ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው ጊዜያዊ ሰሌዳ መሠረት፣ ነሐሴ ወር የ2012 አገራዊ ምርጫ የሚካሄድበት ወር ነው ተብሎ ይጠበቃል። የምርጫ
ቅስቀሳዎችም የሰሌዳውን መጽደቅ ተከትሎ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ እንደሚከናወን ይጠበቃል። ምርጫው ፍትሐዊ እንዲሆን የሚጠበቅ ሆኖ፣ በተለያዩ
አካባቢዎች ግን አስቀድሞ የመወሰን ሥራ እየተሠራ ነው ሲሉ ግዛቸው አበበ ይሞግታሉ። የተለያዩ ክልሎችን በመጥቀስም ይህ አስቀድሞ መወሰን በምን
መንገድ እየተሠራ እንደሆነ በማንሳት፤ በዚህ መካከል ውሳኔው ምንም ይሁን ምርጫ ቦርድ በራሱ አካሄድ በሕግና በስርዓት እንዲሄድ በሃቅም እንዲሠራ ሲሉ
ሐሳባቸውን አካፍለዋል።
ብልፅግና ፓርቲ፣ አብን፣ ኦነግ ሕወሐት… በአንድ ጉዳይ ላይ ተመሳሳይ አቋም የያዙ ቡድኖች ናቸው። ምርጫው ካልተካሄደ ሞተን እንገኛለን ይላሉ። እነዚህ ቡድኖች ለሥልጣን ያላቸው ጉጉትና ለኢትዮጵያ አንድነት (ሕልውና) ያላቸው ደንታ ቢስነት ይህን አቋም እንዲይዙ አድርጓቸዋል ብሎ ማሰብ ይቻላል። ‘የገበያ ግርግር…’ በሚለው ብሂል ለመጠቀም ስለፈለጉ፣ በዚህ ዝርክርኩና ትርምስምሱ በወጣ አገራዊ ሁኔታ ውስጥ ምርጫ መካሄድ አለበት ባዮች መሆናቸው ከዚህ የተለየ ግምት አያሰጣቸውም። እነዚህ ቡድኖች ጎን ለጎን ደግሞ ምርጫውን ከወዲሁ ለማቆጣጠርና ለእነሱ ባጋደለ መልኩ ለመወሰንም እየሠሩ ነው።
በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ልመና እንደሚዋጣላቸው፣ ለምነው የፈለጉትን እንደማያጡ፣ ልመና ስጦታቸው ነው ሊባል እንደሚችል ተናግረው ነበር። ከዚህ ጋር አያይዘውም ለምርጫ ፉክክር ሲሉ ገንዘብ ለምነው ጅማ ውስጥ መለስተኛ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ማስገንባታቸውን ጠቅሰዋል። ይህን የተናገሩት በአሳፋሪውና የሕወሐት/ ኢሕአዴግ ስርዓት ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዱ አባሉ ዐይን አውጣነት በሚገባ በተረጋገጠበት በምርጫ 2007፣ በጥረታቸው ማሸነፋቸውን፣ የእሳቸው መመረጥ የማጭበርበር ውጤት አለመሆኑን በተዘዋዋሪ መናገራቸው ነው።
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሊቀ መንበር ብርቱካን ሚዴቅሳ በተወካዮች ምክር ቤት ፊት ቀርበው ስለ ተጭበረበረው ምርጫ አውስተው፣ ይህን የመሰለ ቁማር ሊደገም እንደማይገባውና የምርጫ ቦርድም ይህ እንዲደገም እንደማይፈቅድ ተናግረዋል። በዚህ ጊዜ አንድ የምክር ቤቱ አባል በቁጣ፣ እሳቸው በሕዝብ ባይመረጡ ኖሮ እዚያ ምክር ቤት እንደማይገኙና ነገር ግን በሕዝብ ስለተመረጡ የምክር ቤት አባል ሆነው በማገልገል ላይ መሆናቸውን ገልጸው ነበር። በእርግጥ እያንዳንዱ በግንቦት 2007 ምርጫ ተመረጠ ተብሎ ከፌዴራሉ እስከ ቀበሌ ባሉ፣ በተመራጮች በሚያዙ ቦታዎች ላይ የሚገኘው ሰው ሁሉ አንድ በአንድ ቢጠየቅ ተመሳሳይ መልስ እንደሚሰጥ አጠራጣሪ አይደለም። አጭበርብሬ ወይም ተጭበርብሮልኝ ለዚህ በቃሁ የሚል ግለሰብ ማግኘት ከባድ ሊሆን ይችላል።
