የውጪ ሀገር ዜጎች የፖለቲካ ተሳትፎ ከኢትዮጵያ ሕግ አንፃር

0
977

ከሰሞኑ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ አባል ሆነው መቀጠል ይችላሉ አይችሉም የሚሉ ክርክሮ ሲነሱ ሰንብተዋል፡፡ የኢትዮጵያ
ሕገ መንግሥት የመምረጥ እና መመረጥ መብትን ለኢትዮጵያውያን ብቻ ያረጋገጠ ቢሆንም የፖለቲካ ፓርቲ የመመስረት እና አባል የመሆን መብትን
ያቀፈውን የመደራጀት መብት የውጪ አገር ዜጎችንም ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ አስቀምጧል ሲሉ የክርክሩን ሁለት ፊቶች የህግ ባለሞያው ሚኒሊክ
አሰፋ ይያስረዳሉ፡፡

የፖለቲካ ተሳትፎ የፖለቲካ ሥልጣን ለመያዝ የሚደረጉ የምርጫ ውድድሮች ላይ መራጭ ሆኖ ከመሳተፍ ጀምሮ የፖለቲካ አቋም ይዞ ፓርቲዎችን መደገፍ፣ አባል መሆን፣ መመስረት፣ ለምርጫ መወዳደር እና ፖለቲካዊ በሆኑ የመንግሥት ሥራዎች ላይ ተሹሞ መሥራትን የሚያጠቃልል ሰፊ መብት ነው። አገራት ዜጎቻቸው ሉዓላዊ መሆናቸውን ከሚያሳዩባቸው መንገዶች አንዱ ይህንን መብት ለዜጎቻቸው ብቻ ከልሎ በማስቀመጥ ነው። ይህም በዛች አገር ውስጥ የፖለቲካ ሥልጣን በአገሪቱ ዜጎች ብቻ የሚያዝ እና የሚወሰን መሆኑን በማረጋገጥ የዜጎችን ሉዓላዊነት የሚያስከብር መሆኑ ይታመናል። አገርን አገር የሚያሰኘውም ቀዳሚው ነገር ለዜጎች ብቻ የተከለለ መብት እና ግዴታ በማስቀመጥ ለአባላቱ (ለዜጎቹ) ብቻ የሚሠራ መንግሥታዊ ሥርዓት መዘርጋቱ ነው።

ለማሳያነት የአሜሪካ ሕገ መንግሥት የሕዝብ ተወካዮች እና የላይኛው ምክር ቤት አባል ሆኖ ለመመረጥ አሜሪካዊ ዜጋ ከመሆን ባለፈ በቅደም ተከተል ለሰባት እና ለዘጠኝ ዓመታት የአሜሪካ ዜጋ ሆኖ መገኘትን እንደ ቅድመ ሁኔታ ያስቀምጣል። ከአንድ በላይ ዜግነት መያዝን (dual or multiple citizenship) የሚፈቅዱ አገራት ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች መምረጥ ቢችሉ እንኳን በምርጫ ውድድር እንዳይሳተፉ ክልከላ ያደርጋሉ። በአውስትራሊያ ኹለት ዜግነት መያዝ የተፈቀደ ቢሆንም ሕገ መንግሥቱ ተጨማሪ ዜግነት ያላቸው ሰዎች ለፓርላማ መወዳደር እንደማይችሉ ይደነግጋል። ይህ ሁሉንም ከአንድ በላይ ዜግነት የሚፈቅዱ አገራት የሚመለከት አይደለም። በተወሰኑ ሁኔታዎች ኹለት ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች የምክር ቤት አባል ሆነው የመመረጥ መብት እንዲኖራቸው የሚፈቅዱ እንደ ኒውዚላንድ ያሉ አገራትን መጥቀስ ይቻላል።

ነገር ግን ዜጋ ላልሆኑ ሰዎች የተሻለ መብት የሚሰጥ ተራማጅ የምርጫ ሕግ ያላቸው አገራትም አሉ። ኒውዚላንድ ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸው የውጪ አገራት ዜጎች የመምረጥ መብት እንዲኖራችው አድርጋለች። የውጪ አገር ዜጎችን የፖለቲካ ተሳትፎ የሚመለከተውን የስትራትስበርጉን ስምምነት የፈረሙ የአውሮፓ ካውንስል አባል አገራት፤ ከተወሰኑ ዓመታት በላይ በአገራቸው የቆዩ የውጪ አገራት ዜጎች በአካባቢያዊ ምርጫዎች ላይ የመምረጥም ሆነ የመመረጥ መብት እንዲኖራቸው አድርገዋል። ካናዳ፣ ዴንማርክ፣ ፊንላንድ፣ አውስትራሊያ፣ እስራኤል እና ስዊዘርላንድ ደግሞ የውጪ አገር ዜጎች በክልላዊ ወይም አካባቢያዊ ምርጫዎች ላይ እንዲሳተፉ የሚፈቅዱ አገራት ናቸው። ይህም ከፍተኛ ልምድ እና ብቃት ያላቸው ስደተኞች በቋሚነት በሚኖሩበት አገር ውስጥ ያሉ የከተማ አስተዳደሮች ውስጥ አዎንታዊ አስተዋጽዖ እንዲያደርጉ ያስችላቸዋል።

ሆኖም የውጪ ዜጎች እና ኹለት ወይም ከዚያ በላይ ዜግነት ያላቸው ሰዎች የፖለቲካ ተሳትፎ ሊገድብ ይገባል ወይስ አይገባም፣ ከተገደበስ በምን ደረጃ ሊሆን ይገባል የሚለው ጉዳይ በብዙ አገራት ትልቅ የመከራከሪያ ነጥብ ሆኖ ቀጥሏል። ኢትዮጵያ ውስጥ በሥራ ላይ ባሉ ሕጎች መሠረት የውጪ አገር ዜግነት ያላቸው ሰዎች የፖለቲካ ተሳትፎ የማድረግ መብት እስከምን ድረስ ነው የሚለውን ሕገ መንግሥቱ ላይ ካሉ ድንጋጌዎች በመነሳት መተንተን እንችላለን። እዚህ ጋር ልብ መባል የሚኖርበት ጉዳይ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት መሠረታዊ መብቶች እና ነፃነቶችን በደነገገበት ምዕራፍ ሶስት ውስጥ ሁለት ዓይነት የመብት ድንጋጌዎች አሉ። የመጀመሪያው የድንጋጌ ዓይነት መብትን ለውጪ አገራት ዜጎች ጨምሮ ለማንኛውም ሰው የሚሰጥ ሲሆን “ማንኛውም ሰው” በሚል ሀረግ የሚጀምር ነው። ሁለተኛው ደግሞ መብት ለኢትዮጵያዊያን በብቸኝነት የሚሰጥ ሲሆን “ማንኛውም ኢትዮጵያዊ” ወይም “ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ” በሚል ሀረግ ይጀምራል። በሕይወት የመኖር፣ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ፣ የመሰብሰብ፣ የመደራጀት እና መሰል መብቶች ለ “ማንኛውም ሰው” የተረጋገጡ እና ኢትዮጵያውያንን እና የውጪ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ መብቶች ናቸው።

በሌላ በኩል የንብረት ማፍራት መብት፣ የመሥራት፣ የልማት እና መምረጥ እና የመመረጥ መብቶች ለዜጎች ብቻ የተረጋገጡ መብቶች ሆነው ተቀምጠዋል። የሕገ መንግሥቱን አንቀፅ 32 ብናይ ደግሞ ከቦታ ቦታ የመዘዋወር መብት ለኢትዮጵያዊያን እና በሕጋዊ መንገድ ኢትዮጵያ ውስጥ ለገቡ የውጪ ዜጎች ብቻ የተሰጠ ሆኖ ተቀምጧል። ይህም በሕገወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ የገቡ የውጪ አገር ዜጎችን የዚህ መብት ተቋዳሽ እንደማይሆኑ የሚያመላክት ነው። ወደ ተነሳንበት ሀሳብ ስንመለስ የሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 38/1 የመምረጥ እና የመመረጥ መብት ያላቸው የኢትዮጵያ ዜግነት ያላቸው ሰዎች ብቻ መሆናቸውን ይደነግጋል።

