የትራምፕ የአፍሪካዊያን የጉዞ እገዳ

0
1139

በሕዝበኝነታቸው የሚታወቁት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከመጡ ጀምሮ አገራቸው የፈረመቻቸውን የተለያዩ አካባቢያዊ እና ዓለም አቀፋዊ ስምምነቶች በማጣጣል እና እስከ አካቴውም ጥለው በመውጣት የአሜሪካውያንን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ይጥራሉ፡፡ የአካባቢ ብክለትን ለመቀነስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተካሔደው ስምምነት አገራቸውን ሲያስወጡ የአሜሪካ የኃይል እና ማዕድን ቁፋሮ ድርጅቶች የተሻለ ሥራ ፈጣሪ እና ውጤታማ እንዲሆኑ ነበር፡፡ አሜሪካ ወታደራዊ ጦር ሰፈር ከገነባችባቸው አገሮች ደህንነታችሁን ያረጋገጥኩበት በሚል የምትቀበለው ክፍያ እንኳን እንዲጨምር አድርገዋል፡፡ በመሆኑም ትንሽ የሚባል የአሜሪካ ጥቅም እንደሌለ እንደሚያምኑ በተደጋጋሚ አሳይተዋል፡፡

የዛሬ ሁለት ዓመት በፊት የአሜሪካ መንግሥት በሰባት አገራት ዜጎች ላይ የጉዞ እገዳ ሲጥል ጉዳዩ የዓለም መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። የሊቢያ፣ ኢራን፣ ሱማሊያ፣ ሶሪያ፣ የመን፣ ሰሜን ኮሪያ እና ቬኒዝዌላ ዜጎች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የሚከለክለው የአሜሪካ እርምጃ አገሪቱን ከሽብርተኞች ለመከላከል እና የዜጎችን ደህንነት ለማረጋገጥ እንደተወሰደ ቢገለፅም ተቃውሞ ግን ከአገሪቱ ውስጥም ሆነ ከውጭ የመነጨ ነበር። እንዲያውም የአብዛኞቹን አገራት ሃይማኖት እና የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን ስሜት ግምት ውስጥ በመክተት እርምጃው “የሙስሊም እገዳ” በመባል ይጠራል። በዚህ ሳምንት የአሜሪካ እና ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኋን እየዘገቡ ያሉት ደግሞ ይህ እርምጃ ሰፉ ባለ መንገድ ሌሎች አገራትንም እንዲያካትት ሊደረግ እንደሆነ ነው።

በዚህም መሠረት በአሜሪካ የስደተኞች ፕሮግራም ውስጥ የሚካተቱ አገሮች የአሜሪካንን የደህንነት መስፈርቶች ማሟላት እንደሚገባቸው እየተገለፀ ነው። በአዲሱ ዝርዝር ውስጥ የተካተቱት አገራት ደግሞ ቤላሩስ፣ ማይናማር (በርማ)፣ ኤርትራ፣ ኪርጊዝስታን፣ ናይጄሪያ፣ ሱዳን እና ታንዛኒያ እንደሆኑ እየተዘገበ ነው። ይህ ጉዳይ ሲነሳ ሊረሳ የማይገባው ነገር ከመስመር በወጣ ንግግራቸው የሚታወቁት ትራምፕ የዛሬ ሁለት ዓመት በፊት ወደ አሜሪካ የሚገቡ ስደተኞችን ጉዳይ ከካቢኔ አባላት ጋር በዝግ ሲወያዩ ከቆሻሻ አገሮች የሚመጡ ስደተኞችን ለምን እንቀበላለን ማለታቸውን ነው።

