለማወቅ፣ እንዲሁም ለመሳተፍ ጉጉት ያድርበታል። በትውልድ ቅብብል የደረጁ ክህሎቶችን፣ እውቀቶችን ለወጣቱ ለማስተላለፍ ያግዛል። መንግሥትም ሕዝብም እያደረጉ ያሉትን ጥረት ያግዛል። አሁን በሚድያ ብዙ ሽፋን የተሰጠውም ስለተመዘገበ ነው። ስለ በዓሉና ስለ ቅርሱ ሰፊ ግንዛቤ ኅብረተሰቡ በተለይ ወጣቱ እንዲኖረው ያደርጋል። ቅርሱም ከትውልድ ትውልድ ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ እንዲተላለፍ ያግዛል። የአገራችንን መልካም ገጽታም ይገነባል።

የተዘጋጁ ሰነዶች በዩኔስኮ ድረ ገጽና ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኀን ይለቀቃሉ። በዚህም ምክንያት ቱሪስቶችና ተመራማሪዎችን ወደ አገር ይስባል። የዓለም ሕዝቦች ቅርስ ሲሆን፣ መንግሥትም ሕዝብም ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንዲጠብቅ፣ እንዲንከባከብና ለትውልድ እንዲያስተላልፍ ይረዳል።

ለውጦችም እያየን ነው። አንደኛ በቱሪስት ፍሰቱ። መስቀል በፊትም ቢኖርም የበለጠ በዓለም ደረጃ ሲተዋወቅ ትልቅ ተጽእኖ ይኖረዋል። ምዝገባ ሥነ ስርዓቱ ላይ እንኳን ደስ አላችሁ ያላለን አባል አገር የለም። የነበረውን ትግል አይተዋል፤ ቅርሱም ታዋቂ ነው። አንዳንዶች መጥተው ያዩ አሉና ስብሰባው እስኪረበሽና እረፉ እስኪባል ድረስ ደስታቸውን ሲገልጹን ነበር። እነርሱም ለሌሎች አስተዋውቀው ቱሪስቶች ወደ አገር እንዲመጡና እንድንጠቀም የሚያደርግ ነው።

እርሶ በዚህ ላይ ገፍተው እንዲሠሩ የደረገዎ ምን ይሆን?

በ2003 በአውሮፓውያን አቆጣጠር የማይዳሰሱ ቅርሶች ጥበቃ ስምምነት አጸደቀ፤ ዩኔስኮ። ያ ለማይዳሰሱ ቅርሶች ጥበቃ ትልቅ አስተዋጽኦ ነው። እያንዳንዱ አገር ትኩረት ተሰጥቶ በአገሩ ያሉ ቅርሶችን እንዲመዘግብ፣ እንዲጠብቅ፣ እንዲያስተዋውቅ አስችሏል። አሁን ማስመዘግቡም የዛ አካል ነው። ቅርሶች በአገር አቀፍ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም ታውቀው ጥበቃ እንዲደረግላቸው ነው ስምምነቱ የወጣው።

ከሦስት ዓመት በኋላ በእኛ አቆጣጠር በ1998 ኢትዮጵያ ተቀብላ አጸደቀች። ይህ ትልቅ እርምጃ ነበር። እኔ ሲጸድቅ አካባቢ ነው ወዲዚህ መሥሪያ ቤት የመጣሁት። ከዛ ምን ምን የማይዳሰሱ ቅርሶች አሉን የሚለውን ማሰባሰብ ተጀመረ። ከደቡብ ክልል ነው የተጀመረው። ‹አንትሪፖሊጂ መምሪያ› የሚባል ክፍል ያኔ ነበር፤ በክፍሉ ያሉ ባለሞያዎች ተጀመረ። እኔ እንደውም ከአንድ መስክ በኋላ ነው የተቀላቀልኩት። ከዛ በኋላ እኔም እያለሁ ወደ 45 ብሔረሰቦች በተለይ ደቡብና ቤኒሻንጉል ሄደን ምን ምን አለ የሚለውን አይተናል።

