ዳሰሳ ዘ ማለዳ (ጥር 21/2012)

0
622

በኢትዮጵያ 60 በመቶ ህጻናት የልደት ማረጋገጫ የላቸውም

 

የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ 60 በመቶ የሚሆኑ ህጻናት ስለማንነታቸው የሚገልጽ የልደት የምስክር ወረቀት እንደሌላቸው ገለጸ።ምንም እንኳን ሕገ መንግስቱ አንድ ህጻን ከተወለደ በኋላ ስም የማግኘት፣ ወላጆቹን የማወቅ፣ ዜግነት የማግኘት እንዲሁም የተወለደበት ቦታና ቀን መታወቅ እንዳለበት የሚደነግግ ቢሆንም ህጻናቱ በህግ ከተቋቋመ ተቋም ስለማንነታቸው የሚገልጽ የልደት መረጋገጫ የላቸውም ተብሏል።የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ሙጅብ ጀማል  ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት  የመጀመሪያውን መንፈቅ አመት ያከናወናቸውን ተግባራት ባብራሩበት ወቅት ባለፉት አምስት አመታት ኤጀንሲው በኢትዮጵያ  ይህን ዓለም ለሚቀላቀሉ ለ12 ሚሊዮን ህጻናት የልደት የምስክር ወረቀት ለመስጠት አቅዶ ለሁለት ሚሊዮን ህጻናት ብቻ የልደት የምስክር ወረቀት ማግኘታቸውን ገልጻዋል።በመሆኑም  ከእቅዱ አንጻር 10 ሚሊዮን የሚሆኑ ህጻናት በወሳኝ ኩነት መረጃቸው አልተመዘገበም ይህ ማለት  በአገሪቱ 60 በመቶ የሚሆኑት ልጆች ህጋዊ መታወቂያ እንደሌላቸው የሚያሳይ ነው ብለዋል። (ኢ.ፕ.ድ)

…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………..

በስድስት ወር ውስጥ በከፍተኛ ትምህር ተቋማት ላይ ሁከት እና ብጥብጥ የፈጠሩ አንድ ሺህ 207 ግለሰቦች ላይ እርምጃ ተወሰደ። የሳይንስእና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ሒሩት ወልማርያም (ረዳት ፕሮፌሰር ) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ጥር 21/2012 ባቀረቡት የስድስት ወራት ሪፖርት ላይ እንደተናገሩት  421 ተማሪዎች ለአንድ ዓመት ከማገድ ጀምሮ እስከ ማባረር እርምጃ እንደተወሰደባቸው ገልጸዋል። እርምጃ ከተወሰደባቸው መካከል 140 ተማሪዎችና መምህራን ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ መሆኑንም ተናግረዋል። ከሕዳር 30 ጀምሮ በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ላይ የብሔር እና የሐይማኖት መልክ ያላቸው ግጭቶች የተስተዋለ ሲሆን ለዚህም ማህበራዊ ሚዲያዎች ግጭቶቹ እንዲስፋፉ ማድረጋቸውን በሪፖርታቸው ላይ አመላተዋል።

…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………..

የሦስቱ ሚኒስትሮች  ሹመት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ሳይፀድቅ በፊት በመገናኛ ብዙሃን ይፋ መደረጉ ቅሬታ አስነሳ። ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 5ኛ ዓመት 11ኛ መደበኛ ጉባኤ  የሦስት ሚኒስትሮችን ሹመት መርምሮ ያጸደቀ ሲሆን ኢንጅነር ጌታሁን መኩሪያ(ዶ/ር) የትምህርት ሚኒስትር፣  አብርሃ በላይ(ዶ/ር ) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር እንዲሁም  መላኩ አለበል የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል። የምክር ቤቱ አባላት  እንደተናገሩት ሹመቱን በማፅደቁ ሂደት ጥር 6/2012  በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተመረጡት  የእነዚህ ተሿሚዎች ሹመት ቀድሞ ይፋ መደረጉ የአካሄድ ችግር ያለበት ነው  ብለዋል። የተፈጠረው የአካሄድ ወይም የቅደም ተከተል መዛነፍ ለቀጣይ እርምት የሚወሰድበት ነው ተብሏል።(የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት)

…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………..

