የወሃ ናሙናን ወደ ውጪ መላክ የሚያስቀር የምርምር ማእከል ተገነባ

0
618

የውሃን ኬሚካላዊ ይዘት ለማረጋገጥ ወደ ውጪ አገር መላክን የሚያስቀር የመስኖ እና ውሃ አስተዳደር ምርምር ማእከል ተገነባ። ማእከሉ የተገነባው ከሞሮኮ ንጉሥ መሐመድ 6ኛ የዘላቂ ልማት ፋውንዴሽን በተገኘ 140 ሚሊዮን ብር ድጋፍ እና በመንግሥት 150 ሚሊዮን ብር በጀት ነው።

ከከርሰ ምድር ተቆፍሮ የሚገኝን የውሀ ሀብት ለጤና ተስማሚነት ለማረጋገጥ ወደ ውጪ አገራት በመላክ ኢትዮጵያ በዓመት በርካታ ሚሊዮን ዶላሮችን እንደምታወጣ የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዋሲሁን ዓለማየሁ ተናግረዋል። የማእከሉ መገንባት ይህንን ከፍተኛ ወጪ በአገር ውስጥ ለማስቀረት እንደሚረዳና ከውሃ እና መስኖ ቴክኖሎጂ ጋር የተያያዙ ሙያዊ ሥልጠናዎችን ለመስጠት እንደሚያግዝም ተናግረዋል።

የውሃ ብክነትን ለመቀነስ እና የተበከለ ውሃን መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል የሚያስችሉ ጥናት እና ምርምሮችን ማእከሉ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።
ማእከሉ ውሃን በማከም፣ በመስኖ ልማት እና ውሃን መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል ምርምር የሚደርግባቸው ቤተ ሙከራዎችን የያዘ መሆኑ ተገልጿል። የውሃ ኬሚካላዊ ይዘት እና ሥነ ሕይወት ላይ ምርምር ለማድረግ የሚረዱ ኹለት ቤተ ሙከራዎችን እና ማስተማሪያ ማእከላትም አጠቃሎ በኢትዮጵያ የውሀ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ግቢ ውስጥ የተገነባው ይህ ማእከል፣ 2 ሺሕ 600 ሜትር ስኩየር ላይ አርፏል።

ለቢሮ አገልግሎት፣ ለመማሪያ ክፍሎች፣ ለስብሰባ አደራሽ እና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አገልግሎት የሚሆኑ ክፍሎችም እንደሚኖሩት ታውቋል።
ለሥልጠና ማእከሉ የሚያስፈልጉ መሣሪያዎች ከውጪ አገር በመግባት ላይ ሲሆኑ፣ እስከ አሁን ሦስት ኮንቴነር እቃ ገብቶ መጠናቀቁን እና ሌሎች ዕቃዎችን የማስገባቱ ሥራ በሂደት ላይ መሆኑን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ዋሲሁን ተናግረዋል። ማእከሉ በቀጣይ ሦስት ወራት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ወደ ሥራ እንደሚገባም ጨምረው ገልፀዋል።

አክለውም ማእከሉ የውሃ ብክነትን ለመከላከል የሚያስችሉ ሥራዎችን ለመሥራት ያግዛል ያሉ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ በርካታ ገንዘብ ወጥቶበት ከሚታከመው እና ለአገልግሎት ከሚውለው ውሃ ውስጥ 35 በመቶ የሚሆነው በተለያዩ ምክንያቶች ይባክናል ብለዋል።

ለዚህም የውሃ ማስተላለፊያ መስመሮች ማርጀትና በጊዜው አለመቀየር፣ ሲሰበሩ አፋጣኝ ጥገና አለመደረጉ በምክንያት የተጠቀሰ ሲሆን፣ ተጠቃሚው ኅብረተሰቡ ብዙ ወጪ ወጥቶበት የታከመውን ውሃ መኪና ለማጠብ እና መሰል ሥራዎች መዋሉ በምክንያት ተጠቅሰዋል።

በስምጥ ሸለቆ ተፋሰስ ከሚገኙ ሀይቆች ውስጥ የዝዋይ፣ ላንጋኖና እና አብያታ የውሃ ጥራት ደረጃን ለማወቅ 11 ናሙናዎችን በመውሰድ 16 የማዕድን ይዘት እና ኹለት የማይክሮ ባዮሎጂ የምርመራ ዓይነቶችን በማካሄድ የፍተሻው ውጤት ተጠናቆ የውሃ ጥራት ምርምር እየተካሄደ እንደሚገኝ ታውቋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ብቻ በየእለቱ ከምድር እና ከርሰ ምድር የውሃ ምንጮች ከ600 ሺሕ ሜትር ኪዩብ በላይ ውሃ በማምረት የሚያቀርብ ሲሆን፣ ከ500 ሺሕ በላይ ተጠቃሚዎች አሉ።

የገፈርሣ ግድብና ማጣሪያ ጣቢያ በቀን 30 ሺሕ ሜትር ኪዩብ ውሃ፣ የለገዳዲ ግድብና ማጣሪያ ጣቢያ የድሬ ግድብ ጨምሮ በቀን 195 ሺሕ ሜትር ኪዩብ ውሃ የማምረት አቅም አላቸው። የጉድጓዶች እና ሌሎች የከርሠ ምድር ምንጮች ውሃ የማምረት አቅምም በቀን 383 ሺሕ ሜትር ኪዩብ ነው።

አዲስ አበባ ያለው የውሃ አቅርቦት በቂ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ በርካታ ቅሬታዎች የሚቀርቡ ሲሆን፣ ከጥራት ጋር የተያያዙ ችግሮችም ይስተዋላሉ። አንድ የውሃ ማስተላለፊያ መስመር በየ15 ዓመቱ መቀየር የሚገባው ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ይህ ሲተገበር አይስተዋልም።

ቅጽ 2 ቁጥር 65 ጥር 23 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here