በዚህ ስምምነት መሠረት አምስት የማይዳሰሱ ቅርሶች ምድቦች አሉ። አፋዊ ትውፊት፣ ማኅበራዊ ክዋኔና ስነስርዓቶች፣ ትውፊታዊ እደጥበባት፣ አገር በቀል እውቀቶች (ስለተፈጥሮና የዓለም አፈጣጠር ማኅበረሰብ ያለው እውቀት) እና ክውን ጥበባት ናቸው። በዚህ በእያንዳንዱ ምድብ ምን ቅርሶች አሉን የሚለውን አየን።

ይህን ሠርተን፤ ያኔ አዲስ አወቃቀር እየተሠራ ነበርና በአዲስ መልክ ክፍሎች ሲዋቀሩ፣ የማይዳሰሱ ቅርሶች ክፍል ለብቻው ሆነ። እኔም ከቅርስ ጥበቃ ወደ ጥናት መጣሁ። የማይዳሰሰውና በውስጥ የማስመዝገብ እንጂ በውጪ የማስመዘግብ ላይ መዋቅር አልነበረውም። በጊዜው በነበሩት አመራር ይህን ነገር እንደ አዲስ መሥራትና ማስመዝገብ አለብን የሚል ነጥብ አነሱ። ማን ይሥራ ሲባል እኔን መደቡኝና በአስተባባሪነት፣ አንድ ኹለት ሰዎችና ካሜራ ባለሙያ ይዘን ጀመርነው።

ከዛ በመስቀል ጀመርን። አብረን ከጀመርን ውስጥ ነገሩ ጠንከር ሲል ገሸሽ ያሉ አሉ። እኔም የምችለውንና ሌሎች የሚሰጡኝን አስተያየት በመጨመር የመስቀል በዓል እንዲመዘገብ ተሠራ። በዛ ልምድ አግኝተን ቀጠልን። በዚህ ሥራ ፋና ወጊ ነኝ ማለት እችላለሁ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስመዝገብ። በአገር ውስጥ ምዝገባ ላይ ግን በፊትም ሌሎች ሰዎች ነበሩ።

ሌሎች እንዲመጡ ብዙ እታገላለሁ፤ በግሌ። ግን ክፍሉም በደንብ የተዋቀረ ነው ለማለት አይቻልም። በግለሰብና ጥቂት ለማለት በማስደፍር የሰው ኃይል እየተሠራ ነው። እኔ አንድ አንድ ሰው በአዲስ ሥራዎች ላይ ልምድ ለማካፈል እየሞከርኩ ነው። በሂደት ሌሎችንም በደንብ ለማሳተፍ ጥረት እናደርጋለን።

አንዳንዶች በስጋት አንዳንዶች በቸልታ የቀሩት ደግሞ ከጥቅም አንጻር ነገሩን ተወት ሊያደርጉት ይችላሉ።፤ለገዛኸኝ ብርታት የሆናችው ምንድን ነው?

ከበፊትም በጸባዬ አንድ ነገር ውስጥ አልገባም፤ መሠራት አለበት ብዬ ከገባሁ ግን፤ ባለኝ አቅም ለመሥራት ጥረት አደርጋለሁ። የፈለገ ራሴ ብጎዳና መስዋዕትነት የሚያስከፍል ቢሆን ሥራዬ ብዬ ከእለት ተእለት እሠራለሁ። ለምሳሌ ጥምቀት ከሦስት ዓመት በፊት ነው የተጀመረው። እናም ፊልድ ከመሄድ ጀምሮ፣ የማስመረጫ ሰነዱን ማዘጋጀት፣ እንደገና ለተለያየ ባለድርሻ አካላት ታቀርቢያለሽ። እሱንም እኔ ነኝ የማቀርበው። በተሰጠኝ አስተያየት መሠረት ደግሞ አስተካክላለሁ።