ምርጫ ቦርድ በተቃዋሚነትም ይሁን በግል ተወዳዳሪነት ቀርበው የነበሩ ግለሰቦችና ቡድኖች እንዲሁም የየአካባቢው ሕዝቦች ባለፉት ምርጫዎች በተለይም በምርጫ 2007 የታዘቡትን መጥፎና አሳፋሪ አካሄድ፣ የደረሰባቸውን በደል በግልጽ አሳውቀው፣ ከዚያ አሳፋሪ ምርጫ ሊወሰድ የሚገባው ትምህርት ተወስዶ፣ ሊታረም የሚገባው ነገር ሁሉ ታርሞ ጥንቃቄ ካልተደረግ፣ ቀጣዩ ምርጫ ከችግሮች የጸዳ፣ ተአማኒና ፍትሐዊ የመሆን ዕድሉ በጣም የመነመነ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል። የሰው ሕይወት እስከ ማጥፋት በደረሰ ግፍ ምርጫውን ያጭበረበሩት ግለሰቦች ባሉበት ቀጥሉ ተብለው ምርጫ ማካሄድ፣ አደገኛ ነገር ነው። ለዓመታት ሰፍኖ የኖረው አጉል ልምድ አይደገምም ማለት ከባድ ስህተት ሊያስከትል ይችላል።
ምርጫ ቦርድ ልብ ይበላቸውም አይበላቸውም፣ ቀጣዩን ምርጫ አስቀድሞ የመቆጣጠርና ውጤቱን ከወዲሁ የመወሰን ሩጫዎች መታየት ከጀመሩ ሰነባብተዋል። ሩጫው የተጀመረው በአዲስ አበባ ይመስላል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብልጠት ይሁን ሽወዳ፣ ውሉ ባልለየለት አካሄድ፣ ድምጽ ሳያሰሙ (ለሕዝብ ይፋ ባልሆነ መንገድ) የአዲሰ አበባ ምክር ቤት አባል ያልሆነ ሰው ማለትም የአዲስ አበባ ሕዝብ ያልመረጠው ግለሰብ የአዲሰ አበባ ምክትል ከንቲባ የሚሆንበትም መንገድ አመቻችተዋል ኢንጅነር ታከለ ዑማን በሹመት አስቀምጠዋል። ይህን በማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መጭውን የአዲስ አበባ ከንቲባ እየወሰኑልን ሊሆን ይችላል።
ምንጩ ይፋ ባልተደረገ ገንዘብ ምክትል ከንቲባውን በየሰው ልብ ለማስቀመጥ ከፍተኛ ሥራ እየተሠራ ያለው፣ አስጎምዥ ሸገርን ማስዋቢያ የልማት ዕቅዶች አንዱ በአንዱ ላይ እየተደራረበ ይፋ የሚደረጉት፣ እዚህም እዚያም የአንዳንዶች ሥራ ተጀምረ ተብሎ ቁፋሮዎች የሚታዩት ኢንጂነሩን ‘ፈረስ ያደርሳል እንጅ አይዋጋም!’ ባይ መራጭ ወይም አስመራጭ ሆነው ዳር ሊቀሩ አይደለም። እንዲያውም ለአዲሰ አበባ ምክር ቤት ባይወዳደሩም ወይም ተወዳድረው ቢሸነፉም የተሻሻለው ቻርተር ከምክር ቤቱ ውጭ ለሆነ ሰው የያዙትን ሥልጣን የማይነፍግ ነውና፣ ዕድሜ ለዐብይ አሕመድ ብለው ዘና ማለት ይችላሉ። እንዲህ ከሆነ ደግሞ ይህ አካሄድ ያለ ዐቢይ አሕመድ የሚሳካ አይመስልምና ‘ዐቢይና ብልጽግና ፓርያቸውስ እንዴት ያደርጋሉ?’ የሚል ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ይሆናል።
ዐቢይ መመረጥ አለባቸው፣ ጅማ ውስጥ በአንድ ወረዳ ተመርጠው ቢመጡም ምክር ቤቱ በብልጽግና ሰዎች የበላይነት ካልተያዘ ጠቅላይ ሚኒስትርነትን አያገኙም። ስለዚህ መጠነ ሰፊ ሥራ ያስፈልጋል። ይህ ሥራ ሕጋዊ መሆንና አለመሆኑን እግር በእግር የመከታተሉ ጉዳይ በዋነኛነት የምርጫ ቦርድ ኃላፊነት ነው። ምርጫ ቦርድ ይህን ኃላፊነቱን በተገቢው መንገድ መወጣት የሚችለው ገና ከአሁኑ የክትትል እና የጥንቃቄ ሥራዎቹን መሥራት ሲችል ብቻ ነው። ብልጽግና ፓርቲን ከተወዳዳሪዎች እንደ አንዱ ብቻ አድርጎ የሚያይ መሆኑን ማስመስከር ይጠበቅበታል። የጠቅላይ ሚኒስትሩንም ሆነ የሌሎች የብልጽግና ፓርቲ ባለሥልጣናትን ሐሳብ እየተቀበለ የምርጫ ቦርዱ መመሪያ ከማድረግ መቆጠብ አለበት። አሁን በመላ አገሪቱ ለሚታዩ ችግሮች መፍትሔ ለማግኘት መጨነቅ ሳያስፈልግ ምርጫ የሚካሄድ ከሆነ፣ ምርጫው ከተገቢው መንገድ ውጭ እንዲካሄድ የሚወሰነው በብልጽግና ፓርቲ ካድሬዎች ብቻ ሳይሆን በየከተማው፣ በየመንደሩ በየጎጡ ራሳቸውን ከሕግ በላይ በሚያደርጉ ወገኖች ፍላጎት ጭምር የመሆኑ ዕድል በጣም የጎላ ነው።
በገዥው ቡድን ላይ ‘የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች!’ የሚባለው ተረት ሊደርስበት ይችላል። ከአዲስ አበባ ቀጥሎ ምርጫውን የመቆጣጠር ትልቅ ሥራ በመሠራት ላይ ያለው ሕወሐት በሚወዳርበት በትግራይ ነው። ሕወሐት በትግራዩ የምርጫ ሜዳ ላይ እውነተኛ ተቀናቃኞች እንዳይኖሩ የማድረግ ሥራወቹን ከጀመረ ሰነባብቷል። ብልጡ ሕወሐት የቀጣዩን ምርጫ አቅጣጫ በመቆጣጠር ሳይገታ ውጤቱን ተገማች በማድረግ ላይ ያለም ይመስላል። በታኅሣሥ ወር መጨረሻ ላይ የጠራውን አስቸኳይ ስብሰባ ተከትሎ ልቡ የተዘጋጀ መሣሪያ ነው። ከፎረሙ አካሄድና አደረጃጀት አንጻር ሕወሐት መቶ በመቶ ማሸነፍ እንዳልፈለገ መገመት ይቻላል።
ሕወሐት ምርጫውን ወደ ቅርጫ ይቀይረውና ጥቂት የአሸናፊነት ቦታዎችን ለታማኝ ተቃዋሚ ድርጅቶችና ለግል ተወዳዳሪወች በመልቀቅ የአንበሳውን ድርሻ እሱ ይወስደዋል። የዐቢይ አሕመድ መንግሥትና ምርጫ ቦርድ፣ ወደዱም ጠሉም ምርጫው ጊዜውን ጠብቆ በትግራይ እንደሚካሄድ ሕወሐት ቀደም ብሎ አሳውቋል። በዚህ ዓመት ምርጫ ሳይካሄድ በሥልጣን ላይ መቀጠል ሕገ-ወጥነት ነው የሚል ድምዳሜ ላይ የደረሰው ሕወሐት፣ በአስቸኳይ ስብሰባው የተለየ ነገር አላሳወቀምና በቆየው አቋሙ እንደ ጸና መገመት ይቻላል። ሕወሐት በአስቸኳይ ስብሰባው ኹለቱ መንግሥታት (የብልጽግና ፓርቲና የሕወሐት መንግሥታት) በሚስማሙበት አብረው እየሠሩ፣ በማይስማሙበት ደግሞ ተለያይተው እንደሚቀጥሉ ተናግሯልና፣ ቀጣዩ ምርጫ በልዩነት ከሚካሄዱ ጉዳዮች ውስጥ አንደኛው ሊሆን ይችላል። ሕወሐት ወደ ቀሪው የኢትዮጵያ ክፍል ምርጫ ላይ ከወዲሁ የመወሰን እጁን ለመላክም እየሞከረ ነው።
በስውር የሚሠራው ባይታወቅም፣ በይፋዊ አካሄዱ ግን በርካታ ብሔረሰቦችን የሚወክሉ ያላቸውን ከ40 በላይ ፌደራሊስት የፖለቲካ ቡድኖች መቀሌ ላይ በፎረም አሰባስቦ ‘የኅብረ ብሔር ፌደራሊስት ኃይሎች ጥምረት ለአገራዊ መድኅን’ በሚል ሥያሜ አብረው ለመሥራትና በምርጫውም አብረው ለመካፈል ለፊርማ ማብቃቱን አሳውቋል። የጥምረቱ ፕሬዘደንት የኦሮሞ ነጻነት ንቅናቄ ሊቀመንበር ናቸው የተባሉት ደረጀ በቀለ ሲሆኑ፣ ደረጀ ‹‹የሕወሐት አገልጋይ ሳንሆን ፌዴራሊዝምን ለማስቀጠል የቆምን ኃይሎች ነን›› ሲሉ ተደምጠዋል። አማራ ክልልም ምርጫውን አስቀድሞ የመወሰን ሥራ የሚሠራበት ክልል ነው።
