ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ውጪ ይሰማራሉ ያሏቸው 50 ሺሕ ሰዎች እስከ አሁን አልተላኩም

0
306

ሰኔ 24/2011 ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሦስት ዓመታት ውስጥ 200 ሺሕ የሠለጠኑ ሠራተኞች ወደ ሩቅ ምሥራቅ ለመላክ እና በ2012ም 50 ሺሕ የሚሆኑትን ለመላክ ቅድመ ዝግጅት መደረጉ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢገለጽም፣ እስከ አሁን ግን አንድም ሠራተኛ በዚህ መሰረት ለሥራ አልተሰማራም።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ውስጥ ፈተና የሆነውን የሥራ አጥነት ችግር ለመፍታት ከተለያዩ አገራት ጋር በመሆን የሥራ እድሉ መመቻቸቱን ገልፀው ነበር።

ይህንን ለማድረግም የሠራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የውጪ አገር ስምሪት አዋጅ መሻሻል ቢኖርበትም፣ እስከ አሁን ድረስ ይህ ባለመጠናቀቁ መላክ እንዳልቻለ ሚኒስቴሩ ለአዲስ ማለዳ አስተውቋል። በሥራ ላይ ያለው አዋጅ ዕድል የሚሰጠው ለቤት ሠራተኞች እና በእንክብካቤ ሥራዎች ወደ ውጭ አገር ለሚሰማሩ ዜጎች ብቻ በመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ለገለፁት ሙያን መሰረት ያደረጉ የሥራ ስምሪቶች ዜጎችን ለመላክ እንደማይሆን የሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ደረጄ ታዬ ተናግረዋል። በዚህም መሰረት አዋጁ ላይ ማሻሻያዎች እየተደረጉ መሆኑንም ጨምረው ገልፀዋል።

‹‹ዜጎች በአገራቸው ቢሠሩ ይመረጣል፤ ካልሆነ ግን ወደ ውጭ አገር ሄደው ለመሥራት ፍላጎት ያላቸው የተማሩ ባለሙያዎችን ለመላክ ከአዋጁ ባሻገር ከሚቀበሉ አገራት ጋር ስምምነት ማድረግ ይገባል›› ሲሉ ደረጄ ይናገራሉ።

አዋጁ በቤት ውስጥ ሥራ እና በሞግዚትነት አረጋውያን እና ሕጻናትን ለመንከባከብ ለሚያቀኑ አዋጁ አስፈላጊ የጥበቃ አንቀፆችን ያሟላ መሆኑን ባለሞያው ይገልፃሉ። እስከ አሁን የቤት ሠራተኞችን የሚቀበሉት የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች፣ ዱባይ፤ ኳታር እና ጆርዳን የሠለጠኑ ባለሞያዎችንም ለመቀበል ፍላጎት ማሳየት መጀመራቸውንም ጨምረው ተናግረዋል።

ከአረብ አገራት ባሻገርም ወደ አውሮፓ አገራት ሥራ ፈላጊ ዜጎች በሕጋዊ መልኩ ለሥራ እንዲሰማሩ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች መኖራቸውን ኃላፊው ቢገልጹም፣ ይህ አዋጅ መጠናቀቁ ግን አስፈላጊ መሆኑን ጨምረው ተናግረዋል። አዋጁን የማርቀቅ ሥራው ተገባዶ ለአስተያየት ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መላኩንም ደረጄ ተናግረዋል።

ሳውዲ አረቢያ የቤት በተለይም ኢትዮጵያውያን መምህራኖችን ለመውሰድ ፍላጎት ያሰየች ሲሆን፣ በተጨማሪም ሆላንድ፣ ጃፓን እና ሲውዘርላንድም የሠለጠኑ ኢትዮጵያውያን ሠራተኞችን የሥራ ፈቃድ ለመስጠት ፍላጎት ካሳዩ አገራት መካከል መሆናቸውን ይናገራሉ። የአገራቱ የሥራ ልምድ እና ሥልጠና ፍላጎት የሚለያይ ሲሆን፣ ከየአገሩ ጋር በሚደረጉ ስምምነቶች የሚቀጠሩበት መስፈርቶች እንደሚሰናዱም ደረጄ ተናግረዋል።

የሚሻሻለው አዋጅ ሲፀድቅ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚመረቁ ተማሪዎች የዚህ እድል ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ እና ከስምሪቱ በፊት የሚሰጡ ሥልጠናዎች እና የብቃት ማረጋገጫ እንደሚወስዱም ተናግረዋል። የደመወዝ ክፍያ ጉዳይ በሚመለከትም ዜጎዎች እንደሚያቀኑባቸው አገራት ዝቅተኛ የደሞዝ ወለል ይወሰናል ተብሏል።

በኢትዮጵያ የሥራ አጥነት ችግር እየተባባሰ የመጣ ጉዳይ መሆኑ በተደጋጋሚ ይነገራል። ይህ ችግር ደግሞ በስፋት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመርቀው የሚወጡ ተማሪዎች ላይ ይስተዋላል። ይህም ችግር ዜጎች በሕገወጥ መንገድ ከአገር እንዲወጡ ከሚያስገድዳቸው ጉዳዮች አንደኛው እንደሆነ ይገለጻል።

በኢትዮጵያ ላለው የሥራ አጥነት ችግር በርካታ ምክንያቶችን መጥቀስ የሚቻል ሲሆን፣ ከምክንያቶቹ መካከልም የወጣቶች የሥራ ፈጠራ ስኬታማ አለመሆን፣ የትምህርት ፖሊሲው እና የኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ናቸው።

ኢትዮጵያ ፈጣን እድገት እያስመዘገቡ ካሉ አገራት መመደቧ ቢነገርና የአምራች ኃይሉ ቁጥሩ እያሻቀበ ቢመጣም፣ ለአምራቹ ኃይል አቻ የሚሆን በቂ ሥራ እድል አለመፈጠሩንም አዲሰ ማለዳ በቅፅ 1 ቁጥር 23 ሚያዚያ 5/2011 ላይ ባወጣቸው ዕትም ላይ ስለ ሥራ አጥነት በሰፊው መተንተኗ ይታወሳል።

ቅጽ 2 ቁጥር 65 ጥር 23 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here