የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለሠራተኞቹ ሲያቀርብ የነበረውን የቤት መግዣ ብድር ባጋጠመው የገንዘብ እጥረት ምክንያት ከጥር 14/2012 ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ አቆመ።
ባንኩ ለከፍተኛ አመራሮቹ በላከው የውስጥ ማስታወሻ ላይ እንደገለፀው ያጋጠመውን የገንዘብ እጥረት ለመፍታት የተለያዩ አሰራሮችን እየተገበረ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የባንኩን ወጪዎች መቀነስ መወሰኑ እና የቤት መግዣ ብድሩን ለግዜው ማቆምም ተጠቅሰዋል።
የባንኩ ፕሬዝዳንት ባጫ ጊና የፈረሙበት ይህ የውስጥ ማስታወሻም ባንኩ የገጠመውን የገንዘብ እጥረት ለመፍታት ሠራተኞቹ የቻሉትን ጥረት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። ባንኩ በመስከረም ወር መጀመሪያ ለኹለተኛ ጊዜ የሚሰጥ የቤት መግዣ ብድርን እና ሠራተኞች በደሞዛቸው ልክ የሚበደሩትን ብድር ማቆሙ ይታወሳል።
በተመሳሳይም የመኖሪያ ቤት ማደሻ እና የተጨማሪ ግንባታ ብድርን ማቋረጡን አስታውቆ ነበር። አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የባንኩ ሠራተኞችም የባንክ ሠራተኛ ሆነው ለመቀጠል ዋነኛ የሚባሉት ጥቅማ ጥቅሞች ከሆኑት መካከል የቤት ግዢ ብድር መቋረጡ እንደሚያሳስባቸው ይገልፃሉ። በተለያዩ ቅርጫፎች የሚሠሩ ሠራተኞች እንደገለፁትም የባንክ ሥራው የሚያመጣውን የተለያዩ ጫናዎች ተቋቁመው እንደሚሠሩ እና መሰረታዊ የሚባለው ጥቅም የሆነው የቤት መሥሪያ ብድር መቆሙ የሥራ ተነሳሽነት እንዲሁም በባንኩ ውስጥ ያላቸውን ቀጣይነትም ጥያቄ ውስጥ እንደሚከተው ይናገራሉ። በሒደት ላይ ስላሉ የብድር ጥያቄዎችም የተላለፈው ደብዳቤ ያለው ነገር ባለመኖሩ ጥያቄያቸው በሒደት ላይ የሆኑ ሠራተኞች ጥያቄአቸውን የባንኩ ፕሬዝዳንት ባጫ ጊና እንዲመለከቱላቸው ደብዳቤ ማስገባታቸውን የአዲስ ማለዳ ምንጮች ገልፀዋል።
አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የባንኩ ሠራተኛ አንደገለጹትም ለገንዘብ እጥረቱ በአገሪቱ ያለው አጠቃላይ የኢኮኖሚ ሁኔታ ምክንያት በመሆኑ በቅርቡ ይሰተካከላል ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል። የሠራተኞች የቤት ግዢ ብድር ማመቻችት በባንክ ኢንዱስትሪው የተለመደ ማበረታቻ ነው የሚሉት የባንክ እና የኢኮኖሚ ተንታኙ አብዱልመናን መሃመድ ናቸው። ‹‹የባንክ ኢንዱስትሪው ካለው ሠራተኛ ቢያንስ 40 በመቶውን ይዞ የሚገኘው ንግድ ባንክ ለአገሪቱ ሜጋ ፕሮጀክቶች ገንዘብ የማቅረብ ግዴታ አለበት። ስለዚህ እንደ አሁኑ ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት በሚያጋጥምበት ወቅት ለቤት መግዣ የሚሆን ብድር ማቅረብ የሚቻል አይደለም›› ሲሉ የባንኩን ውሳኔ ያብራራሉ።
ነገር ግን ያለጥርጥር ብድሩ መቆሙ ብድር የሚፈልጉ ሠራተኞቹን የሥራ ተነሳሽነት የሚጎዳና በግዴለሽነት እንዲሠሩ ማድረጉ የማይቀር እንደሆነም ይናገራሉ። አብዱልመናን እንደሚሉት የብድሩ መቆም በባንኩ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ወይም የሰው ኃይሉ ላይ የሚያመጣው ጫና የሚወሰነው ብድር ለመውሰድ የሚፈልጉ እና የሚጠይቁ መስፈርቶቹንም የሚያሟሉ ሠራተኞች ቁጥር ትልቅ ከሆነ ብቻ ነው ሲሉም ያብራራሉ። ነባር የባንኩ ሠራተኞች ያለጥርጥር ባንኩን ትተው ብድር ወደሚያቀርቡላቸው ባንኮች መሄዳቸው አይቀሬ ነው የሚሉት ባለሞያው ባንኩ የገጠመው የገንዘብ ችግር ግን የተለየ አይደለም በኢንዱስትሪው ውስጥ ካጋጠመው ችግር የሚለይ አይደለም፤ ብቸኛ ልዩነቱ ግን ለሜጋ ፕሮጀክቶች ገንዘብ የማቅረብ ኃላፊነቱ እንደሆነ አብዱልመናን ያስረዳሉ። ‹‹የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ፣ እየጨመረ የመጣው የብድር እና የተቀማጭ ገንዘብ ምጣኔ›› በባለሞያው ባንኩ ለገጠመው የገንዘብ እጥረት በምክንያትነት ተጠቅሰዋል።
እንዲሁም ወቅቱ ግብር የሚከፈልበት መሆኑ እና የልማት ድርጅቶች ለመንግሥት የሚከፍሉት የትርፍ ድርሻ የሚከፈልበት ጊዜ መድረሱም በተጨማሪ የባንክ ኢንዱስትሪው ላጋጠመው የገንዘብ እጥረት ምክንያት ነው ሲሉ አብዱልመናን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2010/11 የበጀት ዓመት ያልተጣራ 17 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ያተረፈ ሲሆን ይህም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጻር የ10 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ብልጫ ማሳየቱን የንግድ ባንክ ሪፖርት ያመላክታል። በተጨማሪም የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ 712 ቢሊዮን ደርሷል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የንግድ ባንኮች ላይ ያልተለመደ የገንዘብ እጥረት መከሰቱን ምክንያት በማድረግ ይህን ችግር ለማቅለል እና የገንዘብ ተቋማት ከችግራቸው እንዲወጡ ለማድረግ የዘጠኝ ቢሊዮን ብር ብድር ለመስጠት ጨረታ አውጥቷል።
እስካሁን 12 ባንኮች ጨረታውን ለመሳተፍ የተመዘገቡ ሲሆን እያንዳንዱ ባንክ መጫረት የሚችለውም እስከ ሁለት ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ነው። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ22 ሚሊየን በላይ ደንበኞች ያሉት ሲሆን ከ37 ሺህ 894 በላይ ቋሚ እና ከ22 ሺህ በላይ ግዜአዊ ሠራተኞች አሉት። በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጡን የባንኩ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊን የአብሥራን ለማነጋገር ብንሞክርም ምላሽ ሊሰጡን አልቻሉም፡፡
ቅጽ 2 ቁጥር 64 ጥር 16 2012