በዚህ ክልል ምርጫውን የመወሰን ጨዋታውን የጀመረው አብን የተሰኘው አዲስ መጤ ቡድን ነው። አብን መጀመሪያ ላይ አማራ ክልል ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎችን ለመወሰን (የሚፈቀድላቸውና የማይፈቀድላቸው) የሚዳዳው ንግግር መብዛቱና ብሎም ግልጽ የድፍረት ሥራዎችን መሥራቱ የአደባባይ ምስጢር ነው። ራሱን የአማራ ሕዝብ ብቸኛ ወኪል አድርጎ የሚያቀርበው አብን፣ አንዳንድ ፓርቲዎችን በይፋ የአማራ ሕዝብ ጠላቶች ብሎ ፈርጆ በአማራ ክልል እንዳይንቀሳቀሱ ለማድረግ በከፍተኛ ደረጃ መሞከሩም ሁሉም የሚያውቀው ጉዳይ ነው። ራሱን ብአዴንን/ አዴፓን (የአሁኑን የአማራ ብልጽግና ፓርቲን) በንቅናቄውና በሕዝብ ጠላትነት ፈርጆ የሚያብጠለጥለው አብን፣ ተከፋፍለው በስውር ሲሻኮቱ በነበሩት የአማራ ክልል ባለሥልጣንት መካከል እጁን ወይም ዓላማውን የማስገባት ዕድል አላገኘም ብሎ ማሰብ ትልቅ መዘናጋት ሊሆን ይችላል። አብን አጠያያቂ የሆኑ፣ ለነጻና ፍትሐዊ ምርጫ ተጻራሪ የሆኑ ኹለት ሥራወችን ትኩረት ሰጥቶ በገሃድ ሲሠራ የታየባቸው ጊዜያት ነበሩ።
እነዚህ ሥራዎች አንደኛ አዴፓ (የአማራ ብልጽግና ፓርቲ) ዘላለማዊ የአማራ ሕዝብ ጠላት እንደሆነ አድርጎ መስበክና ሲሆን ኹለተኛው አገር አቀፍ ወይም ኢትዮጵያዊነትን የሚሰብኩ ፓርቲዎችንም አማራን የሚከፋፍሉ የአማራ ጠላቶች አድርጎ መፈረጅ ናቸው። አሁን አሁን እነዚህ አካሄዶች ቀዝቀዝ ያሉ ቢመስሉም አብን ጉዳዮቹን የውስጥ ለውስጥ ሥራዎች አድርጓቸው መሆኑን ወይም አብን ለባህሩ እንግዳ የሆነ መርከብን እንደሚያነጉድ የውሃ ስር ዓለት አድፍጦ እየተጠቀመባቸው መሆንና አለመሆኑን ጊዜ ግልጽ ያደርግልናል።
አሁን ግን ‘… አማራ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ሲል ነው ጠላት ያበዛው… ኢትዮጵያዊነትህን ወዲያ ጣልና አማራነትህን አጥበቀህ ያዝ…’ እያሉ ሲቀሰቅሱ የነበሩት ምላሶች ጸጥ ያሉ ይመስላል። ኢዜማ በባህርዳር እና በደብረ ታቦር ላይ የጠራቸው ስብሰባዎች በስኬት ሊካሄዱ ይቅርና ተገቢውን ቅስቀሳና ጥሪ ማድረግ ባልተቻለባቸው አጋጣሚዎች የታጠረ ነበር። የባሕርዳሩን ስብሰባ ለመምራትና ለመካፈል ወደ ከተማው የተጓዙ የኢዜማ አመራሮች፣ ችግር ሲገጥማቸው ወደ አማራ የጸጥታና የደኅንነት፣ ወደ አማራ ልዩ ኃይል ጽሕፈት ቤት በመሄድ አቤት ብለው ነበረ። በዚህ ጊዜ የተሰጣቸው መልስ የስብሰባዎች መከልከል የእነዚህ መሥሪያ ቤቶች ፍላጎት ጭምር እንደነበረ የሚያሳብቅ ዓይነት ነው። የእነዚህ መሥሪያ ቤቶች ኃላፊዎች “…ምንም ማድረግ አይቻልም፣ የፖለቲካ ውሳኔ ነው…” የሚል ምላሽ እንደሰጧቸው አንዱዓለም አራጌ በአንድ ቃለ ምልልሳቸው ላይ ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ባለሥልጣናት ድብቅ ክፍፍል ወደ መገዳደል አድጎ፣ በደም በጨቀየ አሳዛኝ ድርጊት ለሕዝብ ይፋ ከሆነ በኋላ ለውጥ ይኖር ይሆን? ክልሉ ለሁሉም ዓይነት ተወዳዳሪዎች እኩል መፎካከሪያ ሜዳ ለማዘጋጀት ቆርጦ የተነሳ አስተዳደርና የጸጥታ መዋቅር ዘርግቶ ይሆን? አብን በአማራ ክልል እዚህ ግቡ የሚባሉ ሁሉን አቀፍ (ከሁሉም የዕድሜ ክልልና ከሁሉም የኑሮ ዘርፍ…የተውጣጡ ታዳሚዎች የተገኙባቸው) ስብሰባዎችን አካሂዶ ባያውቅም ንቅናቄው በአማራ ክልል ምርጫ በከፍተኛ ልዩነት እንደሚያሸንፍ በደጋፊዎቹ አማካኝነት አውርተው በማስወራት ላይ ናቸው።