በእርግጥ አሁን በጥምቀት ላይ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያንም የተሳተፉ ነበሩ። እና ከዛም ከዩኔስኮ ጋር ምልልስ አለ፤ ይሄ አልተሟላም ይሄ ተሟልቷል የሚል አለ። ምዝገባ ቦታ ላይ ያለው ትግልም ቀላል አይደለም። ዘንድሮ እንኳ እዛ ሄጄ ቪዛ ተሰርዞብኝ አንድ ቀን ኤርፖርት አድሬአለሁ። እንደዛ ያሉ ችግሮች አሉ፤ ግን ከእግዚአብሔር ጋር ሆኜ ለዚህ ውጤት ለመብቃት በመታደሌ ደስታ ይሰማኛል።

ኤርፖርት ያደሩበት ምክንያት ምን ነበር?

ከዚህ [ከኢትዮጵያ] ቀደም ብለን ነው ዝግጅት የጀመርነው፤ ስብሰባው ኹለት ወር ሲቀረው። ኮሎምቢያ እዚህ [ከኢትዮጵያ] ኤምባሲ የላትም፤ እኛም እዛ ኤምባሲ የለንም። በዛ ላይ ‹ኦን አራይቫል ቪዛ› አይሰጥም የሚል ሕግ አላቸው። ስለዚህ ምን ማድረግ ይቻላል ሲባል፣ በብዙ ድካም በዩኒስኮ በኩል የኤሌክትሮኒክ ቪዛ ተገኘ።

ልክ እዛ ስደርስ፤ መጀመሪያ የገባሁበት ኢሚግሬሽን ላይ አስተባባሪዋ ግራ ተጋባች። ምነው ስላት ቪዛው መሰረዙን ነገረችኝ። ምክንያቱን አላውቅም ብላ ወደ ኃላፊዎች አቀረበችኝ። ችግሩ ይፈታል ብዬ ነበር ስጠብቅ የነበረውና ከክፍል ክፍል አብሬ ስዞር ቆየሁ። መጨረሻ ግን ሲጨርሱ መልሰው ወደ ፍተሻ ቦታ አመጡኝ። ምንድን ነው ስል ቢሮ እንደምገባ ነገሩኝ፤ ግን በመጣሁበት አውሮፕላን መልሰው ሊያስገቡኝና ሊመልሱኝ  ነበር።

ሕጋዊ ሰው ነኝ፤ አገር ወክዬ ነው የመጣሁት፣ የዩኔስኮ ስብሰባ እንዳለ ይታወቃል፣ ወረቀትም ይዣለሁና ጊዜ ስጡኝ ችግሩን በ24 ሰዓት እፈታለሁ አልኩኝ። አምስት ስድስት ሆነው ነበር እየገፉ ሊያስወጡኝ የነበረው። ለ24 ሰዓት በዛ ኤርፖርት እደር አሉኝና ቶሎ ችግሩን እንድፈታ፤ አለበለዚያ እንደሚመልሱኝ አሳሰበቡኝ። የገባሁት ቅዳሜ ማታ ነው። ስለዚህ ፌስቡክ ላይ ለሚኒስቴር መሥራያ ቤቱ መልዕክት ላኩኝ። ለዩኔስኮ ቋሚ መልእክተኛ እንዲልኩልኝ አደረግሁ።

የጉባኤውን ተሳታፊዎች ጉዳይ የምትከታተል ሴት ነበረችና እርሷ ችግሩ እየተፈታ መሆኑን በማግስጡ ጠዋት በጽሑፍ መልእክት ገለጸችልኝ። እሱን [ጽሑፉን] ግን እነርሱ አልተቀበሉም። ተስፋ የመቁረጥ ሁኔታ ውስጥ እያለሁ፣ ሥሜ በማጉያ ተጠራ። ወዲያው ኹለት የኢሚግሬሽን ኃላፊዎች መጥተው ጉዳዩ እንደገባቸውና መልእክት እንደደረሳቸው ጠቅሰው፣ ይቅርታ ጠየቁኝ። ሆቴል ቡክ አድርጌ ስለነበር ደውለው በመስተንግዶ ሄጄ ለመሳተፍ ቻልኩ።

