‹‹የኔ ዜማ›› – ጥበበኞችን ያገናኘ የባለዜማው አልበም

0
661

አበበ ብርሃኔ፣ ይልማ ገብረአብ፣ አማኑኤል ይልማ፣ አብርሃም ወልዴ፣ አበጋዝ ክብሮም፣ አቤል ጳውሎስ፣ ቴዎድሮስ ካሳሁን፣ ፀጋዬ ደቦጭ፣ አየለ ማሞ እና ሰለሞን ሳህለ እንዲሁም ናትናኤል ግርማቸውና ሌሎችም፤ በሙዚቃው አንጋፋ ከሆኑ እስከ ጀማሪዎቹ ድረስ የተሳተፉበት ነው፤ ‹የኔ ዜማ› አልበም። እንዲህ ያሉ በርካታ የሙዚቃ ቀማርያን አሻራቸውን ያኖሩበት ሙዚቃ ከተሰማ የከራረመ ይመስላል። ብዙዎችም ‹‹ጎሽ! አዲስ ነገር ልንሰማ ነው›› ሲሉ አስተያየት መስጠት ከጀመሩ ውለው አድረዋል።

እነዚህን የሙዚቃ አንጋፎች ይዞ አዳዲሶቹንም አሳትፎ የተገኘው አልበም የዳዊት ፅጌ ‹የኔ ዜማ› ነው። ዳዊት ‹ባላገሩ አይዶል/ ባላገሩ ምርጥ› የድምጻውያን ተሰጥኦ ውድድር ላይ በነበረው ተሳትፎ አይረሴ የሆነ ትዝታን በተመልካች ያኖረና ብዙዎች ቆመው ያጨበጨቡለት ድምጻዊ ነው። አራት ዓመታት የወሰደ የመጀመሪያ የአልበም ሥራውን በሚመለከትም ከአልበሙ ዝግጅት ጀምሮ እስከ ስርጭት ድረስ የተሳተፉ ባለሞያዎች በተገኙበት፣ ባሳለፍነው ሐሙስ ጥር 7/2012 በሸራተን ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል። በዚህ ላይ መሳተፍ የቻለችው አዲስ ማለዳም ጥቂት ነጥቦችን ሰባስባ ለአንባቢዋ ቋጥራለች።

አልበሙ

‹‹የኔ ዜማ›› 14 አዳዲስ ሙዚቃዎችን አካትቷል። ከእነዚህም 13 ሙዚቃዎች በሲዲ ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ አንዱ ደግሞ በመረጃ መረብ ላይ የተለቀቀ ነው። ይህ የሆነው ሙዚቃዎቹ እያንዳንዳቸው የሚይዙት ደቂቃ ጨመር ያለ በመሆኑና ሲዲው ላይ ማኖር ስላልተቻለ እንደሆነ ተጠቅሷል። በዚህ አልበም የአይረሴው የክቡር ዶክተር ጥላሁን ገሠሠ አንድ ሙዚቃ በተወሰኑ ለውጦች ተካትቷል። ‹‹ቃልኪዳን›› የተሰኘው ይህን ዜማ ለመሥራት ተገቢውን ፈቃድ ያገኙ መሆኑን የጠቀሰው ዳዊት፤ እንደውም ቀድሞም በዚያው ሙዚቃ ሥራ ላይ የነበሩት አየለ ማሞ የዳዊት አልበም ላይ በተካተተው የጥላሁን ሙዚቃ ዳግም አሻራቸውን አኑረዋል።

በአልበሙ ከተካተቱ 14 ሙዚቃዎች ውስጥ ሌላው ባላገሩ ቁጥር አራት ሙዚቃ ነው። ይህም ባላገሩ አይዶል ለውድድሩ አሸናፊ ሊሰጠው ቃል ከገባው ሽልማት መካከል አንዱ ሲሆን፣ ጊዜው ደርሶ ዳዊት ሙዚቃውን በአልበሙ ሊያካትት ችሏል። በተጨማሪም ከአልበሙ ውስጥ ለኹለት ሙዚቃዎች በቅርብ ጊዜ የሙዚቃ ቪድዮ ይሠራላቸዋል ተብሏል።