ለመሆኑ አብን በምርጫው የጠበቀውን ያህል ድምጽ ባያገኝ ውጤቱን አሜን ብሎ ለመቀበል የሚያስችል የሥነ ልቦና ዝግጅት አለውን?የፈቀዳቸውን ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሲቪክ ማኅበራት፣ ታዋቂ ግሰለቦችን ወዘተ… በፎረም አደራጅቷል። ይህ የተጋሩ ፎረም ምርጫውን ለመወሰን በአንድ ወቅት አብን በደብረ ማርቆስ አንድ ስብሰባ አካሂዶ ነበር። በስብሰባው ብዙ ጥያቄዎችን የሚያጭረው የአብን መዝሙር ተዘመረ። አብን አማራ ነውና ከዚህም በተጨማሪ ለሌሎች ሕዝቦች ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊነቴን አስቀድማለሁ ለሚል አማራም ጠላት ለመሆን የሚዳዳው ቡድን ነውና፣ የመዝሙሩ ቅኔ ሲፈታ የአክሱም ሃውልትን፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን የሠራን እኛ ነን ሲል፣ አገውና ትግሬ ለሆኑት ሕዝቦች ብቻ ሳይሆን ለሌላው አማራም ጥያቄን መጋበዙ ግድ ነው።
በደብረ ማርቆሱ ስብሰባ መገባደጃ ላይ ስብሰባውን የሚመሩት ወጣቶች፣ ታዳሚዎች ይህንኑ መዝሙር ይዘምሩ ዘንድ አዘዙ። እጅ ለእጅ መያያዝ እንደሚገባም በትእዛዝ መልክ ተነገረ። ከፊት ለፊት የተቀመጡ ብዙ ትልልቅ ሰዎች እጅ ለእጅ አልተያያዙም ነበር፣ መዝሙሩንም አልዘመሩም። ይኸኔ ከመድረኩ ላይ ካሉት ወጣቶች አንዱ ‘እጅ ለእጅ ያልተያያዘ የአማራ ጠላት ነው’ ሲል አምባረቀ። ለመሆኑ አብን ይህን መሰሉን አሸማቃቂ ስትራቴጂ ይዞ ነው ወደ ምርጫ የሚገባው? በአማራ ክልል ምርጫውን አስቀድሞ የመወሰን ሥራ የሚሠራው በአብን ብቻ አይደለም። የብልጽግና ፓርቲን መወለድ ተከትሎ የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ምርጫውን ከመወሰን አልፎ በእጅ የማስገባት ሥራ ለመጀመር ዳር ዳርታ እየታየበት ነው።
በክልሉ የመደመር ጽንስ ሐሳብን በሚመለከት የሚደረጉ የአባላት ውይይቶች ብዙ ጥያቄዎችን ማስተናገዳቸውና ብዙዎቹ መልሶች በደፈናው ‘…ከመደመር ውጭ ሌላ መስመር የለንም፣ ማሸነፍ የምንችለው በመደመር እሳቤ ነው፣ በቀጣዮቹ ዐስር ዓመታት አገሪቱንም ሆነ ሕዝቡን ማበልጸግ የሚቻለው በመደመር ፍልስፍና ነው…’ የሚሉ ዓይነት መሆናቸውና ከረር ያለ ክርክር ያነሱ ወገኖች ግልምጫ ሊሰነዘርባቸው ሙከራ መደረጉ ይነገራል። ውይይቱ በደፈናው ‘ተቀበል!’ በሚል ዓይነት የአዝማሪና የግጥም አቀባይ ግንኙነት መስመርን የተከተለ ነበር። ቅሬታ የተሰማቸው ብዙዎች እንደሆኑት ሁሉ በዚህ የመታጀል አካሄድ በመሄድ በአገር አቀፍ ደረጃ ተረባርቦና ተግባብቶ ምርጫውን ማሸነፍ እንደሚቻል ተንብየው የፈነጠዙም አሉ።
ይኸኛው አካሄድ ‹ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ቆራጥ አመራር ጋር ወደፊት!› የሚል ዓይነት አንደምታ ያለው ነው። ነገሩ በሕወሐት ቤት ‘መስመር ኃይልና’ (ኃይላችን መስመራችን) ተብሎ ለአብዮታዊ ዴሞክራሲ ታማኝነት እንደሚዘመረው ሁሉ፣ በአማራ ብልጽግና ፓርቲ ውስጥም ኃይላችን መደመራችን እየተባለ መዘመር ተጀምሯል ማለት ይቻላል። በአፋር ክልልም ለየት ያለ አካሄድ ይታያል። በእርግጥ በዚህ ክልል ነገሮችን ለመቆጣጠርና ለራስ በሚጠቅም መንገድ ለማስወሰን ጥረት የሚደረገው በሕወሐት ነው። ሕወሐት ከክልሉ አልፎ ወደ አፋር ክልልም እጁን እያስረዘመ ነው። የፌዴራሉ ጌታቸው አሰፋ ክልላዊ አምሳያ የሆኑት ተክኤ፣ በአካል ወይም በወኪል አፋር ክልልን ሳይጎበኙ የቀሩበት ጊዜ የለም።