የስብሰባው ቀን 6 ቀን ነው። ሰኞ ኅዳር 29 ተጀመረ እስከ ታኅሳስ 4 ቀን ቆየ። ስለስምምነቱ አፈጻጸም በቀጣይ መከናወን ስላለባቸው ጉዳዮች ጎን ለጎን ስብሰባ ስለሚደረግ ነው። እግዚአብሔር ረድቶን እንጂ ከአየር መንገዱ ብመለስ፣ ለሥራውም እንቅፋት ሊሆን ይችል ነበር።

ብዙዎች ከባዱ ሥራ ካለቀ በኋላ ሽልማቱ ላይ አለንበት ወይም ቀድሞም ነበርንበት ይላሉ። በእርስዎ እንቅስቃሴ ዙሪያ ይህን ታዝበዋል?

ያኔ የገዳ ስርዓት ሲመዘገብ አንድ ቪድዮ ኤዲተር ነበር። የገዳ ስርዓት ሲመዘገብ የነበረውን ሂደት ተከታትሏል። እናም አልቆ ገዳ ተመዘገበ ሲባል ከክልልም፣ ከሁሉም ሰዉ በሚድያ እየወጣ ‹ያዙኝ ልቀቁኝ› የሚል በዛ። እና ደውሎልኝ ‹Success have multiple fathers, while failure is an Orphan› (‹ስኬት ብዙ አባቶች/ባለቤቶች አሉት፤ ውድቀት ግን ባለቤት አልባ ነው) አለኝ። ይህን አባባል መቼም አልረሳውም።

በእርግጥ ኃላፊዎች ድርሻ አላቸው። ሰነዱ ለይ ይፈርማሉ፤ አስተያየት ይሰጣሉ። የመንግሥት ሥራ ነው፣ በመንግሥት በጀት ነው የሚሠራው። እና እንደገና ስብሰባ ይጠራል፤ ኃላፊዎች የማስተባበር ሥራ አለ፤ ድጋፍ ይሰጣሉ። እዚህ ላይ ዮናስን ማንሳት ይቻላል። በነበረ ጊዜ አስተያየት ይሰጣል።

ኃላፊዎች ሐሳብ ይሰጣሉ። የሚያቀርቡት ሐሳብም ተቀባይነት ሲያገኝ ሥራውን ለማዳበር ይውላል። እኔም ያንን መልስ አምጥቼ በአቅሜ ተንትኜ ዋናውን ሰነድ ማዘጋጀት ነው። ከዛ አስተያየት ይሰጣል፤ ከዩኒቨርስቲ የሚመጡ ምሁራን አስተያየት ይሰጣሉ። ያንን ሐሳብ ተቀብዬ የማካትተው እኔ ነኝ። አሁን ጥምቀት ላይ  ከቤተክርስትያን እነ መምህር ዳንኤል ሰይፈሚካኤለ ትልቅ እገዛ ሲያደርጉ ነበር፤ አስተያየት በመስጠት፤ የሃይማኖት ጉዳይ ስለሆነ። እንዲሁም አባ ኪሮስ የሚባሉ አባት አሉ፤ አዲስ አበባ የተካሄደውን ቀርጸው ትብብር ያደርጉልናል። ክልሎችም ቢሆኑ፣ ባለው አቅም ድጋፍ ያደርጋሉ፤ ሰነዱ ይላካል። አስተያየት ካላቸው ይልካሉ።

ግን አንዲት ቀን ጉባኤ ላይ የተሳተፈም ሰው ተነስቶ ‹አስመዝግቤ› ይላል። አሁን ራሱ በቲቪ የገዳ ስርዓትና ሌሎቹም ሲመዘገቡ ያልነበረ፣ ጥምቀት ላይ ደርሶ አስመዘግበን እያለ መግለጫ ሲሰጥ አይቻለሁ። ያ ግን ስንት ሰው የደከመበት ነው፤ የካሜራ ባለሞያዎች ትልቅ መስዋዕትነት የከፈሉበት ሥራ ነው። ከእነርሱ መረጃ ካላገኘን አይሆንም።

