ኢሕአዴግ መፍረሱን ለምርጫ ቦርድ አሳወቀ

0
372

ኢሕአዴግ የግንባሩ ሶስት ፓርቲዎች ከስመው መውጣታቸውን እና ብልጽግና የተሰኘውን አዲስ ፓርቲ ማቋቋማቸውን ተከትሎ ግንባሩ አለመኖሩን በመግልፅ መፍረሱን የሚያሳውቅ ደብዳቤ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ላከ።

ከ 15 ቀናት በፊት ለቦርዱ በላከው ደብዳቤም ግንባሩን ከመሰረቱት ሶስቱ ፓርቲዎች ወደ ብልፅግና ፓርቲ መግባታቸውን ተከትሎ አንዱ ብቻ በመቅረቱ መፍረሱን የሚያሳውቅ ደብዳቤ ለቦርዱ ማስገባቱን የቦርዱ የኮሚኒኬሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ ለአዲስ ማለዳ አረጋግጠዋል።

በሳምንቱ መጨረሻ ላይም ሕወሃት ግንባሩ ከመፍረሱ በፊት የግንባሩ አባል ድርጅቶች በጋራ ያፈሯቸው ንብረቶች ላይ ክፍፍል እንዲደረግ የሚጠይቅ እና ሃላፊነቱም የምርጫ ቦርድ መሆኑን በመጥቀስ ቦርዱም ይህንን አጣርቶ የፓርቲውን ድርሻ እንዲያካፍል ሲል ማመልከቱነም ቦርዱ ለአዲስ ማለዳ አረጋግጧል። የሀብት ክፍሉን በሚመለከት ማብራሪያ የሰጡት አወሎ እያንዳንዱ ብሔራዊ ድርጅት በግሉ ያፈራው ሀብት አለው እያንዳንዱ አባል ድርጅትም ኦዲት በመደረግ ላይ ይገኛል ብለዋል።

የኦዲት ስራው በስድስት ወራት ውስጥ ይጠናቀቃል የተባለ ሲሆን የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ለግንባሩ ሲያወጡት በነበረው ልክ መረጃዎች በሚሳዩት መሰረት የሃብት ክፍፍል እንደሚደረግ ተገልጿል። መረጃዎችን መሰረት በማድረግም ኢህአዲግ እንደ ግንባር ያፈራቸው ንብረቶች ካሉ ዋጋቸው ተገምቶ በተዋጣው ልክ ይሰጣል ‹‹ከሌለ ደግም የለም ነው ሲሉ›› አወሎ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል። ድርጅቶቹ በተናጥል ያፈሯቸው ንብረቶችን ይዘው ብልፅግና ፓርቲን ይቀላቀላሉ የተባለ ሲሆን ይህ ማለት ግን ድርጅቶቹ በጋራ እንደ ግንባር ያፈሯቸው ንብረቶች የሉም ማለት እንዳልሆነ ተጠቅሷል።

ቦርዱም እነዚህን ንብረቶች በምን አይነት መልኩ ሊካፉሉ እንደሚችሉ አለመወሰኑም በብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ተገልጿል። የብልፅግና ፓርቲ በሚኒስትር ማዕረግ የአገር ውስጥ እና የውጪ ግኑኙነት አስተባባሪ አወሎ አብዲ ለአዲሰስ ማለዳ እንደተናገሩት የፓርቲዎቹ ውህደት ህጋዊ መሰረቱን የተከተለ እና የምርጫ ቦርድን ህግ እና መስፈርት ያሟላ ነው ብለዋል። አንድ ውህድ ፓርቲ የመሆኑ ጥያቄ የሕውሓት ጭምር ሲነሱት እና ሲያሾሩት የነበረ ጉዳይ ነውም ብለዋል። ‹‹አሁን ውህደቱ ሲፈፀም አለመዋሀድ ዲሞክራሲያዊ መብታቸው ነው በብልፅና ፓርቲ ውህደት ላይ የሚያነሱት ጥያቄ ግን ተቀባይነት የለውም ሲሉ›› ገልፀዋል።

አክለውም ከዚህ በኋላ ኢህአዴግ የሚባል ግንባር የለም ‹‹ሕወሀት ለብቻዋ ክልላዊ ብሔራዊ ፓርቲ ሆና መቀጠል ትችላለች። ክልሉንም በህጋዊ መንገድ በምርጫ ማስተዳደር ይቻላል ነገር ግን ኢሕአዴግ የነበሩት መብቶች እና ግዴታዎች ወደ ብልፅግና ፓርቲ ተሸጋግረዋል›› ሲሉ ተናግረዋል። ብልፅግን ፓርቲ በበኩሉ ኢህአዴግን ወደ አንድ ውህድት የማምጣቱ ጥያቄ በተደጋጋሚ በድርጅቱ ጉባዔዎች ላይ ሲነሳ እንደነበር በመግለፅ ጥያቄውንም ተፈፃሚ ለማድረግ በዘርፉ ምሁራን እና ልምድ ባላቸው ግለሰቦች እናምሁራን በሁሉም ክልሎች በተደረገ ሳይንሳዊ ጥናት ኢህአዴግ በማክሰም ብልፅግናን መመሰረቱን ተገልጿል። በሀብት ክፍፍሉ እና ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ላይ አዲስ ማለዳ የሕውሓት የሥራ ሀላፊዎችን በስልከ ለማነጋገር በተደጋጋሚ ብትሞክርም ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 64 ጥር 16 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here