በኢሕአዴግ ውስጥ ልዩነቱና ክፍፍሉ እየሰፋ በመጣበት ጊዜ፣ ሕወሐት አጋር ፍለጋ መጀመሪያ ዐይኑን የወረወረው ወደ አፋር ነበር። ብልጽግና ፓርቲ በአፋር መሰረት እንዳይተክል ብዙ ሕወሐት መራሽ ስብሰባዎች መካሄዳቸው እየተሰማ እንደነበረ የሚዘነጋ አይደለም። አዲስ ማለዳ ጋዜጣ በጥር 2/2012 እትሟ ላይ ለንባብ ያበቃችው ዜና በግልጽ እንደሚያሳየው በቤኒሻንጉል ክልልም ተመሳሳዩ ምርጫzz የመወሰን ሥራ እየተሠራ መሆኑን መረዳት ይቻላል። ይህ ክልል ተመሳሳይ ሥራዎችን ምርጫዎች በመጡ ቁጥር መሥራቱ የሚረሳ አይደለም። የክልሉ ገዥ ፓርቲ አዲሰ ፓርቲ ሊመሠርቱ የተነሱ ሰዎችን እየተከታተለ ሊያሰናክል መሞከሩ ገሃድ እየወጣ ነው። የክልሉ ገዥ ቡድን ይህን የሚያደርገው አዲሱ ፓርቲ ይነጥቀኛል ያለውን የሽናሻ ሕዝብ ድምጽ ላለማጣት ሲል ነው ብሎ መገመት ቀላል ነው።
ፓርቲ ለመመሥረት የተነሳሱ ሰዎችን አርፋችሁ ተቀመጡ ወይም ለእኛ እጅ ስጡና የምንሰጣችሁን ተቀበሉ እያለ ነውና ይህ አካሄድ ምርጫውን በእጅ ለማስገባት ያለን ጉጉት የሚያሳይ ነው። ጉጉቱ አደገኛም ነው። ምክንያቱም አዲስ ፓርቲ ለመመስረት የተነሳሱትን ሰዎች አንድ ጊዜ ዩንቨርስቲ በመበጥበጥ ተጠርጥራችኋል ብሎ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ባለሥልጣኔን ገድላችሁብኛል እያለ ሊወነጅላቸው እየሞከረ ነውና፣ ከውንጀላዎቹ ክብደት አንጻር ሲታይ በቤኒሻንጉል ክልል የተጀመረው አካሄድ ሕወሐት በትግራይ ካወጀው ሰይፍ ተመዟል የሚል ዓይነት የአደገኛ ጠላትነት አቋም ጋር የሚመሳል ነው። በኦሮምያ ጥር ወር ግም ከማለቱ የምርጫ ቅስቀሳ ተጀምሯል። ኦፌኮ፣ ኦነግና ብዙም የማይታወቀው ኦብፓ (የኦሮሞ ብሔራዊ ፓርቲ) በሦስት ተከታታይ ቀናት የምሥራቅ ኢትዮጵያ ከተሞች በሆኑት በጭሮ፣ ሂርና፣ ሐረርና ድሬዳዋ ከተሞች እና በአዲስ አበባ ትልልቅ ስብሰባዎችን አካሂደዋል።
በዘመቻ መልክ ያካሄዷቸው ስብሰባዎች ዓላማ የምርጫ ቅስቀሳ ብቻ ሳይሆን አመራሮች ከሕዝብ ጋር ለማስተዋወቅ፣ የሕዝቡን ንቃተ ሕሊና ለማስፋት፣ ተጨማሪ አባላትን ለመመልመል ጭምር መሆኑን ጃዋር መሐመድ አሳውቋል። አዲስ አበባም የዘመቻው ዒላማ ነበረችና ተመሳሳዩን ስብሰባ በሚሊንየም አዳራሽ አስተናግዳለች። ተመሳሳይ ዘመቻዎች በተለያዩ የኦሮምያ ክፍሎች በተከታታይ እንደሚካሄዱም ይጠበቃል። ለዶቸቨለና ለቪኦኤ አስተያየታቸውን የተቀበሉ አንዳንድ ታዛቢዎች፣ ‘እነ ኦፌኮ ቸኮሉ’ ሲሉ ቢሰሙም ኦፌኮን በቅርቡ የተቀላቀሉት ጃዋር ‘እንዲያውም ዘግይተናል’ ሲሉ በቅድመ ምርጫ ዘመቻው መጀመር ተገቢነት ላይ ተከራክረዋል። በዘመቻው መረራ ጉዲና (ዶ/ር) እና ጃዋር መሐመድ በምሥራቅ ኢትዮጵያ፣ በቀለ ገርባና ዳውድ ኢብሳ በአዲስ አበባ ማሰማራታቸው የዘመቻውን ክብደት የሚያሳይ ነው።