ግን ቀጥታ ከዚህ ሥራ በተገናኘ ጥሩ አስተዋጽኦ አላቸው የምላቸው በጣት የሚቆጠሩ እጅግ ጥቂት ሰዎች ናቸው። ኃላፊዎች ሰነድ ላይ በመጨረሻ የሚፈርሙ ናቸው። ሌላው የደከመበትን ሰነድ ኃላፊው ነው የሚፈርመው። ምክንያቱም ኃላፊው ነው የመሥሪያ ቤቱን የሚወክለው።

ብዙ ጊዜ ግን የመንግሥት ሥራ ይባላል፤ ጥምቀት በዩኒስኮ መመዝገቡ እንደተበሰረ፣ ፌስቡክ ሳይ ሰውም የሚያውቅ አይመስለኝም ነበር፤ ምን ያህል ክትትል እንደሚያደርግ የገባኝ ሳይ ነው። አንዳንዶች የመንግሥት ሥራ አድርገው በቀላል የሚያልፉት አሉ። ጉዳዮን የሚያውቁ ሰዎች ተናግረዋል፤ የሚውቁ ክትትል አድርገው እውቅና ሰጥተውኛል። እኔ ለፍቻለሁ ግን እኔ ብቻ ነኝ የሚል ስሜት የለኝም። ይሄ የአገር፣ የመንግሥት ሥራ ነው።

ግን ለምሳሌ እኔ ሥታው እንደተሰጠኝ ግዴለሽና እገሌ ይህናን ያንን ካላደረገልኝ እያልኩ የምዘናጋ ብሆን፣ እንዲህ ማድረግ አንችልም ነበር። ግን እስከመጨረሻ እግዚአብሔር እስከፈቀደው ድረስ ጥረት እያደረግሁ፣ በራሴ የምችልውን በራሴ፣ ካልሆነ ሌሎች ድጋፍ እንዲያደርጉልኝ እያደረግሁ ነው።

ቀጣይ አዲስ የቤት ሥራና ተመዝጋቢ ቅርስ የትኛው ነው፣ ምንስ ነው?

ሻደይ፣ አሸንድዬና አሸንዳን ለማስመዝገብ የሚያስችል ሰነድ አምና መጋቢት 2011 ላይ ልከናል። ይህ ሰነድ ላይ ዘንድሮ ዩኔስኮ አሟሉ የሚለውን አስተያየት ይሰጣል። ጥያቄ የሚቀርብልን ከሆነ በዛ ላይ ተመሥርተንና ያገኘነውን ልምድ ቀምረን እንደገና ከልሰን እናቀርባለን። እንጂ አምና ተልኳል።

ዘንድሮ የሐረሪ ብሔር የሹዋል – ኢድን በዓል አከባበር ለማስመዝገብ እንጀምራለን። እስከ አሁን የክርስትናው ላይ ነው የሠራነው፤ አሁን የሙስሊሙን እንይ በሚል እንዲሁም ከእነርሱም ጥያቄ ይቀርብልን ስለነበር፤ ያንን ተመልክተን ቅርሱን ለማስመዝገብ የማስመረጫ ሰነድ መረጃ የማሰባሰብ ሥራ እየሠራን ነው።

የሹዋል – ኢድ ክብረ በዓል ረመዳን አንድ ወር ከተጾመ በኋላ ሲፈታ እንደገና ስድስት ቀን ይጾማል። ያ ጾም ሲያልቅ የሚደረግ ክብረ በዓል ነው። ሌላው አካባቢ ጾሙ ይጾማል ግን በዓሉ የለም፤ ይህ በዓል ሐረሪዎች ጋር ነው ያለው። ይህን ከሌሎች እሴቶቻቸው ጋር አድርገን ለማስመዝገብ ነው። አሁን በቀጣይ ሥራዬ ሹዋል ኢድ ነው። አንድ ባልደረባዬም አለች፤ እንደ አዲስ ልምድ ለማካፈልም ከእርሷ ጋር ነው የሄድነው።

በቀጣይ ደግሞ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ እየመረጠ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ቅርሶች ላይ እንሠራለን።