በዚያን ጊዜ ይህንን አገላለፅ የተጠቀሙት ሃይቲ፣ ኤልሳልቫዶር እና የአፍሪካ አገሮችን ለማለት ነበር። ከዚህ ንግግር ለመረዳት እንደሚቻለው የጉዞ እገዳው ሽብርን እና ደህንነትን ብቻ ግምት ውስጥ ያስገባ ሳይሆን የተወሰኑ ቆሻሻ ተብለው ሊፈረጁ የሚችሉ ዜጎች እንዳሉ እና እነዚህ ደግሞ ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ሊታገዱ እንደሚገባ ነው። ይህ ደግሞ ከተለመደው የምዕራባዊያን አመለካከት የተለየ ሳይሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አፍሪካ የቻይና የተፅዕኖ ቀጠና መሆኗን ለመከላከል የጀመሩት ተፍ ተፍ ማለት ከልብ እንዳልሆነ ማሳያ ነው።

የቅኝ ግዛት ጊዜው ካለቀ በኋላ አሜሪካ አፍሪካን “ጭለማዋ አህጉር” በማለት ዞር ብላ ለማየት ተጠይፋት የቆየች ሲሆን በዚህም የተነሳ ከዓለም የተገለለች ሆና ቆይታለች። ይህም ከዓለም የንግድ ልውውጥ አፍሪካ ያላት ድርሻ ግምት ውስጥ መግባት የማይችል በመሆኑ እና ወደ አፍሪካ የሚፈሰው የውጭ ኢንቬስትመንት በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ (ባለፈው ዓመት ከዓለም 1.3 ትሪሊዮን ፍሰት 46 ቢሊዮኑ ብቻ ነበር የአፍሪካ ድርሻ) ይገለፃል።

በአዲሱ የጉዞ እገዳ ከሚካተቱ ሰባት አገሮች ውስጥ አራቱ ከአፍሪካ መሆናቸው እና እንደ ናይጄሪያ ያሉት አገራት ደግሞ በፀረ ሽብርተኝነት እንቅስቃሴዎች ውስጥ የአሜሪካ አጋር መሆናቸው ጉዳዩ የሽብርተኝነት እና ደህንነት ብቻ ያለመሆኑን የሚያሳይ ነው። በዚህ ላይ በሽብርተኝነት አሜሪካንን ሲገዳደሩ የኖሩት እንደ ሳዑዲ አረቢያ ያሉ ኢኮኖሚያቸው ጠንከር ያሉ አገሮች ዜጎች በጉዞ እገዳው ያልተካተቱ መሆናቸው ይህንን ሀሳብ የሚያጠናክር ነው። በመሆኑም የቆሻሻ አገሮች ዜጎች የሚለው የፕሬዝዳንቱ ንግግር ይበልጥ ስሜት ይሰጥ ይሆን ብለን እንድንጠይቅ ያነሳሳናል።

ከዚህ ባለፈ ግን እገዳው በሁለቱ ዙሮች 12 የአፍሪካ እና የእሲያ አገሮችን ያካተተ መሆኑ ግምት ውስጥ ሲገባ ዜጎች ከአሜሪካ ወደ አገራቸው የሚልኩት የውጭ ምንዛሬ አንዱ መስፈርት ነው ወይ የሚያሰኝ ነው። የዓለም ባንክ መረጃ እንደሚያሳየው ወደ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ አገሮች የሚላከው ገንዘብ ቢያንስ ከሦስት ዓመት ወዲህ አዲስ ክብረ ወሰን እየሆነ ነው።

በዚህም መሠረት በ2009 በክብረ ወሰንነት የተመዘገበው 483 ቢሊዮን ዶላር በሚቀጥለው ዓመት በ9.6 በመቶ አድጎ 529 ቢሊዮን ዶላር ገብቶ እንደነበር የዓለም ባንክ መረጃ ያሳያል። ይህ ሒደት ቀጥሎ በ2011 ደግሞ ወደ 550 ቢሊዮን ዶላር የደረሰ ሲሆን በ2013 ደግሞ ወደ 600 ቢሊዮን እንደሚጠጋ ትንበያው ያሳያል። በዚህም መሠረት ስደተኞች ወደ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገሮች የሚልኩት ገንዘብ አገራቱ ትልቁ ከውጭ የሚያገኙት የፋይናንስ ምንጭ እየሆነ ነው። ይህም የምዕራባዊያን ፖለቲካ ማራመጃ የሆነው በእርዳታ ስም የሚሰጠው ብድር እና የፖሊሲ ትዕዛዝን ዝቅ በማድረግ ለአገሮች ሌላ አማራጭ የሰጠ ነው።

