ከኹለት ዓመታት በፊት የተጀመረው እና መልካሳ፣ ሶደሬ፣ ኑራሄራ እና መተሃራ ከተሞችን የሚያቋርጠው የአስፋልት መንገድ ፕሮጀክት ሊነሱ የሚገቡ 772 የኤሌክትሪክ ምሰሶዎችን ለማስነሳት የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን አስፈላጊዉን ካሳ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ቢከፍልም ያለመነሳታቸው እንቅፋት እንደፈጠረበት ገለፀ።
ከዚህ በተጨማሪም የወሰን ማስከበር እና ካሳ የተከፈለባቸዉ ንብረቶች በጊዜው ያለመነሳት ምክንያት 66 በመቶ መድረስ የነበረበት ግንባታው ከ13 በመቶ መሻገር አልቻለም። ከኹለት ዓመታት በፊት አንድ ነጥብ ኹለት ቢሊዮን ብር በጀት ይፈጃል ተብሎ የተጀመረው እና በሰፋፊ የመስኖ እርሻዎች የሚታወቁትን አካባቢዎች ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ እንደሚያነቃቃ ተስፋ ተጥሎበት የነበረው መንገድ 94 ኪሎ ሜትር ከሆነው ጠቅላላ ርዝመቱ ውስጥ 12.46 ኪሎ ሜትር የሚሆነዉ ብቻ መገንባቱን የፕሮጀክቱ መሃንዲስ ፈልመታ አቶምሳ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በ2010 ታህሳስ 23 ተጀምሮ ታህሳስ 23/2013 እንዲያልቅ እቅድ ቢያዝለትም በወሰን ማስከበር ችግሮች ተስተጓጉሏል። መስከረም 2012 አስፈላጊውን ክፍያ አጠናቀናል ያሉት የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት ሳምሶን ወንድሙ የኤሌክትሪክ ኃይሉ ግን እስከ አሁን ምንም ሥራ ያለመሥራቱን ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አዳማ ቅርንጫፍ ኃላፊ የሆኑት መልካሙ ዲቢሳ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ካሳ መክፈሉን አምነው ‹‹ምሰሶዎቹቹን ለማንሳት በቅድሚያ ተለዋጭ የመስመር ዝርጋታ ስለሚስፈልግ እና ለዝርጋታ የሚስፈልጉት እቃዎች ባለመሟላታቸው እንዲሁም ሥራዉ ዓመታዊ አቅዳችን ስላልሆነ የኤሌክትሪክ ኃይሉ እስካሁን ተለዋጭ ዝርጋታውን አልተጀመረም›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ኃላፊዉ ለአዲስ ማለዳ እንዳሉት በቅድሚያ ሊነሱ የሚገባቸውን ምሰሶዎች ለማንሳት የተነጋገሩ ሲሆን ቀሪዉን ሥራ ለሦስተኛ ወገን በጨረታ ለማስተላለፍ ለበላይ አካል ማሳወቃቸውን ገልፀዋል።
የተቋራጩ የፕሮጀክት ኃላፊ የሆኑት ኤሊያስ ይትባረክ እስከ አሁን ለሥራ ክፍት የሆኑት 40 በመቶ ያክሉ የመንገድ ቦታዎች ሲሆኑ እነዚህም የተቆራረጡ መሆናቸውን ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል። ወረዳዎች በፈጠሩት የወሰን ማሰከበር ችግር ምክንያት ግንባታውን የሚያከናውነው ንኮማድ የተባለው ተቋራጭ ዉጤታማ የሆነ ሥራ መሥራት ያለመቻሉን የፕሮጀክት ኃላፊው አክለዋል። ንኮማድ ግንባታውን ለማፋጠን ንዑስ ተቋራጮችን አስገብቶ እየሠራ ቢሆንም ለሥራ ምቹ ሁኔታ ባለመኖሩ ንዑስ ተቋራጮቹ ለቀው እየወጡ መሆኑንም ተናግረዋል።
የመልካሳ-ሶደሬ-ኑራሄራ-መተሃራ መንገድ ፕሮጀክት በምስራቅ ሸዋ ዞን እና በአርሲ ዞን ውስጥ የሚገኙ አምስት ወረዳዎችን የሚያገናኝ ነው። በምስራቅ ሸዋ ዞን አዳማ ከተማን፣ ቦሰትና ፈንታሌ ወረዳዎችን፣ በአርሲ ዞን ደግሞ በጀጁና መርቲ ወረዳዎችንም ይሸፍናል። እስከ አሁን በዞኖቹ የተሠራዉ የወሰን ማስከበር ሥራ በምስራቅ ሸዋ ዞን 70.23 በመቶና በአርሲ ዞን 62.55 በመቶ መሆኑን የፕሮጀክት ኢንጂነር የሆኑት ፈልመታ አቶምሳ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ የተያዘለት የጊዜ ገደብ ሊጠናቀቅ 371 ቀናቶች ቢቀሩትም በሚጠበቀው ፍጥነት ያለመሠራቱ በታቀደለት ጊዜ እንዳይጠናቀቅ ያደርገዋል›› ሲሉ ፈልመታ ተናግረዋል። በተጨማሪም በላይኛው አዋሽና በአምስቱ ወረዳዎች መካከል 70 ኪሎ ሜትር ቦታ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ የሌላቸው ይዞታዎች በመገኘታቸው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ካሳ ለመክፍል እንደተቸገረ እና አሁንም ያልተፈቱ ችግሮች እንዳሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በንኮማድ ኮንስትራክሽን ኃ/የተ/የግ/ማህበር የሚገነባው የመልካሳ-ሶደሬ-ኑራሄራ-መተሃራ መንገድ ፕሮጀክት በመዘግየቱ እስከ አሁን ድረስ የጠየቀው ተጨማሪ ወጪ የለም ተብሏል።
ቅጽ 2 ቁጥር 64 ጥር 16 2012