ለመሆኑ ምን ያህል ዓመት በዚህ ዘርፍ ላይ አገለገሉ

ከ15 ዓመት በላይ ሆኖኛል። መጀመሪያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አንድ ዓመት ሠራሁ። ከዛ ባህልና ቱሪዝም ቆይቼ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ 9 ዓመት አካባቢ ሠራሁ። ባህልና ቱሪዝም ሆኜ በትምህርት ነው ያሳለፍኩት።

የቤተሰብ ጥያቄ ላንሳ፤ ብዙ ጊዜዎን ከከተማ ውጪና በሥራ ስለሚያሳልፉ የቤተሰብ ጊዜን አይሻማም?

ይህን ሥራ ከመጀመሬ በፊት በእረፍት ጊዜ ፊልም የማየት ልምድ ነበረኝ። ያኔም ቢሆን በሥራ ነበር የምናሳልፈው፤ በአገር ውስጥ የማይዳሰሱ ቅርሶች ምዝገባ ሥራ ምክንያት። ያ ሥራ ለዚህኛው መሠረት ሆኖኛል። ከባድ ቢሆንም ያሉን ቅርሶች ምን እንደሆኑ እንዳውቅ አድርጎኛል።

ከመስቀል በዓል መመዝገብ በኋላ ግን ፊልም ቤት ረግጬ አላውቅም። ባለኝ አጋጣሚ ቃና በቀን አንድ ሰዓት አያለሁ። ባልከታተልም አንዱን አያለሁ። ከዛ ውጪ የዜና አውታሮችን እከታተላለሁ። ዋና ትኩረቴ ሥራ ነው። ይህም ተጽእኖ አድርጎብኛል። ትዳር የመያዝ ነገርንም አጓቶብኛል።

መጀመሪያ በታሪክ ትምህርት እንደጨረሱ ጠቅሰዋል፤ ይህን የቅርስ ዘርፍ ቀድሞም ይፈልጉት ነበር?

ትኩረቴ ታሪክም ስለሆነ የተማርኩት አርኪዮሎጂ ነበር። ማለትም ታሪክ ስንማር አራት የሚሆኑ የአርኪዮሎጂ ኮርሶችን ወስጃለሁ። በተለይ ወደ ባህል ከመጣሁ በኋላ አርኪዮሎጂ ለመማር ትልቅ ጥረት አድርጌ ነበር። የሆነ ጊዜ እንደውም ቻይና ተወዳድረን አንድ ልጅ ብቻ በልጦኝ እሱ ሄዶ ተማረና እኔ ቀረሁ። በኋላ ግን ወደ አንትሮፖሊጂ እንድሄድ ያደረገኝ የምዝገባ ሂደት ውስጥ የነበረ አንድ ባልደረባ ነው። ከእኛ ቀድሞ የተማረ ነበር፤ አንትሮፖሊጂ። እና አርኪዮሎጂ የቁፋሮው ነው አንትሮፖሊጂ ግን አሁን ያለውን ባህል ነው የሚያጠናው የሚል ሐሳብ ሰጠኝ።

ዋናው ደግሞ እህቴ ናት። ታናሽ እህቴ ወደ ባህል ዝንባሌ ነበራት። ምክንያቱም የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ባህል ፕሮግራም ላይ ትሠራ ነበር፤ 90ዎቹ አካባቢ። እናም እርሷም ለመማር ትልቅ ጥረት ታደርግ ነበር። ‹ይህኛው ነው የሚሻለው፣ ለሥራ ራሱ ማኅበረሰብ ላይ ለመሥራት፣ ከታሪኩ ጋር ይረዳሃል› ብላ ገፋፍታኝ ነው የገባሁት። በኋላ እዚህ ላይ መሳተፌ አገሬን እንዳውቅ፣ ቅርሶቻችንን እንዳውቅ ረድቶኛል።

በእርግጥ ብዙ መሥራት እንዳለብኝ ይሰማኛል። እግዚአብሔር እስከ ፈቀደ ድረስ የምችለውን እሠራለሁ።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here