ኬኖማድ የተባለው ስደትና ከውጭ ሰዎች ወደ አገራቸው የሚልኩት ገንዘብ ላይ የሚሠራ ድርጅት እንደገለፀው ከ1987 ጀምሮ የሚላከው ገንዘብ ከኦፊሴላዊ እርዳታ ጋር ሲነጻጸር በሦስት እጥፍ ይበልጣል። በ2011/12 ደግሞ ወደ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ አገሮች የተላከው ገንዘብ ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቬስትመንት እንደሚበልጥ እየተጠበቀ ነው። የቀድሞዋ ሶቪየት ሕብረት አካል የነበሩት ኪርጊዝስታን እና ቤላሩስ በጉዞ እገዳው ላይ መካተት በጣም አስገራሚ እና ምክንያቱ በውል ያልታወቀ እንደሆነ መገናኛ ብዙኃን እየዘገቡ ይገኛሉ።

በመካከለኛው እሲያ በጣም ዴሞክራሲያዊ እንደሆነች የሚነገርላት ቤላሩስንም ሆነ ከፍተኛ የሙስሊም ቁጥር ያለባት ኪርጊዝታንን አሜሪካ ከራሽያ ለማራቅ እና ከጎኗ ለማሰለፍ እየሠራች እንደሆነ ይታወቃል። ትራምፕ እንዳይደርሱባቸው የሚፈልጓቸው ሙስሊሞች ቁጥር በቤላሩስ ከአንድ በመቶ በታች መሆኑ ደግሞ የቤላሩስን መካተት ይባስ ያልተገመተ ያደርገዋል። አብዛኛው የቤላሩስ እና የኪርጊዝስታን ከውጭ የሚላክ ገንዘብ ምንጭ ራሺያ መሆኗ ደግሞ አሜሪካ ልታወጣው ነው የተባለው እገዳ የሚላክ ገንዘብን ተመርኩዞ እንዳልሆነ የሚጠቁም ነው። በመሆኑም በዚህም መስፈርት የሁለቱ አገሮች መካተት አሻሚነቱ እንደተጠበቀ ነው።

በአፍሪካ ከፍተኛ ገንዘብ በውጭ ያሉ ዜጎች ከሚልኩባቸው አገሮች መካከል ናይጄሪያ ግንባር ቀደሟ ነች። በ2011/12 ከ25 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወደ ናይጄሪያ ተልኳል። የናይጄሪያ መንግሥት የአሜሪካ የፀረ-ሽብር ዘመቻ አጋር መሆኑ እና በ2010 አሜሪካ ለናይጄሪያዊያን ከፍተኛ ቁጥር ያለው የመኖሪያ ፍቃድ እና ጊዜያዊ ቪዛ የሰጠች መሆኑ አሜሪካ ናይጄሪያውያንን በደህንነት ስጋት ትወስዳቸዋለች ብሎ ለመገመት አዳጋች ያደርገዋል። ሱዳን ሌላዋ በአፍሪካ ከፍተኛ ገንዘብ ከውጭ የምትቀበል ከአሜሪካ ጋር ጥሩ ግንኙነት የሌላት አገር እንደሆነች መረጃዎች ያሳያሉ። ኤርትራም በከፍተኛ ደረጃ ከውጭ በሚላክ ገንዘብ ላይ ከሚመረኮዙ አገሮች አንዷ ስትሆን በአሜሪካ ነጻነትን ከሚገፉ አገራት ተርታ ትፈረጃለች።