ይህ ዘመቻ ምርጫውን ለመቆጣጠር ከሚደረጉ ሙከራዎች ሁሉ ሕጋዊና ተቀባይነት ያለው ቢመስልም ወቅቱን ያልጠበቅ፣ በምርጫ ቦርድ ቅስቀሳ እንዲጀመር በይፋ ሳይነገር የተካሄደ ነው የሚል ወቀሳ እየተሰነዘረበት ነው። ይህ የሦስት የኦሮሞ ፓርቲዎች የተባበረ አካሄድ፣ በኦሮምያው ብልጽግና ፓርቲ ላይ ከፍተኛ ድንጋጤንና ጫናን የሚፈጥር መሆኑን የጠቀሱ ታዛቢዎች በክልሉ ከፍተኛ የምርጫ ፉክክር ሊኖር እንደሚችል ተንብየዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ከመሪዎቹ አንደበት ጥቂት የማይባሉ አነጋጋሪ፣ አጠያያቂና ስሜታዊ ንግግሮችም መደመጣቸው ግርታን የሚፈጥር ሆኗል። በቀለ ገርባ ከስድስት ወራት በኋላ መንግሥት ነን ሲሉ በእርግጠኛት ተናግረዋል።
በቀለ የኦሮሞ ሕዝብ ዘርፎት የሚሄድ፣ ማንነቱንና ቋንቋውን የሚያጠፋ፣ የሚጨቁነውና አንገቱን ስብሮ እንዲኖር የሚያደርገውን መንግሥትን ብቻ እያስተናገደ መኖሩን ተናግረው፣ አሁን ግን የኦሮሞ ሕዝብ የራሴ የሚለውን መንግሥት እንደሚያገኝ፣ ይህ እውነተኛ የኦሮሞ መንግሥት የኦሮምያን ምድር ሁሉ በኦሮምያ ክልል ወስጥ አጠቃልሎ የኦሮምያን ድንበር አስከብሮ እንደሚኖር አስረግጠው ተናግረዋል። አዲስ አበባን የሚያጠቃልለውን የኦሮምያ ድንበር የማስከበሩ ሐሳብ በመረራ ጉዲና (ዶ/ር) ንግግርም ተወስቷል።
እነዚህ አነጋሮች ዘመቻውን የምርጫ ቅስቀሳ የሚደረግበት ሳይሆን የኦሮምያ ሪፐብሊክን ለመመስረት ለሚካሄድ ሪፈረንደም ሕዝብን የማነሳሳት ዘመቻ የሚካሄድበት አስመስለውታል። አፋን ኦሮሞን የፌዴራል የሥራ ቋንቋ ማድረግም በንግግሮቹ ውስጥ ትኩረት የተሰጠው ነጥብ ነበር። በቀለ የራሳችን መንግሥት እንመሰርታለን ሲሉ፣ ከሕወሐት ‘ኹለት መንግሥታት’ የሚል አባባል ጋር የሚመሳሰል ነበርና ቆጠራው ‘ሦስቱ ተገዳዳሪ መንግሥታት’ ወደሚል እንደሚያድግ ያሳያል። ዳውድ ኢብሳ የፊንፊኔ በኦሮምያ ክልል ውስጥ መጠቃለል ዕውን እንደሚሆን ገልጸው፣ የፊንፊኔ በኦሮምያ መንግሥት ስር መግባት ለኦሮሞውም ሆነ ለሌላው ሕዝብ ያስገኛል ያሉትን ጥቅም ለማስረዳት ሞክረዋል።
ዳውድ ኢብሳ መሬትም ለሕዝብ ይመለሳል ካሉ በኋላ፣ መሬት በክልል መንግሥት አጅ ውስጥ እንጅ በፌዴራል መንግሥት እጅ ውስጥ መሆን የለበትም ብለው አደናጋሪ ንግግር አሰምተዋል። የክልል መንግሥት እንጅ የፌዴራል መንግሥት መሬት የለውም ሲሉም ተደምጠዋል። የጃዋር መሐመድ ንግግር ጥንቃቄ የተሞላበት ነበር ማለት ይቻላል። ከወደዳችሁን ድምጻችሁን ስጡን፣ ድምጸችሁን ስጡንና እንምራችሁ ሲሉ ተደምጠዋል። ‘ድንጋይ ሳይወረወርና ጥይት ሳይተኮስ፣ በዘመናዊ መንገድ የሥልጣን ሽግግር የሚደረግባት አገር እንድትኖረን እየሠራን ነው’ ያሉት ጃዋር፣ ሕዝብ ከሚገባው በላይ መስዋዕትነት ከፍሏልና ሁሉም ምርጫው በሰላማዊ መንገድ እንዲካሄድ በርትቶ እንዲሠራ ጠይቀዋል።
