‹‹የታገቱትን ተማሪዎች ጉዳይ በየቀኑ እየተከታተልኩ ነው›› የአማራ ክልል

0
664

በህዳር ወር 2012 የመጨረሻ ሳምንት ከደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ወደ ጋምቤላ ከተማ በመጓዝ ላይ ሳሉ በአጋቾች እጅ የገቡት ተማሪዎች ጉዳይ አሁንም አወዛጋቢ ሆኖ ቀጥሏል። እስከ አሁን ባለው መረጃም ተማሪዎቹ የአማራ ክልል ነዋሪ እንደሆኑ በመገለፁ አዲስ ማለዳ የአማራ ክልል የፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አበረ አዳሙን አነጋግራለች።

ኮሚሽነሩ ምንም እንኳን በጉዳዩ ላይ በቀጥታ ለመሳተፍ የህግ ገደብ ቢኖርባቸውም የታገቱት ተማሪዎች ከተያዙ እለት ጀምሮ የልጆቹን ሁኔታ በቅርበት እየተከታተሉት አንደሆነ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ‹‹የስልጣን ገደብ ቢኖርብንም ልጆቻችን ናቸው እኮ፣ መቶ በመቶ ቅድሚያ ሰጥተን እየተከታተል ነው›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ዛሬ አመሻሹ ላይ ገልጸዋል። ‹‹ጉዳዩ የኛ ጉዳይ ነው፣ ነገር ግን መዋቅር መከበር ስላለበት የፌደራል ፖሊስ እና የክልሉ ፖሊስ እንጂ እኛ ምንም መናገር አንችልም›› ብለዋል።

‹‹የማውቀው ነገር የለም ልልሽ አልፈልግም፤ ግን ደሞ መግለጫ ለመስጠት ገደብ አለብኝ›› ሲሉም ተጨማሪ መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል። ሕ

በወለጋ ዞኖች ጠንካራ መሰረት እንዳለው የሚታወቀው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር(ኦነግ) ቃል አቀባይ ቀጄላ መርዳሳ ግን ‹‹ጉዳዩን በደንቢ ዶሎ አካባቢ ካሉ ሰዎች አጣርተን የተጨበጠ ነገር አላገኘንም፤ አንዳንዱ ነገር ድራማ ይመስላል›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

‹‹ማን የት ቦታ እንደተያዘ ለማረጋገጥ ህብረተሰቡን እና አንዳንድ ተቋማትን ጠይቀናል፣ ተጨባጭ ነገር ማግኘት አልቻልንም›› ብለዋል። ‹‹ምን አልባት ውዥንብር ይሆናል ብለን እንጠረጥራለን፣ ጉዳዩ የተማሪዎቹ ብቻ አይደለም፣ ከዚህ በፊት የኦሮሚያ ክልል ተወላጅ የሆነ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ተያዘ ተብሎ የት እንደገባ ሳይታወቅ ከዛ ተገኘ ተባለ፣ የት እንደነበረ ማን እንደያዘው አልተናገረም›› ሲሉም ጥርጣሬአቸውን ገለጸዋል።

የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሪታሪያት ኃላፊ ንጉሱ ጥላሁን ከሁለት ሳምንት በፊት 21 ተማሪዎች መለቀቃቸውን እና ከነዚህም 13ቱ ሴቶች ስድስቱ ወንዶች መሆናቸውን ገልፀው ነበር። በተጨማሪም አምስት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እና አንድ የአካባቢው ነዋሪ የሆነ ወጣት በአጋቾች እጅ እንደሚገኙ እና እነዚህንም ለማስፈታት መንግስት ጥረት እያረገ መሆኑን ገልፀው ነበር።

በታጋቾቹ ደህንነት ላይ የመጨረሻውን መረጃ ለዶይቼ ቨለ የሰጡት የኦሮሚያ ክልል የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሃላፊ ጌታቸው ባልቻ ከእገታው የተለቀቁት 21 ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው ተመልሰዋል ማለታቸው አይዘነጋም።

አዲስ ማለዳም ወደ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሪታሪያት ኃላፊ ንጉሱ ጋር መረጃ ለማግኘት ያደረገቸው የስልክ ጥሪ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here