‹‹ለአልበሙ ሥያሜ ለምን ‹የኔ ዜማ› ተመረጠ?›› የሚል ጥያቄ በሐሙሱ መግለጫ ላይ ተነስቶ ነበር። ጠቅላላ ሥራው በዚህ ዜማ ሐሳብ የተቃኘ መሆኑን ታድያ የአልበሙ አሳታሚና አከፋፋይ በመሆን በዋናነት ኃላፊነቱን የወሰደው የባላገሩ ቴሌቭዝን ባለቤት የሙዚቃ ባለሞያው አብርሃም ወልዴ ጠቅሷል። በተጨማሪ ግን በአልበሙ ላይ የዜማ ሥራዎች ያበረከተው የአበበ ብርሃኔ የዜማ ስልት መንገሥ ስላለበትም ይህ ሙዚቃ በመጠሪያነት እንደተመረጠ አንስቷል። በኢትዮጵያ ሙዚቃ ዘርፍ ብዙ የዜማ ስልቶች እንደታጡና እንደተተዉም አብርሃም አያይዞ በቁጭት ተናግሯል።

ታድያ ወደ ቀደመ ነገራችን ስንመለስ፤ ለሙዚቃው ቅርበት ያላቸውና የሚከታተሉ ሰዎች ሊያስታውሱ እንደሚችሉት አልበሙ እንደሚለቀቅ ከተነገረ በርካታ ወራት አልፈዋል። በተለይም ‹‹አማን አማን›› የተሰኘውና የሙዚቃ ቪድዮ የተዘጋጀለት የዳዊት ሙዚቃ ለእይታ የወጣና የቀረበ ሰሞን፣ አልበሙም እንደዛው ባልራቀ ጊዜ ለአድማጭ ይደርሳል ተብሎ ተጠብቆ ነበር።

ለዚህም ሳይሆን አልቀረም ብዙዎች ‹‹መች ነው አልበሙ የሚወጣው፤ ምነው ዘገየ?›› የሚሉ ጥያቄዎችን እንዲያቀርቡ ተጨማሪ ምክንያት ሆኗል። ‹‹ሰው ቀለል አድርጎ በሚሰጠኝ ኃላፊነት ምክንያት ፈርቻለሁ፤ ግን ፍርሃቱ ወደ ጥንቃቄ የሚመራ ነው›› አለ፤ ድምጻዊው ዳዊት ፅጌ። ይህን ያነሳው የሰዎች ጥያቄ ምን ያህል ሥራውን በጥንቃቄ እንዲሠራ እንዳበረታታው ሲገልጽና በተጠበቀው ልክ ይገኝ ይሆን የሚለውም በሐሳቡ የሚመላለስ ጉዳይ መሆኑን ሲጠቁም ነው።

ይህ የአድማጩ ጠባቆት ሥራውን በጥንቃቄና በሙሉ አቅም ለመሥራት እንዳበረታቸውም አብርሃም ወልዴ ገልጿል። እንደውም አራት ዓመት የፈጀው አንድም በዚህ ምክንያት መሆኑን ጠቅሷል። ‹‹አንድ አልበም በአራት ወር ውስጥም ሊወጣ ይችላል።›› ያለው አብርሃም፤ ‹‹የኔ ዜማ›› በአናጻሩ ጊዜ ተወስዶበትና እስከ መጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ ያለመሰልቸት በጥንቃቄ የተዘጋጀ ስለመሆኑ ይጠቅሳል። ይህም አንድም አድማጩ ከሚጠብቀው አንጻር ለመገኘት ከማሰብም የተነሳ ነው ብሏል።

በተጨማሪ ታድያ አልበም ለማውጣት ምቹ ያልነበሩ አገራዊ ሁኔታዎች እንደነበሩ አብርሃም አስታውሷል። እነዚህም አልበሙ ይወጣል ከተባለበት ጊዜ አልፎ እንዲዘገይ ቢያደርጉም፤ ጊዜ አግኝቶ በደንብ ለማጥራት ተጨማሪ ጊዜ ሰጥቶናል ብሏል። ‹የኔ ዜማ› አልበምም ለአድማጮች በሲዲ 50 ብር እንዲሁም በ‹ሸክላ መተግበሪያ› ደግሞ በመረጃ መረብ ላይ ይገኛል ተብሏል።