የዓለም ባንክ ከወራት በፊት ባወጣው መረጃ ላይ እንደተጠቀሰው ይህ እንደ አሜሪካ ባሉ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ስደተኞች ወይም የሌላ አገር ተወላጆች ከኢኮኖሚው የሚያወጡት ገንዘብ ስድተኞችን መቀበል ያለውን ጠቀሜታ በእጅጉ የሚገዳደር ነው። በአገር ውስጥ ሠርተው ያገኙትን ገንዘብ ወደ ውጭ የሚያስወጡ ከሆነ ለኢኮኖሚው የሚኖራቸው ጠቀሜታ የሚጠበቀውን ያህል እንዳልሆነ ሲጠቅስ ነው የዓለም ባንክ። ከ1975 ጀምሮ በዓለም ቀዳሚ ከውጭ የሚላክ ገንዘብ ምንጭ ሆና ለቆየችው አሜሪካ ደግሞ የእድገቱ ከፍተኛነት በተለይ የወደፊቱን በማሰብ ከአሁኑ ሊታሰብበት የሚገባ ነው። መረጃዎች እንደሚያሳዩት በ1975 5 ቢሊዮን ዶላር የነበረው ከአሜሪካ ወደ ውጪ የሚላክ ገንዘብ በ2011 68 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል።

የቪዛ ሎተሪ ፕሮግራም ዘርግታ የሌሎች አገሮችን ዜጎች እንደራሷ እያደረገች ያለች አገር ወደ ትውልድ አገራቸው ገንዘብ በከፍተኛ መጠን ፈሰስ የሚያደርጉ ሰዎች ስጋት ሊሆኗት ይችላሉ። የዚህ የጉዞ እገዳ የሰባቱም አገራት ዜጎች የመኖሪያ ፍቃድ እንዳያገኙ እና የቪዛ ሎተሪ ተሳታፊ እንዳይሆኑ ያገደችበትም አንድ ምክንያት ይኄ ሊሆን ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ እንደ እርዳታ እና የውጭ ቀጥታ ኢንቬስትመንት ያሉ ምዕራባዊያን አነስተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸውን አገሮች በፈለጉት መንገድ የሚመሩባቸው መሣሪያዎች አቅም የሚገዳደር አካሔድ መሆኑ ለወደፊቱ አሳሳቢ ሊያደርገው ይችላል።

በአሜሪካ ተቀባይነት የሌለው ፖሊሲ መከተል የሚያጋጭ ምክንያት መሆኑ ግልጽ ሲሆን እርዳታን ወይም የውጭ ቀጥታ ኢንቬስትመንትን መቀነስ ኃያሏ አገር ከምትወስዳቸው እርምጃዎች ውስጥ የሚካተቱ ናቸው። በጉዞ ገደቡ ላይ መረጃዎችን ለአሜሪካ መንግሥት ለማጋራት አገሮች ያላቸው የፍቃደኝነት ማነስ እንደ መስፈርት መወሰዱ ደግሞ በተዘዋዋሪ ከዚህ ጋር የሚገናኝ ነው። በሕዝበኝነት ከሚጠቀሱት የዓለም መሪዎች በግንባር ቀደምትነት የሚቆሙት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ትራምፕ ደግሞ ይህንን አካሔድ ለመግታት ከውጭ በሚላክ ገንዘብ ላይ ጥገኛ የሆኑ አገሮች ዜጎችን ኢላማ ሊያደርጉ ይችላሉ።

በዋነኛነት ከአሜሪካ ገንዘብ የሚላክላቸው አገሮች የደቡብ አሜሪካ እና ካሪቢያን አገሮች ቢሆኑም በተለምዶው “የአሜሪካ ጓሮ” እየተባሉ የሚጠሩ እና የዓለም ብቸኛዋ ኃያል አገር ጫና በከባዱ የሚታይበት ቦታ በመሆኑ የጉዞ እገዳ ውስጥ መካተቱ የማይጠበቅ ነው። ቬኒዝዌላ በመጀመሪያው እገዳ ውስጥ ተካታ የነበረች መሆኑ ደግሞ የፖለቲካ ቅራኔያቸው ጠንከር ያሉ ሶሻሊስት አስተሳሰብን ለሚመርጡ የደቡብ አሜሪካ አገሮች ማስጠንቀቂያ ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 64 ጥር 16 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here