የይዞታ ማረጋገጫ የሌላቸው ባለንብረቶችን መብት የሚገድብ ሕግ ተረቀቀ

0
1787

አዋጁ ክልሎች የራሳቸውን ቁራሽ የከተማ መሬት የሚያስተዳድሩበት መመሪያ ማዘጋጀት እንዲችሉ ዕድል ይሰጣል

የመሬት ባለይዞታዎች የባለቤትነት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት እንዲይዙ የሚያስገድድ እና ይህንን በማያደርጉ ባለይዞታዎች ላይም መብቶቻቸውን የሚገድብ የአዋጅ ማሻሻያ ሊደረግ መሆኑ ተገለፀ።

የፌዴራል የመሬት እና መሬት ነክ ይዞታ ምዝገባ መረጃ እና ማረጋገጫ ኤጀንሲ አዋጅ 818/2006 ላይ አዳዲስ መብት እና ግዴታዎችን የሚፈጥሩ ለውጦችን በተለይም የአሰራር ክፈተትን የሚሞላ ማሻሻያ በማድረግ ላይ ነው።

ከዚህ ቀደም የመሬት ባለይዞታዎች የባለቤትነት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት እንዲይዙ በአዋጅ ተቀምጧል የተባለ ሲሆን፣ አሁን በሚደረገው የአዋጅ ማሻሻያ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ የሌላቸው ባለንብረቶች ላይ ቅጣት የሚጥል እንደሆነ ተገልጿል።

የአዋጅ ማሻሻያው በመሬት አለካክ እና የይዞታ ማረጋገጫ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ላይ ሲስተዋሉ የነበሩ ብዙ የአሰራር ክፍተቶችን ለማስቀረት ያግዛል የተባለ ሲሆን፣ ክልሎች የራሳቸውን ቁራሽ መሬት የሚያስተዳድሩበትን የከተማ መሬት ይዞታ ማረጋገጫ መመሪያ ማዘጋጀት እንዲችሉ ዕድል የሚሰጥ መሆኑ ተገልጿል።

የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት መያዝ በአዲሱ አዋጅ መሰረት ግዴታ እንደሚሆን እና የይዞታ ማረጋገጫ በሌላቸው ባለንብረቶች ላይ ቅጣትንም የሚያስከትል እንደሚሆን የኤጀንሲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አራጌ ክብረት ተናግረዋል። በማያስመዘግቡ ባለይዞታዎች ላይ ስለሚጣለው ቅጣት አሁን መግለፅ አይቻልም ያሉ ሲሆን፣ የማያስመዘግቡ ባለንብረቶች ግን በንብረቱ ላይ ኃላፊነት፣ ክልከላ እና መብት እንደማይኖራቸው ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም ቁራሽ መሬቶች ሲለኩ፣ በሰነዶች ተመዝግቦ ከሚገኘው መረጃ ውጪ በመሬት የይዞታው ላይ የልኬት ለውጥ በሚከሰትበት ወቅት፣ ክልሎች የሚፈቱበት መንገድ አልነበረም የተባለ ሲሆን፣ ባለይዞታዎች ጉዳይ ለማስፈፀም ከክልል ከተሞች ወደ አዲስ አበባ እንደሚመጡ ተገልጿል።

በምዝገባ ሂደት ላይ መሰል ችግሮች ሲከሰቱ ክልሎች ጉዳዩን ለፌዴራል የመሬት ይዞታ ምዝገባ እና ማረጋገጫ ኤጀንሲ ሲመሩት ቆይተዋል። የክልል ኤጀንሲዎች መሬትን ለመመዝገብ የሚያስችል ሥልጣን ኖሯቸው እንደዚህ አይነት ጉዳዮችን ለማየት የሚያስችል መመሪያ አልነበራቸውም ብለዋል።

ክልሎች እንደዚህ ዓይነት ጉዳዮችን ለመፍታት የሚያስችል መመሪያ እንዲያዘጋጁ የሚያስችል መብት በአዋጅ ማሻሻያው እንደሚሰጣቸውም ገልጸዋል።
በአዋጅ ማሻሻያው ላይ ክልሎችን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላት ውይይት እንዲያደርጉ እና ሐሳባቸውን እንዲያካትቱ ተደርጓል ያሉት ኃላፊው፣ አዋጁ እስከ ቀጣይ ዓመት መጀመሪያ ይፀድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል።

የመሬት ወረራን ለመከላከል የሚያስችሉ ጥብቅ ሕጎች በአወጅ ማሻሻያው ተካተውበታል ያሉ ሲሆን፣ ሁሉም የመሬት ባለይዞታዎች የይዞታ ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት መያዝ እንዲኖርባቸው አዲሱ አዋጅ እንደሚያስገድድም ጠቅሰዋል።

በቀድሞው አዋጅ ላይ ይህ ጉዳይ ተካትቶ ነበር። ሆኖም ቅጣቶች አልነበሩትም። አሁን መንግሥት እያንዳንዱን ቁራሽ መሬት መዝግቦ ለመያዝ በትኩረት እየሠራ በመሆኑ፣ ሁሉም ባለይዞታ መሬቱን እንዲያስመዘግብ ለማድረግ በትኩረት ይሠራል ሲሉ ክብረት ገልጸዋል።

የኤጀንሲው የማቋቋሚያ አዋጅ 818/2006 እና የአዋጁ ማስፈፀሚያ ደንብ ቁጥር 324/2006 ሲሆኑ የአዋጁ አንቀፅ 13 ንዑስ ቁጥር 1፣3፣4፣5 እንዲሁም አንቀፅ 27፣28፣29 ማሻሻያ እንደሚደረግባቸው ተገልጿል።

የከተማ መሬት ይዞታ ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 818/2006 በዋናነት ስለሚመዘገበው መብት፣ በተለይም የመሸጥ፣ የመለወጥ፣ የማውረስ፣ ባለቤትነቱን የማዛወር ወይም የካሳ ክፍያ ከመጠየቅ ጋር ስለተያያዙ መብቶች በዝርዝር ያትታል።

ኤጀንሲው በከተሞች የይዞታ ንብረት ምዝገባ እና ማስተላለፍን ጨምሮ በመመዝገብ ከመሬት ይዞታ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን መብቶች፣ ክልከላዎች እና ግዴታዎች ሕጋዊነት የማረጋገጥ ሥራ ያከናውናል። እንዲሁም ዜጎች በይዞታ ላይ ላፈሩት ቋሚ ንብረት ሕጋዊ ዋስትና በመስጠት ላይ እንደሚገኝም ተጠቁሟል።

እንዲሁም በከተሞች የኢኮኖሚ እድገት ውስጥ ቋሚ ንብረት የሕግ ዋስትና በመስጠት፣ በከተሞች የኢኮኖሚ እድገት ውስጥ ቋሚ ንብረት ወደ ገበያ እንዲገባ ማመቻቸት እና ዜጎች ተጠቃሚ መሆናቸው ማረጋገጥ በሚሉ ጉዳዮች ላይ በስፋት በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።

በኢትዮጵያ 18 ከተሞች ዘመናዊ የመሬት አስተዳደር የይዞታ ምዝገባ ስርአትን እየተገበሩ ይገኛሉ። የመሬት ምዝገባ ስርአቱን በዘመናዊ የመሬት ይዞታ መመዝገቢያ ቋት ለማድረግ እየተሠራ እንደሚገኝም ኤጀንሲው አስታውቋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 65 ጥር 23 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here