የደኅንነት ቀበቶ ዋጋ በአራት እጥፍ ጨመረ

0
846

የትራንስፖርት ባለሥልጣን በታኅሳስ ወር ከፊት ወንበር የሚቀመጡ ተሳፋሪዎች የደኅንነት ቀበቶ እንዲያደርጉ ያወጣውን መመሪያ ተከትሎ በገበያ ላይ የደኅንነት ቀበቶ ዋጋ ከ250 ወደ 1200 ከፍ አለ።

ከዋጋ ጭማሪው ባሻገርም የደኅንነት ቀበቶው ከገበያ ላይ የጠፋ ሲሆን፣ የቀበቶው መለዋወጫዎችም ከገበያ ላይ መጥፋታቸውን አሽከርካሪዎች እና ነጋዴዎች ተናግረዋል። ነጋዴዎቹ በውጪ ምንዛሬ ችግር ምክንያት የደኅንነት ቀበቶ ከውጪ አገር ታዝዞ እስኪመጣ መዘግየቱ እንደማይቀር እና በድንገት የተፈጠረው ከፍተኛ ፍላጎት በፈጠረው እጥረት የቀበቶ ዋጋው እንዲጨምር ማድረጉን ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።

በአሽከርካሪዎችና በተሳፋሪዎች ላይ የሚደርሰውን የመንገድ ትራፊክ አደጋ ለመቀነስ ሲባል የተተገበረው ይህ መመሪያ፣ ታኅሳስ አንድ ከመተግበሩ በፊት ቀበቶው እስከ 250 ብር ድረስ ይሸጥ ነበር። አዲስ ማለዳም በቄራ፣ ሰባራ ባቡር፣ ተክለ ሃይማኖት እና በሱማሌ ተራ በሚገኙ የመኪና ጌጣጌጥ እና መለዋጫ መሸጫ መደብሮች ባደረገችው ቅኝት የቀበቶ እጥረት እና የዋጋ ጭማሪውን አረጋግጣለች።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የታክሲ ሹፌሮች እንደሚሉትም፣ የደኅንነት ቀበቶውን አስገዳጅ ማድረጉ ይሁን የሚያስብል ቢሆንም የገበያውን ሁኔታ ያላገናዘበ በሕጉ እና በገበያው መካከል አጣብቂኝ ውስጥ የከተተ እንደሆነ ይናገራሉ።

‹‹አብዛኛው በከተማዋ የሚገኙ ታክሲዎች ከተመረቱ 30 ዓመት የሞላቸው ስለሆኑ አብዛኞቹ የደኅንነት ቀበቶ የላቸውም። ስለዚህም ቢያንስ መንግሥት ቀበቶውን ማድረግ አስገዳጅ የሚያደርግብን ከሆነ የምናገኝበትን መንገድ ማመቻቸት ወይም ጊዜ መስጠት ያስፈልጋል›› ሲሉ ታምሩ ንጉሡ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ሥሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገውና የኹለት ልጆች አባት የሆነው የታክሲ አሽከርካሪ ‹‹የደኅንነት ቀበቶው አሁን ላይ እንዳንገዛ ገበያ ላይ የለም። አሮጌውም እስከ 600 ብር እየተባለ ነው። ይህን ለማድረግ አቅሜ አይፈቅድም›› ሲል ያስረዳል። ‹‹መንግሥት እያደረገ ያለው ዝም ብሎ ገንዘብ መሰብሰበ ነው፤ ለምሳሌ በቅርቡ መንጃ ፍቃድ ለማሳደስ ወደ አራት መቶ ብር ጭማሪ ያለማስጠንቀቂያ አድርጓል። ኑሮአችንን የሚፈትነው የኑሮ ውድነቱ ሳያንስ አሁን ደግሞ መንግሥትም እየፈተነን ነው›› ሲል በምሬት ይናገራል።

በተሳፋሪዎች ፍቃደኛ አለመሆን ምክንያትም እየተቀጣን ነው የሚሉት አሽከርካሪዎቹ፣ የትራፊክ ፖሊሶችም በተሳፈሪ ጥፋት እንደሚቀጧቸው ይናገራሉ። መመሪያው አደጋ በሚበዛባቸው የአገሪቱ ክፍሎች በአግባቡ ሳይተገበር ፍጥነት በማይኖርበት በከተማ ውስጥ መተግበሩ ዓላማውን የሳተ ነው ሲሉም አሽከርካሪዎች ተናግረዋል።
የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ይግዛው ዳኜ፣ መመሪያው ከወጣ በኋላ አተገባበሩ ላይ በመላው አገሪቱ ዳሰሳ እየተሠራ እንደሆነ ተናግረዋል።

ተሻሽሎ በወጣው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ አንቀፅ አምስት ላይ ማንኛውም አሽከርካሪ በሚያሽከረክርበት ወቅት በተሽከርካሪው ውስጥ የተሳፋሪ የደኅንነት ቀበቶ ማሰሩን ማረጋገጥ እንዳለበት ያስቀመጠ ሲሆን፣ በተሻሻለው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 395/2009 መሠረት ለጥፋቱ 250 ብር እንደሚቀጣ ደንግጓል።
ከሰኔ እስከ ታኅሳስ 30/2012 ድረስ ያለው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በኢትዮጵያ ያለው የመኪና ቁጥር አንድ ሚሊዮን 148 ሺሕ 366 ደርሷል።

ቅጽ 2 ቁጥር 65 ጥር 23 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here