ይህም የውጪ አገር ዜጎች የመምረጥ እና የመመረጥ መብት እንደሌላቸው የሚያሳይ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ኹለት ወይም ከዚያ በላይ ዜግነት መያዝ የማይፈቀድ መሆኑን መዘንጋት የለበትም። የሕገ መንግሥቱን አንቀፅ 41/1 ከመንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁ. 1064/2008 እና በተለምዶ የዳያስፖራ አዋጅ ተብሎ ከሚጠራው አዋጅ ቁ. 270/1994 ጋር ስናናብበው ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ ማንኛውም የውጪ አገር ዜግነት ያለው ሰው የፖለቲካ ፀባይ ባላቸው የመንግሥት ኃላፊነቶች ላይ መቀጠር (መሾም) አይችልም። ሆኖም ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከው በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 31 መሠረት የመደራጀት መብት የውጪ አገር ዜጎችን ጨምሮ “ለማንኛውም ሰው” የተሰጠ መብት በመሆኑ የውጪ አገር ዜጎች የፖለቲካ ድርጅቶችን የመመስረትም ሆነ አባል የመሆን መብት እንዳላቸው በመርህ ደረጃ መረዳት ይቻላል።

በተጨማሪም የፖለቲካ ተሳትፎን በተመለከተ ቀጥተኛ ድንጋጌ ሆኖ የሚወሰደው የሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 38 በንዑስ አንቀፅ አንድ የመምረጥና የመመረጥ መብትን ለዜጎች ብቻ የተሰጠ አድርጎ ሲያበቃ በንዑስ አንቀፅ 2 ላይ “ማንኛውም ሰው” የፖለቲካ ድርጅቶች አባል የመሆን መብቱ የተከበረ ነው ሲል ይደነግጋል። ይህም የውጪ አገር ዜጎች የፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆን ይችላሉ የሚል ትርጓሜን ይሰጣል። ነገር ግን የሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 31 ራሱ የመደራጀት መብት አግባብነት ያላቸውን ሕጎች ባልጣሰ መልኩ መተግበር እንደሚኖርበት በመግለፅ መብቱ ላይ ሕጋዊ ክልከላዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ይጠቅሳል።

ይህም ሕገ መንግሥቱን ተከትለው የሚወጡ ሕጎች የውጪ አገር ዜጎችን የፖለቲካ ፓርቲ አባል የመሆን መብት የሚጠብቁ ወይም የሚገድቡ ሆነው ሊወጡ የሚችሉበት እድል እንዳለ ያመላክታል። የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 የመደራጀት እና የፖለቲካ ድርጅቶች አባል የመሆን መብት ላይ ክልከላ ሊደረግበት የሚችል ይህን ጉዳይ በቀጥታ የሚገዛ አዋጅ መሆኑ እሙን ነው።

አዋጁ ለመምረጥ እና ለመመረጥ ኢትዮጵያዊ ዜግነትን እንደ ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጡ የመምረጥ እና የመመረጥ መብት የውጪ አገር ዜጎችን የማያካትት መሆኑን የሚገልፀውን ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ አስጠብቋል። የዚህ አዋጅ አንቀፅ 63 ከሕገ መንግሥቱ ለየት ባለ መልኩ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ፓርቲ የመመስረትም ሆነ አባል የመሆን መብት እንዳለው ይደነግጋል።

ሆኖም የውጪ አገር ዜጎች መሰል ተሳትፎ ማድረግ እንደማይችሉ በግልጽ አይደነግግም። በወርቃማው የሕግ አተረጓጎም መርሕ መሰረት ደግሞ በግልፅ ያልተከለከለ ነገር ሁሉ እንደተፈቀደ ስለሚቆጠር ይህ አንቀፅ የውጪ አገር ዜጎች የፖለቲካ ፓርቲ መመስረት ወይም አባል መሆን አይችሉም የሚል ትርጉምን ሊሰጥ አይችልም። ሕጉ የውጪ አገር ዜጎች የፖለቲካ ፓርቲ መመስረትም ሆነ አባል መሆን አይችሉም ብሎ ግልፅ ክልከላ ማስቀመጥ የነበረበት ሲሆን ከዚህ አለፍ ሲልም የምርጫ ቅስቀሳ እና ዘመቻዎች ላይም የውጪ አገር ዜጎች ተሳትፎ የማድረግ መብት እንደሌላቸው በግልፅ መደንገግ ይችል ነበር። በሌላ በኩል የዚሁ አዋጅ አንቀፅ 69 የውጪ አገር ዜገች አባል የሆኑበት ድርጅት በምርጫ ቦርድ እንደ ፖሊቲካ ፓርቲ መመዝገብ እንደማይችል ይደነግጋል። ሆኖም አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ከተመዘገበ በኋላ የውጪ አገር ዜግነት ያለው ሰውን አባሉ አድርጎ ቢመዘግብ ምን ሊከተል እንደሚችል የሚያስቀምጥ ድንጋጌ የለም።