ባላገሩ ምርጥ

ባላገሩ አይዶል ወይም ባላገሩ ምርጥን ጥቂት እናስታውስ። መስከረም 17 ቀን 2008 አሸናፊውን ዳዊት ፅጌን እንዲሁም እሱን ተከትለው ኹለተኛ እና ሦስተኛ የወጡትን ድምጻውያን ኢሳያስ ታምራት እና ሜላት መንገሻ ያበሰረው ውድድሩ፤ ለተከታታይ ኹለት ዓመታት የተካሄደ ነበር። ይህ የተሰጥኦ ውድድር ከዛን ጊዜ ጀምሮ እንደ ዋና አዘጋጁ አብርሃም ወልዴ ገለጻ፣ ከኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ጋር ስምምነት ባለመፈጠሩ እንዲሁም በወቅቱ አብርሃም በነበረበት የጤና ሁኔታ ምክንያት ተቋርጧል።

ባላገሩ ምርጥን ተወዳጅ ያደረገውና ዋጋ ያሰጠው በባለሙያዎች ሐሳብ የሚሰጥበትና ምርጥ የተባሉ ሥራዎችን በማቅረብ በሚደነቀው አብርሃም ወልዴ ስለሚዘጋጅ ብቻ አልነበረም። ይልቁንም እንደ ዳዊት ፅጌ ያሉ በርካታ አስደማሚ ድምጽ የታደሉ ሙዚቀኞች ስለተገኙበት፣ አልፎም መሃል ከተማ ላይ ያልተወሰነ መሰናዶ ስለነበር ነው።

ባላገሩ ምርጥ ተሰጥኦ ያለውን ሁሉ አስተናግዷል። በክልሉ ዙሪያ በየከተማው ተንቀሳቅሷል፣ እድሜና ፆታ ሳይገድብ ሁሉን አሳትፏል። በተለመደው ከሚደረገው መረዋ ድምፅ ያላቸውን ሰዎች ፍለጋ በዘለለ በአስቀያሚ ድምፅ የሚወዳደሩ መኖራቸው ደግሞ አድማጭ ተመልካቹ የበለጠ እየተዝናና እንዲቆይም አስችሏል። ታድያ ይህ የተሰጥኦ ውድድር እንዲቀጥልና እንዳይቋረጥ የብዙዎች መሻት ቢሆንም ሳይሆን ቀርቷል።

በዳዊት ፅጌ ‹የኔ ዜማ› አልበም ዙሪያ በተሰጠው መግለጫ ላይ የተሰማው ጥሩ ዜና ታድያ በአንጻሩ ነው። አብርሃም ወልዴ ባላገሩ አይዶል/ ባላገሩ ምርጥ ከጥቂት ወራት በኋላ በባላገሩ ቴሌቭዥን እንደሚጀምር ገልጿል። ይህም ተሰጥኦ እያላቸው ሰፋ ያለና አማራጭ የሚሆን መድረክ ላላገኙ ብዙዎች አዲስ በር እንደሚሆን ይጠበቃል።

ባላገሩ ቁጥር አራት

‹‹ባላገሩ›› የተሰኘው ነጠላ ዜማ ከቁጥር አንድ ጀምሮ እስከ እስከ ሦስት ድረስ በተለያዩ ጊዜያት ለአድማጭ ሲደርስ ነበር። ባላገሩ ቁጥር አንድ በአቦነሽ አድነው፣ ቁጥር ኹለት በደሳለኝ መላኩ፣ ቁጥር ሦስት ደግሞ በድምጻውያን ኤፍሬም ታምሩና ጎሳዬ ተስፋዬ በተለያዩ ዓመታት መሠራታቸው ይታወሳል።

የእነዚህ ሙዚቃዎች የግጥምና የዜማ ደራሲ እንዲሁም አዘጋጅ አብርሃም ወልዴ፣ ባላገሩ አይዶል (ባላገሩ ምርጥ)ን ሲያዘጋጅም፤ ለአሸናፊው ድምጻዊ እንደ አንድ ሽልማት ብሎ ያስቀመጠው ባላገሩ ቁጥር አራትን መሥራት እንዲሁም አንድ ሙሉ አልበምን ነበር። ይህም ከዓመታት በኋላ እውን ሊሆን ችሏል። ባላገሩ ቁጥር አራት ሙዚቃም በድምጻዊ ዳዊት የመጀመሪያ አልበም ‹የኔ ዜማ› ውስጥ ለአድማጭ ቀርቧል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here