አክለውም ‘ኖቤል የተሸለምነው ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ስላደረግን ነውና ይህን ክብራችንን ማስጠበቅ አለብን’ ሲሉ ተሰምተዋል። ይህን በተዘዋዋሪ መንገድ ብልጽግና ፓርቲ በቀጣዩ ምርጫ እንደሚሸነፍ አውቆ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ለማድረግ እንዲዘጋጅ ማሳሰቢያ እንደሰጡ አድርጎ መቁጠር ይቻል ይሆን? እንግዲህ ይህን ሁሉ ተገቢና ተገቢ ያልሆነ ምርጫን የመቆጣጠርና የምርጫን ውጤት የራስ የማድረግ ዘመቻ መከታተል፣ የሚገሰጸውን መገሰጽ፣ የሚበረታታውን ማበረታታት ያለበት የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ነው። ምርጫ ቦርድ ለማንም ለምንም አድርባይ ሳይሆን ኃላፊነቱን ለመወጣት ቆራጥ መሆን ይጠበቅበታል።
ቦርዱ የተሸከመው ኃላፊነትና የሕዝብ አደራ በጣም ከባድ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም። ምርጫ ቦርድ ብርቱካን ሚዴቅሳን በመሰሉ በምርጫ ሂደት የቆሰሉ፣ የገዥውን ቡድን ጡንቻ የቀመሱ ተጠሪ ማግኘቱ ተስፋን የሚሰጥ ነው። በአንጻሩ የምርጫ ግርግሮችን፣ ምርጫውን ተከትለው የሚመጡ ግፎችንና መከራዎችን በአገር ቤትና በውጭ ሆነው በቴሌቪዥን መስኮት ሲከታተሉ የነበሩ ግለሰቦችም ተጨምረውበታልና፣ ቦርዱ የጥንቃቄ ሥራዎችን መሥራት የሚጀምረው ስልጣኑንና ኃላፊነቱን ለአባላቱ አበክሮ በማስገንዘብ መሆን አለበት። የምርጫ ችግሮችን በጋቢ ተሸፋፍኖ፣ ቤት ውስጥ ተቀምጦ፣ በቴሌቪዥን መስኮት መከታተልና የቦርዱ ሠራተኛ ተሁኖ መሰል ጉዳዮችን መከታተል ተመሳሳይ ነገሮች አይደሉም። ኃላፊነትም፣ ተጠያቂነትም ይኖራል።
ምርጫ ቦርድ ነሐሴ 10/2012 የቀጣዩ ምርጫ ቀን እንዲሆን ጊዜያዊ ቀን አስቀምጧል። ቀኑ በብዙ ተፈጥሯዊና አገራዊ ምክንያቶች ሊጸና የማይችል ነው። ምርጫው መቼም ይሁን መቼ ቦርዱ ሥልጣኑን በአግባቡ መጠቀምና ኃላፊነቱን በሚገባ መወጣት የሚችለው ለሚከተሉት ጥያቄዎች ተገቢው መልስ መስጠት ከተቻለው ብቻ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባውም።
ለመቆጣጠር በጣም ቀላል በሆኑት የኢትዮጵያ ስቴዲዮሞችና ዩንቨርሲቲቆች ሲታዩ የነበሩትና አሁንም የሚታዩት ሁከቶች ምርጫ ቦርድ ከተሞችና የገጠር መንደሮች በሚቋቋሙ በመቶዎች የሚቆጠሩ የምርጫ ጣቢያወች ሥራውን በአግባቡ መወጣት እንደሚችል የሚናገሩ ናቸውን? የመንግሥት መዋቅሮች፣ ሰላምና ደኅንነትን የማስፈን እንዲሁም ሕገ ወጦችን አደብ የማስገዛት ግዴታ ያለባቸው ወገኖች ምርጫ ቦርድ ሥራውን በነጻነትና በሙሉ ድፍረት እንዲሠራ የሚያስችል ቁመና አላቸውን? ሕገ-ወጥ አደረጃጀቶችን ወደ ሕጋዊና ሰላማዊ አደረጃጀት በመለወጡ ሥራ በትኩረት ሳይሠራ ሕግን የሚያስከብር መንግሥት በሁሉም ቦታ አለ ማለት ይችላልን? የገዥው ቡድን፣ የተቃዋሚ ቡድኖችና የግል ተወዳዳሪዎችስ ወደ የትኛውም የአገሪቱ ክፍሎች እየሄዱ፣ ያሻቸውን ባንዲራና ምልክት (ዓርማ) እየተጠቀሙ (እያውለበልቡ)፣ ዓላማቸውን ያለ ምንም መሸማቀቅ እያሳወቁ፣ በነጻነት ቅስቀሳ የማድረግና የመወዳደር መብታቸው እንዲጠበቅ ማድረግ ይቻላልን? ምርጫ ቦርድ ራሱ ሊወስን የሚገባውን ነገር ራሱ ይወስናል ብሎ ሕዝብ ይጠብቃልና፣ ገለልተኝነቱን ጠብቆ በሃቅ ይሥራ።
ግዛቸው አበበ [email protected]
ቅጽ 2 ቁጥር 64 ጥር 16 2012


