ዳሰሳ ዘ ማለዳ (ጥር 14፤ 2012)

0
1142

በከተማ አስተዳደሩ ውስጥ ቁልፍ የሚባሉ የተለያዩ ሹም ሽሮችን እንደሚያስተናግድ የሚጠበቀው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ከነገ ጠዋት ጀምሮ ለሶሰት ቀን የሚቆይ መደበኛ ስብሰባ ጠራ። በከተማ አስተዳደሩ ውስጥ ካሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊነቶች እስከ ወረዳ ድረስ የሚደርስ የሹም ሽር ውጤትን እንደሚያስከትል ይጠበቃል ሲሉም የአዲስ ማለዳ ምንጮች ገልፀዋል። በከተማ አስተዳደሩ ውስጥ ያሉ የተለያዩ የስራ ሃለፊዎችም ‹‹በግምገማ ውጤት መሰረት›› ከስራ ሃላፊነታቸው ላይ መነሳታቸውን የሚገልፅ ደብዳቤ እንደደረሳቸውም ገለፀዋል። (አዲስ ማለዳ)
…………………………………………………………………………………………………………………………………………………
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) ዛሬ ከደቡብ ክልል ከተወጣጡ ከሁለት ሺህ በላይ ከሚሆኑ ተወካዮች ጋር በጽህፈት ቤታቸው ባካሄዱት ምክክር በክልል ከመደራጀት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጥያቄዎች በአንድ መድረክ ላይ መልስ መስጠት እንደማይቻል ተናገሩ። ከሁሉም የክልሉ ዞኖች ከተወጣጡ ምሁራን፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶች እና የወጣት ተወካዮች ጋር በተካሄደው ምክክርም ከሰላም እጦት ጋር ተያይዞ ለሚነሱ ጥያቄዎች ተነጋግሮ መፍትሄ የማበጀት ስራ ይሰራል ብለዋል፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ። እንዲሁም አዲስ በሚዋቀር ኮሚቴ ከመሰረተ ልማት እና ከመልካም አስተዳደር እጦት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጥያቄዎችን በዘላቂለነት ለመፍታትም ቃል ገብተዋል።(ፋና ብሮድካስቲንግ)
.…………………………………………………………………………………………………………………………………………………
ባለፉት 70 አመታት ከታየው የከፋ እንደሆነ የተገለፀው እና ኢትዮጵያን ጨምሮ በምሥራቅ አፍሪካ አገራት የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ወረርሽኝ ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማጠናከር የተባበሩት መንግሥታት የአስቸኳይ ዕርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ 10 ሚሊዮን ዶላር ለገሰ። ተቋሙ እንዳለው የአንበጣ መንጋው ቀድሞም የምግብ እጥረት የገጠማቸው ማኅበረሰቦች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች የነበረ ሰብል እና የግጦሽ ሳር አውድሟል። “ይኸ አውዳሚ የአንበጣ ወረርሽኝ በምሥራቅ አፍሪካ በአሳሳቢ እና አስፈሪ ፍጥነት እፅዋትን እያወደመ ነው። ቀድሞም የምግብ እጥረት የገጠማቸው ተጋላጭ ቤተሰቦች ሰብላቸው አይናቸው እያየ ሰብላቸው እየወደመ ነው” ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት የአስቸኳይ ዕርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ ኃላፊ ማርክ ሎውኮክ ተናግረዋል።
ኃላፊው አስቸኳይ እርምጃ ካልተወሰደ የአንበጣ መንጋው ወደ ሌሎች አገሮች ተዛምቶ አስከፊ ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል አስጠንቅቀዋል። (ዶይቸ ቬለ)
……………………………………………………………………………………………………………………………………………………
በኢትዮጵያ እየተስፋፋ የመጣው የስፖርት ውርርድ (ቤቲንግ) ሙሉ በሙሉ እንዲቆም ዛሬ በኢፌዴሪ ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር አዘጋጅነት በተካሄደው መድረክ ላይ ተጠየቀ። በስፖርት ውርርድ ዙሪያ የተለያዩ አገራትን ልምዶች በማንሳት ጥናታዊ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት የተካሄደ ሲሆን በኢትዮጵያ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ስነ ልቦናዊ ቀውሶችን እያስከተለ በመሆኑ ውርርዱ እንዲቆም ጥያቄ ቀርቧል። ውርርዱ በብሄራዊ ሎተሪ በህጋዊነት ተመዝግቦ እና ለመንግስትም ግብር ሚከፈለበት ህጋዊ የንግድ እንቅስቃሴ በመሆኑ ለክልከላ አስቸጋሪ ሆኖ መገኘቱን የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መጥቀሱ የሚታወስ ሲሆን በተለያዩ አማራጮችም ውርርዱ እንዲከለከል ህግ አውጪው ላይ ጫና ለማሳደር ቅስቀሳዎችን እያካሄደ ይገኛል። (አዲስ ማዳ)

…………………………………………………………………………………………………………………………………………………
የግሪክ ሕገ መንግስታዊ ፍርድ ቤት ዳኛ በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩት ካትሪና ሳኬላሮፖሉ በአገራቸው ታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዘዳንት ሆነው የፓርላማውን አብላጫ ድምጽ በማግኘት ተመረጡ። ታሪካዊ በተባለው እና ሮብ እለት በተካሄደው ጉባኤው ላይ የወግ አጥባቂው ኒው ዴሞክራሲ ፓርቲ ከፍተኛውን ድምፅ ይስጣቸው እንጂ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ይሁንታቸውን አልነፈጓቸውም። በመጋቢት ወር ስልጣን የሚረከቡት ካትሪና ለአምስት አመታት አገሪቱን ያስተዳድራሉ። (አልጀዚራ)
.…………………………………………………………………………………………………………………………………………………

ለስራ በተላኩበት አገር በተደጋጋሚ ሰራተኞቹ እየጠፉበት ያለው ኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ)ገዥውን ፓርቲ ማገልገል ብቻ አላማቸው ያደረጉና ከዚያ ውጭ የሕዝብም ሆነ የትኛውም ፓርቲ ፍላጎት የማይነሱበት፤ ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጉዳዮችን ለመዘገብ የሚያስችል ሁኔታዎች የሉም በሚል በያዝነው ሳምንት በእግሊዝ ለንደን ለስራ በሄደበት ወቅት ጥገኝነት የጠየቀው ቢላል ወርቁ ተናገሩ። ከቢላል በተጨማሪም ቢቢሲ ያጋገራቸው የድርጅቱ ሰራተኞች ኢቢሲ ጉዳዮች እየተመረጡ ነው የሚዘገቡት እና የኤዲቶሪያል ነፃነትም የሌለበት ነው ሲሉ ወቅሰዋል። “እንደ ከዚህ ቀደሙ እኔን ብቻ አገልግሉ የሚልና ሌላውን ሰምቶ እንዳልሰማ የሚሆን መገናኛ ብዙኃን በመሆኑ የድርጅቱ አገልጋይ ሆኖ ላለመቀጠል ወስኛለሁ” ሲል ቢላል ለቢቢሲ ተናግሯል። (ቢቢሲ)

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here