ዛሬ ንጋት ላይ የኤሌክትሪክ ገመድ ተቃጥሎ በኡራኤል ቤተክርስትያን አቅራቢያ የሚገኙ የባኞ ቤት፣ የሤራሚክ፣ የመስታወት እና የፍሬም ሥራዎችን የሚሠሩ ሦስት ሱቆች ላይ የእሳት አደጋ ደረሰ።‹‹የእሳት አደጋው የተነሳው ለዛሬ ጥር 21/2012 ንጋት ከሌሊቱ 10 ሰዓት አካባቢ ሲሆን፣ መንስኤውም በሱቆቹ አካባቢው ያለው የኤሌክትሪክ ገመድ በእሳት በመያያዙ ነው።›› ሲሉ የአካባቢው የዐይን እማኖች ለአዲሰ ማለዳ ተናግረዋል። በእሳት አደጋው ኹለቱ ሱቆች ላይ ጉዳት ሲያደርስ፣ በአንደኛው ሱቅ ላይ ግን ጉዳቱ የከፋ አለመሆኑን ለማወቅ ተችሏል።የእሳት አደጋው ከደረሰ በኋላም የአዲሰ አበባ እሳት እና ድንገተኛ አደጋ መከላከልና መቆጣጠር ባለሥልጣን በቦታው ተጨማሪ ጉዳት ሳይደርስ እሳቱን መቆጣጠር መቻሉንም የዐይን እማኖቹ ገልጸዋል። በንብረቶቹ ላይ ስለደረሰው አደጋ የባለሥልጣኑን የሕዝብ ግንኙነት ለማነጋገር ብንሞክርም ስልካቸው ባለመሥራቱ ምላሽ ማግኘት አልተቻለም።(አዲሰ ማለዳ)

…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………..

በአርባ ምንጭ ከተማ ከ35 ኩንታል በላይ አደንዛዥ ዕፅ ተያዘ። ዕፁ በተለምዶ ኤፍ ኤስ አር ተብሎ በሚታወቀው የጭነት መኪና ሲዘዋወር መያዙን የአርባ ምንጭ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ዳንኤል አረጋ ተናገሩ። በዛሬው እለት ጥር 21/2012 የተያዘው አደንዛዥ ዕፅ  በሚመለከተው አካል በተገቢው መንገድ ከከተማ ውጭ የሚወገድ መሆኑም ተነግሯል። አደንዛዥ እጾች በህብረተሰብ ጤና እና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ላይ እንዲሁም በወጣቱ ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ ከፍተኛ በመሆኑ ሁሉም ዜጋ መሰል ድርጊቶችን በመጠቆም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ ከከተማው ፖሊስ ጥቀርቧል።(ፋና)

…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………..

 

 

የግብጽ ኮፕቲክ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ልዑካን ገር ተነጋገሩ። ታውድሮስ ሁለተኛ የቤተ ክርስቲያኑ ዋና መቀመጫ በሆነችው የካይሮ አባሲያ በሚገኘው የቅዱስ ማርቆስ የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ካቴድራል ልዑካን ቡድኑን ተቀብለው የተነጋገሩ ሲሆን የሁለቱ ቤተክርስቲያናት ሃላፊዎች ቤተክርስቲያናቱ ለረጅም ዘመናት ባላቸው ግንኙነት ዙሪያ ምክክር አደርገዋል።እንዲሁም የአስተሳሰብ ልዩነቶቻችን ወደ ጎን በመተው የኮፕቲክ ቤተክርስቲያናት ለክርስትና እምነት ተከታዮች አንድነት በጋራ መስራት እንደሚገባቸው በውይታቸው ላይ አንስታዋል።የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንና የግብጽ ኮፕቲክ ቤተክርስቲያን ከ4ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያ አጋማሽ ጀምሮ ለረጅም ክፍለ ዘመናት የቆየ ግንኙነት አላቸው።(ኢዜአ)

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here