ይህ ሲሆን በምርጫ ቦርዱ ሊወሰዱ ከሚችሉ እርምጃዎች መካከል አንዱ የፓርቲውን ምዝገባ መሰረዝ ሊሆን እንደሚችል እሙን ነው። ሆኖም የፖለቲካ ፓርቲን በቦርዱ ውሳኔ ስለመሰረዝ የሚያወራው የአዋጁ አንቀፅ 98 የውጪ አገር ዜጋን አባሉ አድርጎ የመዘገበ የፖለቲካ ፓርቲ ከምዝገባ ይሰረዛል የሚል ድንጋጌ አላስቀመጠም። የፖለቲካ ፓርቲዎችን ለመሰረዝ የሚያበቁ ምክንያቶች ሆነው የተቀመጡት ሁኔታዎች 1) በፓርቲ ዋና ዋና ጉዳዮችን የተመለከቱ ለውጦች ሲኖሩ ለቦርዱ አለማሳዋቅ፣ 2) ዓመታዊ የሥራ እና የሂሳብ ሪፖርት አለማቅረብ፣ 3) የፓርቲውን ጠቅላላ ጉባዔ በፓርቲ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት አለማድረግ፣ 4) በሁለት ተከታታይ ምርጫዎች ያለመሳተፍ እና 5) በምዝገባ ወቅት የተደረገ ወይም የሰነድ ማጭበርበር ድርጊቶች ናቸው። የዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ ኹለት ቦርዱ ከላይ ከተዘረዘሩ ምክንያቶች ጋር ተመጣጣኝ የሆኑ የአዋጁ ድንጋጌዎች ተጥሰዋል ብሎ ሲያምን አስፈላጊውን ሂደት ተከትሎ ጥሰት የፈፀመውን ፓርቲ ከምዝገባ ሊሰርዝ እንደሚችል ያስቀምጣል። የውጪ አገር ዜጎች አባል የሆኑበት ድርጅት በምርጫ ቦርድ እንደ ፖሊቲካ ፓርቲ መመዝገብ እንደማይችል የሚያስቀምጠው የአዋጁ ድንጋጌ ከእነዚህ ለስረዛ ያበቃሉ ተብለው ከተዘረዘሩ ምክንያቶች ጋር ተመጣጣኝ መሆኑ ባያጠራጥርም ራሱን የቻለ ለስረዛ የሚያበቃ ምክንያት ሆኖ አለመቀመጡ ግን ብዥታን የሚፈጥር ነው።

ሕገ መንግሥቱ በዚህ ጉዳይ ላይ ግልፅ የሆነ ክልከላ ያስቀመጠ ባይሆንም በሌሎች ሕጎች መሰል ክልከላ ማድረግ እንደሚችል ሕገ መንግሥቱ ራሱ አመላክቷል። ሆኖም አዋጁ ጉዳዩን በረዥም ትርጓሜ የሚደረስበት እና ለትርጉም ክፍት አድርጎ ማለፉ ተገቢነት ያለው አይደለም። በዚህም ከላይ ከተዘረዘሩ ሰፊ የሕግ ክፍተቶች አንፃር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 የውጪ አገር ዜጎችን የፖለቲካ ፓርቲ አባልነት በተመለከተ ጥርት ያለ አቋም ይዟል ለማለት ይከብዳል። መንግሥት ይህን አዋጅ በዚህ መልኩ ማውጣቱ ከአረቃቀቅ እንከን ወይም ሆነ ብሎ ጉዳዩን ለትርጉም ክፍት ከማድረግ (intentional vagueness ለመፍጠር ከማሰብ)

ቅጽ 2 ቁጥር 64 ጥር 16 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here